- ክቡር ሚኒስትር በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ ሰማሁ፣ ምን ገጠመዎት?
- ጎሽ እንኳን ቶሎ መጣህ፡፡
- በሰላም ነው?
- ምን ሰላም አለ ብለህ ነው?
- ምን ገጠመዎት?
- በሉ ተባለ እኔም ፈጽሞ የሚታሰብ ነገር እንዳልሆነ ተናገርኩ… አሁን በድንገት ተነስተው ሌላ ይላሉ፡፡
- አልገባኝም ክቡር ሚኒስትር? ፈጽሞ አይታሰብም ያሉት ምንድነው?
- ድርድር ነዋ፡፡
- የግድቡን ድርድር ማለትዎ ነው?
- ወዴት ነው የምትሄደው አንተ ደግሞ?
- ድርድር ከሆነ የሚሆነው የህዳሴ ግድቡ ድርድር ይሆናል ብዬ ነው… ስላልገባኝም ነው?
- እዚህ የአገር ውስጥ ነው… የሰሜኑ ድርድር ነው እንጂ፡፡
- እሱንማ በሚገባ ሲያስረዱ አልነበረም እንዴ? እንዲያውም ሰሞኑን የተናገሩትን ብዙ ሰዎች ሲቀባበሉት አይቻለሁ።
- ምን ብዬ የተናገርኩትን ነው የተቀባበሉት?
- አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ፈጽሞ ድርድር አይኖርም፣ አይታሰብም ያሉትን፡፡
- ይኸውልህ… እሱን እኮ ነው የምልህ፣ እኛን እንደዚያ በሉ ይላሉ ውሎ ሳያድርና የተናገርነውን ሳያዘጋጁን ሐሳብ ይቀይራሉ፣ ታዲያ ቃል አባይ እንጂ እንዴት ሰላም ልሆን እችላለሁ?
- ድርድር ይደረጋል ተባለ እንዴ?
- የት ነበርክ አንተ ደግሞ…?
- አልሰማሁም ክቡር ሚኒስትር።
- ተባለ እንጂ… ለዚያውም መላው ሕዝብ እንዲያውቀው ተደርጎ ነው የተገለጸው፡፡
- እርስዎ ለምን ተጨነቁ ታዲያ?
- ምን ይላል ይኼ? ድርድር ፈጽሞ አይታሰብም ብዬ ስናገር ነበር እያልኩህ? ወዳጆቻችን ቢጠይቁ ምን እመልሳለሁ አሁን?
- መንግሥት በይፋ የገለጸውን ነገር ወዳጆቻችን ምን ብለው ሊጠይቁ ይችላሉ?
- አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ድርጅት ጋር በጭራሽ ድርድር አይኖርም ያልከው ከምን ተነስተህ ብለው መጠየቃቸው አይቀርም።
- እንደዚያ ማለትዎ ነው ያሳሰበዎት?
- እንዴት አያሳስበኝም? አስረግጬ እኮ ነው የተናገርኩት፡፡
- ይህ ብዙ አያሳስብም… መፍትሔ አለው፡፡
- ምን ዓይነት መፍትሔ? ብዙ ታለፋኛለህ እንጂ ብልህ እኮ ነህ?
- መፍትሔው ቀላል ነው፡፡
- እኮ ምንድነው?
- የተናገሩትን ደግመው መናገር ነው።
- ምን እያልክ ነው?
- አሸባሪ ተብሎ ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ፈጽሞ ድርድር አይኖርም፣ አይታሰብም ይበሉ፡፡
- ጤነኛ አይደለህም እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር አያስቡ መፍትሔው እሱ ብቻ ነው፡፡
- እንዴት?
- ምክንያቱም መንግሥት ወደ ድርድር ሊገባ የሚችለው ይህንን የሕግ ግዴታ ካነሳ ብቻ ነው።
- አልገባኝም?
- ይኸውልዎት ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ብድግ ብሎ ወደ ድርድር ሊገባ አይችልም፣ ወደ ድርድር የሚገባ ከሆነ አስቀድሞ ፍረጃውን ማንሳቱ አይቀርም።
- እህ… ድርድር ከመጀመሩ በፊት ፓርላማው የአሸባሪነት ፍረጃውን እንዲያነሳ ይደረጋል እያልክ ነው?
- በትክክል፡፡
- ስለዚህ እኔ የተሳሳትኩት ነገር የለም ማለት ነው? እንደዚያ ማለትህ ነው አይደል?
- ልክ ነዎት፣ እርስዎ ሽብርተኛ ከተባለ ድርጅት ጋር ድርድር አይኖርም አይደለም እንዴ ያሉት?
- አዎ፡፡
- ስለዚህ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ፍረጃው ስለሚነሳ እርስዎ የተናገሩት ትክክል ነው ማለት ነው።
- አሃ… ድርድሩ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር አይሆንም ማለት ነው? እንደዚያ ነው አይደል?
- በትክክል፡፡
- አንተ ዘንድ መላ አይጠፋም የምለው ለዚህ ነው… ግን…
- ግን ምን ክቡር ሚኒስትር?
- ግን በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
- ምኑ ላይ?
- ፍረጃው ሳይነሳ ድርድር ቢካሄድስ?
- እንደዚያ ሊሆን አይችልም፣ ከሆነም ደግሞ…
- እሺ… ከሆነ ደግሞ ምን?
- ከሆነማ ችግሩ የእርስዎ ብቻ ሳይሆን የመንግሥትም ይሆናል፣ ስለዚህ መንግሥት ፈጽሞ እንደዚያ አያደርግም፡፡
- እንደዚያ አይደለም ማለት ያለብህ!
- እንዴት ልበል?
- መንግሥት ፈጽሞ ከሽብርተኛ ጋር አይደራደርም!
[ክቡር ሚኒስትሩ አመሻሹን ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን እየተላለፈ ያለውን ውይይት በተመስጦ እየተከታተሉ አገኟቸው]
- እንዴ መንግሥት ወሰነ በቃ?
- በፍጹም፡፡
- ይኸው አሁን የተባለውን አዳመጥኩት እኮ?
- ፈጽሞ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር ድርድር አይደረግም፡፡
- አዬ… እኔ ስለእሱ አይደለም የጠየኩህ፣ የመንግሥት ተቋማት በምርመራ ጋዜጠኞች ይመረመራሉ የተባለውን ነው የምልህ።
- እንደዚያ ተብሏል እንዴ?
- ከዚህ በኋላ በመንግሥት ሚዲያዎች የምርምራ ጋዜጠኝነት እንደሚጀመርና የመንግሥት ተቋማት ጉድ እንደሚገለጥ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡
- እሱን እንኳ ተይው፡፡
- እንዴት?
- ጋዜጠኞች ይችሉታል ብለሽ ነው?
- እንዴት አይችሉትም?
- ያስቸገረውን ጋዜጠኛ አንዱ ክልል ወስዶ ሲያስረው ይቆማል።
- የመንግሥት ድጋፍ ስለሚኖራቸው ለማሰር ይቸገራሉ፣ እሳቸውም ባለሥልጣናት በራቸውን ለምርመራ ጋዜጠኞች ክፍት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
- ጋዜጠኛን ለማሰር እንኳን ችግር የለውም… በተለመደው መንገድ በቀላሉ ማሰር ይቻላል።
- እንዴት ተደርጎ? በምን ምክንያት?
- በዘገባው የአንድን ማኅበረሰብ ክብር ነክቷል ብሎ ከአዲስ አበባ ውጪ ማሰር ይቻላል።
- ያላደረገውን?
- እሱን ፍርድ ቤት ይወስነዋል።
- ምንም ችግር አይከሰትም በለኛ?
- አልኩሽ እኮ፣ እንኳን ጋዜጠኛ ዋናውም አልቻሉትም፡፡
- ዋናው ማናቸው?
- ኦዲተሩ!