Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ባንኮች ደንበኞች መረጃ መስጫ ጊዜ ሊጠናቀቅ ቀናቶች ብቻ ቀሩ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ባንኮች የደንበኞቻቸውን ሙሉ መረጃ እንዲያጠናክሩ የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በዚህ ሳምንት የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ከተሰጠው ቀነ ገደብ በኋላ መረጃዎችን ያልሰጡ ደንበኞች አካውንታቸውን ማንቀሳቀስ እንደማይችሉ ታውቋል፡፡

ባንኮች ይህንኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ተከትለው ደንበኞቻቸው ወደ ባንክ ቀርበው በመመርያው መሠረት አስፈላጊውን መረጃ እንዲሰጡ እያደረጉ ቢሆንም፣ ጥቂት የማይባሉ ደንበኞች በመመርያው መሠረት ወደ ባንክ በመሄድ በመመርያው የተቀመጠውን መረጃ እየሰጡ አይደለም፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የተያዩ ባንኮች የሥራ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ ባለፉት ስድስት ወራት መመርያው በሚጠይቀው መሥፈርት መሠረት የደንበኞቻቸውን መረጃ እየሰበሰቡ ነው፡፡ ይሁንና ይህንን መረጃ ላለመስጠት እስካሁን ያልቀረቡ የባንክ ደንበኞችን መረጃ የማሰባሰቡ አስፈላጊነትን በመጥቀስ፣ መረጃውን እንዲሰጡ እያበረታቱ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ጥቂት የማይባሉ ደንበኞች ቀርበው መረጃውን ባለመስጠታቸው ባንኮች ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ወደ ደንበኞቻቸው በመደወል መረጃዎችን እየተቀበሉ የመመርያው ድንጋጌ መተግበር እየገቡ ነው፡፡

ባንኮች በመመርያው መሠረት አስፈላጊውን መረጃ ሰብስበው እንዲያጠናቅቁ የተሰጣቸው ጊዜ የሚጠናቀቀው የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በመሆኑ፣ ይህ የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ዛሬን ጨምሮ አራት ቀን ብቻ የቀረ በመሆኑ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለደንበኞች ዕድል በመስጠት እየሠሩ መሆናቸውንም ያነጋገርናቸው የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ 

መመርያውን ለማስፈጸም እስካሁን ባንኮች ለደንበኞቻቸው ጥሪ በማድረግ በግንባር ቀርበው ፎርሙን እንዲሞሉ እያደረጉ ሲሆን፣ የጊዜ ገደቡ የመጠናቀቂያ ሳምንታት ላይ ግን በስልክ ጭምር በመጠቀም እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ከየካቲት 21 ቀን 2014 በኋላ መረጃዎቻቸውን ለባንክ ያልሰጡ የባንክ ደንበኞች አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ የሚደረግ በመሆኑ እንዲህ ያለው ችግር እንዳይገጥማቸው ታስቦ መሆኑን ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር አቶ ፍሬዘር አያሌው ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በመመርያው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መሠረት የባንክ ደንበኞች ወደ ባንክ በመሄድ መረጃውን የማይሰጡ ከሆነ አካውንታቸውን ባንኮች እንዳይንቀሳቀስ የማድረግ ሥልጣን ስለተሰጣቸው በዚሁ መሠረት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ይህ በመመርያው በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን፣ መረጃቸውን ባለመስጠት አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ የሚደረጉት ደንበኞች አካውንታቸውን ማንቀሳቀስ የሚችሉት በአዲሱ አሠራር መሠረት በመመርያው የተቀመጠውን መረጃ ሲሰጡ ብቻ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡  

መመርያው በሚያዘው መሠረት ባንኮች የደንበኞቻቸውን ሁኔታና ታሪክ የሚከታተል አዲስ አደረጃጀትና ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አሠራር እንዲዘረጉ የሚያስገድድ ለመሆኑ በዚሁ መሠረት ባንኮች ዝግጅት በማድረግ መረጃዎችን እየሰበሰቡ ቢገኙም ሥራው አድካሚ እንደነበር ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ስለመሆኑ የሚገልጹት የባንክ የሥራ ኃላፊዎች እስከ የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ መረጃ ያልሰጠ ደንበኛቸውን አካውንት እንዳያንቀሳቅሱ መመርያው የሚያስገድድ በመሆኑ በቀረው ቀናት ደንበኞች መጃውን እንዲሰጡም ከማሳሰብ አልተቆጠቡም፡፡

ቀነ ገደቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ አሁንም ደንበኞችን በመጎትጎት ፎርሙን እንዲሞሉ የሚደረግ መሆኑን የጠቀሱት የእናት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ አንዳርጌ፣ በበኩላቸው ደንበኞች በቀረበው ጊዜ ቀርበው መረጃውን እንዲሰጡ መክረው እንዲህ ያለው የመረጃ አሰባሰብ ብዥታ የሌለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

