Tuesday, February 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጉራማይሌ!

ከልደታ ወደ ፒያሳ የሚደረገው ጉዞ ሊጀመር ነው፡፡ ዕልፍ ብንሆንም ብቻ ለብቻ ቆመናል። ሐሳቦቻችንና ውጥኖቻችን በሕይወት መድረክ ላይ የተጠላለፉ ነባርና ደብዛዛ መስመሮች መስለዋል፡፡ ገንዘብን፣ ብሔርን፣ እምነትን፣ የገዛ አቋምን፣ ቡድንተኝነትን፣ ወዘተ መነሻና መድረሻችን አድርገን ዘመኑም ይታዘበናል፡፡ ይኼው እየደረቡ መታረዝ፣ እየበሉ መራብ፣ እያፈቀሩ መጠላት ሆኗል ልማዳችን። በወል አቧድኖ የሚያቧጭቀን አባዜ በዝቶ በነጠላ ኑሮ ያብከነክነናል። ተሳፋሪ ይወርዳል፣ መልሶ ይሳፈራል። ሥር እየሰደደ ያስቆዘመን ሰብዓዊነት የራቀው የጥላቻ ስሜት ግን መቋጫ ፌርማታ እንዳጣ ነው። ሳንነጋገር ተግባብተን፣ ይኼንኑ የብቻነት ቅዝምዝም መንገድ ያበጀንለት መስሎን በፋሽን አልባሳት፣ በሞዴል አውቶሞቢል፣ በዘመነኛ ደርበ ብዙ የመኖሪያ ቤት፣ በቴክኖሎጂ በተራቀቁ ጌጠኛ የእጅ ስልኮች ብንሸፍነውም፣ ገመናችን ደጅ ተሰጥቶ ፀሐይ ይሞቃል። ምክንያቱ ደግሞ የጀመርነው የቁልቁለት መንገድ ማለቂያ የለውምና፡፡ ስሜትና ሐሳብ የመንገዳችን ገባር ናቸውና፡፡ ወይ እኛ!

እንባና ሳቅ ሰው የመሆን ዕዳ ነባር ምሰሶዎች ናቸው ይባል ነበር። ይኼው እዚያ የታክሲው ጎማ ሥር አንድ ጠኔ ያደባየው ወድቆ እጆቹን መዘርጋት አቅቶት፣ ያው መንገዱን ተሻግሮ አንዱ ሕይወት አልጋ በአልጋ ሆኖለት፣ ጭረት የማያውቀው የሚመስል አፍላ ጎረምሳ ደረቱን አሳብጦ ሲንጎማለል፣ የመሸብን ሳይነጋልን የነጋላቸው ደግሞ የንጋታቸው ብርሃን ዓይን ወግቶ ያጠፋል። ሕይወት በአድሏዊነት ስትታማ ደግሞ መልሳ የወደቀውን አንስታ፣ ከፍ ከፍ ያለውን ዝቅ አድርጋ ስሟን እያደሰች ግራ ገብቷት ግራ ታጋባለች። እንጀራን ተገን አድርጎ የሚያጣድፈን ኑሮ ሞልቶ ላይሞላ፣ ጎድሎ ላይጎድል የጎዳናው ሥውር ጥያቄ ከትርምሱ ጀርባ ለምን? ለማን? እንዴት? ከየት? ወዴት? እያስባለ ብቻ የሚኮረኩር ይመስላል። ባይመስልም ለነገሩ ኑሮና ኗሪው ትርፉ መጠየቅ ብቻ ነው። ካልተጠየቀ ደግሞ መልስ የለም፡፡ መልስ የሌለው ሕይወት ደግሞ ይሰለቻል፡፡ እየሰለቹ፣ እያሰለቹና እየተሰለቻቹ መኖር ከመቃብር በላይ ይከብዳል ይላሉ የገባን ነን የሚሉ፡፡ ሳይገባን እየገባን እየኖርን ነው መሰል ከሰው በታች የምንኖረው!

ጉዟችን ተጀምሯል። ከሾፌሩ ጀርባ የተሰየሙ ወጣቶች በሞባይል ስልኮቻቸው እያወሩ ነው። ‹‹እሺ እባክህ እናንተ በውስኪ እኛ ደግሞ በድራፍት እያዘገምን ነው…›› ሲለው፣ ‹‹ክብሩ ይስፋ ለእርሱ ለመድኃኔዓለም…›› ይላል በወዲያ በኩል። ‹‹ምናለበት ለብቻቸው ቢያወሩ። ላውድላይ አድርገው ሲያደነቁሩን ዝም ትላለህ?›› ይላል መሀል መቀመጫ ላይ ከጎኔ የተሰየመ ጎልማሳ። ወያላው በፈገግታ ብቻ ጥሎን ሸሸት አለ። ‹‹እኔ የምለው? ዲሲ እንዴት ነው ዌዘሩ?›› አለ እዚህ ሸገር የፒያሳ ታክሲ የተሳፈረው። ‹‹አሸወይና ነው። ምን ኑሮማ ያለው አዱገነት አይደለም እንዴ? እኔማ ከእንግዲህ ቆይ ታየኛለህ ያለችኝን ሰባስቤ ሮጬ መምጣት ነው…›› ይለዋል። ‹‹እኛ በየት በኩል ሮጠን እንውጣ እንላለን እሱ ሮጬ እመጣለሁ ይላል። አይ አለማወቅ። ከራርመው ሲለዩዋት እንኳን አገር ወፍም ታባባለች እኮ…›› ይላል ጎልማሳው። አንዳንዱ ደግሞ እንደ እርጎዝንብ ጥልቅ ማለት ሲወድ!

‹‹የሚናገረውን አያውቅምና ይቅር በሉት ብሎ ማለፍ ነው…›› ባዩዋ ደግሞ ከጀርባ፣ ሦስተኛው ረድፍ ላይ ጥቁር ሰማያዊ ባርኔጣ ደፍታ አንዳች የሚያህል መነጽር ዓይኗ ላይ የደነቀረች ወጣት ናት። ‹‹እህም…›› ይላል ጎልማሳው በመነጽሯ ውስጥ ዓይን ዓይኗን እያየ። ‹‹እኔ የምልህ እስኪ ሚስትም ፈልጉልን እንጂ። እኛማ እንዳያያዛችን ማጥመድ የምንችል አልመሰለኝም…›› ሲል የዲሲው ይኼኛው፣ ‹‹ዕድሜ ለለውጥ መሪውና ለዳያስፖራ ተንከባካቢው መንግሥታችን ከየስደታችሁ ሰብስቦ አምጥቶ በተናችሁ፣ ይኼው ለመድናችሁ። ካልሆነማ እንዳንተ ይኼን ያህል ዘመን ዲሲ መኖር አይደለም አንድ ሦስት ሚስት አታገባም ነበር?›› አለውና ተሳሳቁ። በዚህ መሀል ኔትወርክ አስቸገራቸውና ጨዋታቸው ተደነቃቀፈ። ‹‹ኔትወርኩ አሁንም እንደ ባሰበት ነው…›› ከማለቱ የዲሲው፣ ተሳፋሪው ወዳጃችን ደግሞ፣ ‹‹ዛሬም፣ ትናንትም፣ ነገም እንደ ባሰበት ነው…›› ብሎ ቻው ሳይለው ባትሪው አለቀ። ባትሪውም የቴሌ ችግር ነው እንዳትሉ ብቻ!

ወያላው ሒሳብ እየሰበሰበ ነው። ሾፌራችን እንደ ሰደድ እሳት ጨዋታ ሲቀጣጠል፣ ‹‹ታክሲ ውስጥ በህቡዕ መደራጀት ክልክል ነው...›› እያለ ለወያላው የሬዲዮኑን ድምፅ ጨመር ያደርገዋል። የስፖርት ትንታኔ እናደምጣለን። ‹‹ክርስቲያኖ ሮናልዶ የማንቼ ካፒቴን ቢሆን የሚሰማን ደስታ በእውነቱበእውነቱሞራላችንን የሚገነባ ነው…›› ይላል ተንታኙ፡፡ ‹‹ስለራሱ ሞራል አያወራም እንዴ? ለምን የእኛን ይጨምራል?›› ይላል ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹እውነት ግን ሮናልዶ አንጀት ይበላል። ሁሌ እኮ እንዳበበና እንደ ጎመራ ነው…›› ስትል ባለመነጽሯ፣ ‹‹ሊዮኔል ሜሲ ሳይሳካለት ዓይተሽ ታውቂያለሽ?›› ብሎ ጎልማሳው አፈጠጠባት። ‹‹በኳስ መፋጠጡን ትታችሁ በአገር ጉዳይ አትፋጠጡም? ለምሳሌ በአገራዊ ምክክሩ ላይ… .›› ብሎ አንዱ ከጋቢና ወሬ አስገለበጠ። ከሾፌሩ ጀርባ የተየሰመች ወይዘሮ፣ ‹‹በስንቱ እንፋጠጥ?›› አለችው። ወዲያው ጋቢና የተሰየመው ወጣት ቀልባችንን ወደ ሜሲና ሮናልዶ ፍጥጫ ወሰደው።

 ‹‹እኔ እኮ የእኛ ሰው ነገር ከመጠን በላይ ሆኖብኛል፡፡ ቁጭ ብለን በጠረጴዛ ዙሪያ የእኔ ርዕዮተ ዓለም፣ አስተዳደር፣ ፍትሕ፣ አገር ግንባታ፣ ኢኮኖሚ፣ ልማት፣ ወዘተ በማለት ለመፎካከር ታጥቀን መነሳት ሲኖርብን፣ እንደ ግመል ሽንት ወደኋላ እያፈገፈግን ሰበብ ስንደረድር ያስገርመኛል፡፡ ለመነጋገር የማንመች ጉዶች…›› እያለ በታከቱ ዓይኖቹ ቃኘን፡፡ አንዳንዴ ያሰኛል!

ጉዞው በጦፈ ወሬ ታጅቦ ሳይታወቀን ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ኡ…ሁ…ሁ…ሁ…›› ብሎ አንዱ ወደ መጨረሻ ወንበር በረዥሙ ከሳል ጋር ተነፈሰ። ‹‹ምነው? ቻይና ሄደህ ነበር እንዴ?›› አሉት አጠገቡ የተሰየሙ አዛውንት። ‹‹የለም እዚህ ነው ያለሁት፣ ግን ካናዳ ተንቀባርሬ መኖር አምሮኝ ነው…›› ብሎ መለሰላቸው። ‹‹ሲያምርህ ይቅር እንዳንልህ አንተም እንደ እኛ ብዙ አምሮህ የቀረ ነገር ስለሚኖር ሌላ ዕጦት አንመኝልህም…›› አለችው ቆንጂት። ‹‹ደግሞ ካናዳ ተንቀባሮ መኖር ያማረው ማን ተንቀባሮ ሲኖር ዓይቶ ነው? እንኳን ተሰዶ የሄደው እዚያም የተወለደ አልደላው…›› ጎልማሳው ገባበት። ‹‹ድሎት? የምን ድሎት?›› ጠየቀች ወይዘሮዋ። ‹‹አልሰማችሁም ይህቺን ጆክ። ሰውዬው በቃ ኑሮ ከበደውና የእኔ ቢቀር አህያዬን በድሎት ማኖር አለብኝ ብሎ ቆርጦ ተነሳ። ከዚያ ቀስ እያለ የዕለት ምግቧን በመጠንም በዓይነትም ሲጨምር መጨረሻ ላይ አህያው ድሎት በዝቶበት ፍግም አለ። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‘ወይኔ በድሎት ላኖረው ያሰብኩት አህያዬ ሞተ!’ ጉድ እኮ ነው እያለ ሲያለቅስ ከረመ…›› ሲል ተሳፋሪዎች ግራ ተጋብተው ተያዩ። ‹‹ድንቄም ቀልድ፣ እንኳን በድሎት እንዲሁ በድህነት መኖር ተቻለ እንዴ ዘንድሮ?›› ብላ ወይዘሮዋ ነገር ማምጣት ስትጀምር፣ ‹‹እዚህ አገር በድሎት መኖር ስለማያዋጣ እኮ ነው ካናዳ በድህነትም ቢሆን ተንቀባርሬ መኖር ያማረኝ…›› ብሎ ያ ቀልደኛ ወጣት ጣልቃ ገባባት። ‹‹መጨረሻ›› ብሎ ወያላው ሲያወርደን ውስጣችን ያለው ጉራማይሌ ከየልቦናችን ጋር አነጋገረን፡፡ ኧረ ስንቱ ነገር ይሆን ያራራቀን? ስንቱስ ይሆን አላግባባ ያለን? ከስንቱ ጋር ይሆን ሆድና ጀርባ ሆነን የምንኖረው? ጉራማይሌ ተሁኖስ ይዘለቃል ወይመልካም ጉዞ!

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት