Tuesday, May 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ከአርባ እስከ ሃምሳ በመቶ ያህሉ መካንነት የሚከሰተው ከወንዶች ጋር በተያያዘ ችግር ነው›› ፌሩዝ አውካሽ (ዶ/ር)፣ የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ ሕክምና ዳይሬክተር

ልጅ መውለድ የትዳር መሠረት ነው፡፡ በጥንዶችም መካከል ፍቅር፣ መግባባትና መተሳሰብ በሞላበት መንገድ የትዳር ጊዜያቸውን እንዲያጣጥሙ የማድረግ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ይህ ዕድል ያልተሳካላቸው ጥንዶች ግን ግራ ሲጋቡ ይስተዋላል፡፡ ሴቷም የመውለጃ ጊዜዬ ሳያልፍ ዕድሌን ከሌላ ዘንድ ልሞክር ስትል፤ ወንዱም ወላድ ሴት ፍለጋ መንቀሳቀስ ይጀምራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ደግሞ ለትዳር መፍረስ ዋነኛው ምክንያት ይሆናል፡፡ በመደበኛ መንገድ እርግዝና እምቢ የሚላቸው ጥንዶች ለሳይንስ ምሥጋና ይግባውና በሕክምና ልጅ መውለድ የሚችሉበት መንገድ ተፈጥሯል፡፡ ቀደም ባሉት ዓመታት ይህንን ሕክምና ለማግኘት ወደ ውጪ አገር መሄድ ግድ ነበር፡፡ አሁን ግን ሕክምናውን በአገር ውስጥ መስጠት ከተጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ ይህንን የሕክምና አገልግሎት እየሰጠ ያለውም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ ሕክምና ማዕከል ነው፡፡ የመካንነት ሕክምናና ተያያዥ ጉዳዮችን አስመልክቶ ታደሰ ገብረማርያም የማዕከሉን ዳይሬክተር ፌሩዝ አውካሽን (ዶ/ር) አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- መካንነት ሲባል በአብዛኛው ኅብረተሰብ የሚነገረው በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት ችግር መስሎ ነው፡፡ የወንድ መካንነት የለም እንዴ?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- በኅብረተሰቡ ዘንድ መካንነት ሲባል ብዙ ጊዜ በሴቶች ላይ ብቻ የሚከሰት ችግር መስሎ ይታያል፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከትና አረዳድ ነው፡፡ በዓለም ውስጥ በቅርቡ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከሆነ ግን ከ40 እስከ 50 በመቶ መካንነት የሚከሰተው ከወንዶች ጋር በተያያዘ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመደበኛው መንገድ መውለድ የማይችሉ ጥንዶች በምን ዓይነት የሕክምና ዘዴ ነው መውለድ የሚችሉት?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- በጥንዶች ላይ የሚደርሰውን መካንነት ለመከላከል፣ ወይም እንዲወልዱ ማድረግ የሚቻለው በተለምዶ ‹‹ቴስት ቲዩብ ልጅ›› የሚባለውን በመፍጠር ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ከጥንዶች ላይ የዘር ፍሬያቸው በረቀቀ መንገድ ተወስዶ ላቦራቶሪ ውስጥ እንዲዋሃድ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ፅንሱ ላቦራቶሪ ውስጥ ከተፈጠረ በኋላ ለአምስት ቀናት ያህል እንዲያድግ ይደረጋል፡፡ ከተጠቀሱት ቀናት በኋላ ወደ ሴትየዋ ማሕፀን ውስጥ በመክተት ወይም በመመለስ እርግዝናው እንዲቀጥል የሚደረግበት ልዩ የሕክምና ዓይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕክምናው በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዴት ይገመግሙታል?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከ1000 በላይ የሚሆኑ ጥንዶች ይህንን የሕክምና አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ አገልግሎቱ በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰርጾ በመግባቱ ወይም በስፋት እየታወቀ በመምጣቱ የተነሳ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎቱን ለማግኘት ቢያንስ ለሦስት ዓመታት ያህል ወረፋ መጠበቅ ግድ ሆኗል፡፡ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ ከመጀመሩ አስቀድሞ ጥንዶች ውጪ አገር እየሄዱ አገልግሎቱን ያገኙ ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ ለከፍተኛ ወጪና ለውጭ ምንዛሪ ብክነት አስተዋጽኦ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

ሪፖርተር፡- መካንነት ለሚያጠቃቸው ወይም ማስረገዝ ለሚሳናቸው ወንዶች ምን ዓይነት ሕክምና ነው የሚደረግላቸው?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- ይህንን በተመለከተ ሁለት ዓይነት ሕክምና አለ፡፡ የመጀመርያው ሕክምና የወንዶች የዘር ፍሬ በፈሳሽ ውስጥ ሳይገኝ ሲቀር ከቆለጣቸው በቀዶ ሕክምና የምትገኘውን ትንሿን የዘር ፍሬ በልዩ ዓይነት መርፌ ወስዶ የሴቷ እንቁላል ውስጥ ማስገባትና ፅንሱ እንዲፈጠር ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው አካሄድ ደግሞ የወንዶችን የዘር ፍሬ ወስዶ በላቦራቶሪ ውስጥ የተለያየ ትሪትመንት [ሕክምና] መስጠት፣ ከዚያም በጣም ጥሩዎችን የዘር ፍሬ መርጦ የሴቷ የዘር ፍሬ የሆነው እንቁላል ተመርቶ በሚፈለፈልበት ቀን ወደ ማሕፀኗ በማስገባት የሚደረግ የሕክምና ዓይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለወንዶች የወሊድ መከላከያ ዘዴ ይኖር ይሆን?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- በወንዶች ላይ የሚሠራ የእርግዝና/የወሊድ መከላከያ ዘዴ አለ፡፡ ይኼውም የወንዶች የዘር ፍሬ ማምረቻ አካል ከሆነውና በግራና ቀኝ ካሉት ኳሶች መሳይ ድብልብል ነገሮች ተነስቶ ወደ ብልት የሚያገናኘውን ቱቦ በመቁረጥ የዘር ፍሬው ከፈሳሹ ጋር እንዳይገናኝ የሚያደርግ ሕክምና ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕክምና ‹‹ቫስክቶሚ›› ይባላል፡፡ በጣም ጠቃሚና ተጓዳኝ በሽታ የማያስከትል የእርግዝና መከላከያ መንገድ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም አገሮች በስፋት ይሠራበታል፡፡ በተለይም ባደጉ አገሮች ውስጥ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ የሚሰጥ የእርግዝና መከላከያ ዘዴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሕክምናው መሰጠት ከጀመረ ከ35 ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ የዕድሜውን ርዝማኔ ያህል ግን እስከዛሬ ድረስ ምንም ዓይነት መስፋፋት አልታየበትም፡፡ አገልግሎቱም ያገኙት በጣም ጥቂት ወንዶች ብቻ  ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ያልተስፋፋበት ምክንያት ይታወቃል?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- ያለመስፋፋቱ መንስዔ እንደሚመስለኝ በማኅበረሰባችን ውስጥ ካለው የወንዶች የበላይነት ጋር ተያይዞ የመጣ ስሜት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከዚህም ሌላ ሕክምናውን አስመልክቶ የሚታየው የተዛባ አመለካከት ለሕክምናው መስፋፋት እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ የተዛባውም አመለካከትና አስተሳሰብ ሕክምናው የግብረ ሥጋ ግንኙነትን ሊቀንስና ብልትም አልቆም ሊል ይችላል ከሚል ስሜት የተፈጠረ ነው፡፡ ይህንንም አመለካከት ሳይንስ አይደግፈውም፡፡ ከተጠቀሱት ችግሮች ጋር የሚያገናኝ አንዳችም ነገር የለም፡፡ ቫስክቶሚ በሚሠራበት ወቅት የግንኙነት ፍላጎትን አይቀንስም፡፡ የብልት መቆም ችግር አይኖረውም፡፡ ቀዶ ሕክምናውም ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ በላይ አይፈጅም፡፡ አሁን ቀዶ ሕክምናው እየተሻሻለ መጥቶ በቢላዋ መጠቀም ቀርቶ በጣም ቀጭን በሆነች መሣሪያ ጠቅ አድርጎ እንዲከፈት ማድረግ ብቻ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሕክምናው ባለመስፋፋቱ የተነሳ በዘርፉ በተሰማሩ ባለሙያዎች ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ አለ?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- አዎ አለ፡፡ ብዙ ወንዶች ይህንን ሕክምና ባለማድረጋቸው የተነሳ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ልምድ ለማካበት በሚያደርጉት ጥረት ላይ እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ማዕከላችሁ አሁን የደረሰበትን ደረጃ ሊያስረዱን ይችላሉ?

ዶ/ር ፌሩዝ፡- የመካንነትና የሥነ ተዋልዶ በኢትዮጵያ የመጀመርያው የመንግሥት የጤና ተቋም ነው፡፡ ማዕከሉ የተቋቋመው አሜሪካ በሚገኘው የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ትብብርና ዕገዛ ነው፡፡ ትብብርና ዕገዛውም በሰው ኃይል ሥልጠና፣ ፋሲሊቲን በማሟላትና የፋይናንስ ድጋፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን ከዚህ ሁሉ ድጋፍ ተላቅቆና ራሱን ችሎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎቹም በሙሉ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ከዕውቀት እስከ ሕይወት ክህሎት

ዋርካ አካዴሚ ከትምህርት አመራርና ፔዳጎጂ፣ ከሳይኮሎጂ፣ ከዓለም አቀፍ ኪነ ጥበብ፣ ከኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ከባንኪንግና ዓለም አቀፍ ፋይናንስ አመራር ሙያዎች በተውጣጡ ባለሙያዎች የተቋቋመ የትምህርት ተቋም ነው፡፡...

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...