አንዳንድ ደንብኞች በፎርሙ ላይ የሚጠየቀው ወርኃዊና ዓመታዊ የገቢ መጠን መጠየቁ ለምን? የሚል ጥያቄ በማንሳት መረጃውን ከመስጠት ሲቆጠቡ የሚታይ በመሆኑ፣ ይህንን ብዥታ በማጥፋት ደንበኞችን ማሳመን የባንኮች ተጨማ ሥራ ሆኖ መቆየቱንም ያመላክታሉ፡፡

መረጃውን መስጠት ግድ ነው፡፡ መረጃው ከምንም ጋር የተያያዘ ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ አካውንቱ እንዳይንቀሳቀስ ከተደረገ በኋላም ማንቀሳቀስ የሚቻለው ወይም አዲስ አካውንት መክፈት የሚቻለው ፎርሙ ሲሞላ ብቻ መሆኑን ካነጋገርናቸው የባንክ ኃላፊዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመሆኑም ደንበኞች ከአላስፈላጊ ብዥታ ወጥተው መመርያው የሚደነግገውን ማሟላት አስፈላጊ መሆኑንም አፅንኦት ሰጥተው እየገለጹ ነው፡፡

አያይዘውም በተለይ ቼክ የሚያንቀሳቅሱ የባንክ ደንበኞች፣ በብሔራዊ ባንክ ድንጋጌ መሠረት መረጃውን ቀርበው ካልሞሉና በዚሁ ምክንያት አካውንታቸው የማይንቀሳቀስ ከሆነ ይከፈል ያሉት ቼክ የማይከፈል በመሆኑ እንዲህ ያለው ችግር እንዳይገጥማቸው ያሳሰቡት የባንክ ኃላፊዎች፣ ለማይቀረው ነገር በቶሎ የሚፈለግባቸውን ይሙሉ ብለዋል፡፡

በዚህ መመርያ የተደነገገውን ማስፈጸም ከባድ ሥራ በመሆኑ መረጃ የማሰባሰቡ ሥራ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገዋል የሚል ምልከታ ቢኖርም፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተሰጠ ምላሽ የለም፡፡ እንደ አንዳንድ የባንክ የሥራ ኃላፊዎች ግን ይህንን  መረጃ የማሰባሰቡ ሥራ ተጨማሪ የጊዜ  ገደብ ሊሰጠው ይገባ ነበር ይላሉ፡፡ መመርያው ከመተግበሩ በፊትም ደንበኞች በቂ መረጃ ማግኘት እንደነበረባቸው ገልጸው፣ አሁን የተሰጠው ጊዜ ገደብ ከተጠናቀቀ በኋላ እንዳይንቀሳቀሱ ሊደረጉ የሚችሉ አካውንቶች፣ የገንዘብ እንቅስቃሴው ላይ ችግር እንዳይፈጥር መታሰብ እንዳለበትም ይመክራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያው የሚተገበርበትን የጊዜ ገደብ ማራዘሙ አስፈላጊነት ላይ ከባንኮች ጋር ተነጋግረዋል የሚል መረጃ ቢኖርም አቶ ፍሬዘር ግን የቀረበልን ነገር የለም ብለዋል፡፡

የዚህ መመርያ ዓላማ በግልጽ በመመርያው መግቢያ ላይ ተቀምጧል ያሉት አቶ ፍሬዘር፣ በአገራችን ብሔራዊ መታወቂያ ባለመኖሩ ከባንክ ሒሳብ መክፈት ከገንዘብ መክፈልና ማስቀመጥ ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች በመታየታቸው ይህንን ችግር ለመፍታት ተግባራዊ የተደረገ ነው፡፡

በመመርያው ላይ እንደተጠቀሰውም በጥቁር ገበያና በሌሎች ሕገወጥ ተግባራት የተሰማሩ አካላት ይህንን ክፍተት ሲጠቀሙ የሚስተዋል በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል መመርያው መውጣቱን ያመለክታል፡፡

በዚሁ መሠረት ባንኮች አዲስ ለተጀመረው ብሔራዊ መታወቂያ፣ ለዜጎች የመስጠት ሒደቱ እስኪደርስ የፋይናንስ ተቋማት ለደንበኞቻቸው መለያ እንዲሰጡ መመርያው የሚያስገድድ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮች ከ72 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች ያሉዋቸው ሲሆን ከእነዚህ ደንበኞች ውስጥ አንዳንዶች ሁለትና ከዚያ በላይ የባንክ አካውንት ያላቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት ከአንድ በላይ የባንክ አካውንቶች ያላቸው ደንበኞች አካውንታቸውን በአንዱ እንዲጠቀልሉ የሚያዝ ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ወሮችም ባንኮቹ ይህንን መመርያ ለማስፈጸም ሲሠሩ ከቆዩት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ይኸው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች