ከስድስት በላይ የውጭ አገር ኩባንያዎች ይሳተፉበታል
በጤና ክብካቤ አገልግሎት ግብዓቶች፣ በሕክምና መልገያዎችና የመድኃኒት አቅርቦት ላይ የሚያተኩር ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕይና ጉባዔ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡
‹‹ኢትዮ ኸልዝ›› የሚል መጠርያ ያለውና ለስድስተኛ ጊዜ የሚዘጋጀው መድረክ የአገር ውስጥ አምራቾች ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ የሚወስዱበት እንደሚሆን አዘጋጁ ፕራና ኤቨንትስ አስታውቋል፡፡
ተቋሙ እንደገለጸው፣ ከየካቲት 26-28 ቀን 2014 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል በሚካሄደው ዓውደ ርዕይና ጉባዔ ከተለያዩ አገሮች የተውጣጡ ከ60 በላይ ኩባንያዎች የሚሳተፉበት ሲሆን የልምድ ልውውጥም ይደረግበታል፡፡
የፕራና ኤቨንትስ ዳይሬክተር አሰፋ ዓለም (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የጤና ጉባዔው የሚመለከታቸው አምስት ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም የሕክምና አገልግሎት ልህቀትን፣ የታካሚ ደኅንነትን፣ የጨረርና ላቦራቶሪ ምርመራዎችን፣ የመጀመርያ ደረጃ የጤና ክብካቤና መድኃኒት ናቸው፡፡
በጉባዔው ከሚኖረው ውይይት ለሕግ አውጪዎች ግብዓት የሚገኝበት ይሆናልም ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ዋቅቶላ እንደገለጹት፣ በጤና ኢንዱስትሪው ላይ እየታየ ያለውን ችግር ለመቅረፍና ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ ለመውሰድ ዓውደ ርዕዩ ትልቅ ሚና ይኖረዋል፡፡
በዓውደ ርዕዩ የዘርፉ ተዋናዮች የንግድ ልውውጥን የሚያሳድጉበት የገበያ ትስስርን የሚፈጥሩበት፣ እንዲሁም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የዕውቀት ሽግግርን የሚፈጽሙበት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ፖሊሲዎችን እንደ አዲስ ማሻሻሉ፣ ይኼም በዘርፉም ተዋንያን የሆኑ ባለሙያዎችም ሆነ የውጭ አገር ኩባንያዎች ተሳትፏቸው እንዲያድግ የሚያደርግ መሆኑን አቶ ዳንኤል አብራርተዋል፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን የሆነ የፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ማዘጋጀቷን ያስታወሱት አቶ ዳንኤል፣ ይህም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 70 በመቶ የሚሆነውን የሕክምናና የመድኃኒት አቅርቦት ራሷን እንድትችል ያደርጋታል ብለዋል፡፡
በዚህም ኢንዱስትሪ ላይ 29 የዘርፉ ተዋናዮች ለመሳተፍ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸው፣ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ተቋም በአሁኑ ወቅት ግብዓቶችን እያመተ እንደማገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓመት 50 ቢሊዮን ብር ለመድኃኒትና ለሕክምና መገልገያ ዕቃዎች እያወጣች መሆኑን፣ ይህም ኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ማሳደሩን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ እዚህ ግባ የሚባል ምርት እየተመረተ አለመሆኑን የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ምርቱንም ለማምረት እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን በማስወገድ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ያስፈልጋል ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ 12 የመድኃኒት አምራቾች እንዳሉ ገልጸው፣ የእነዚህንም አምራቾች ቁጥር በማሳደግ እንዲሁም ደግሞ የውጭ አገር ኩባንያዎች ወደ ዘርፉ እንዲገቡ በማድረግ መንግሥት አቅጣጫዎችን አስቀምጦ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዘርፉም አብዛኛውን ጊዜ ችግር የሚፈጠረው ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ መሆኑን፣ በተለይም ደግሞ አምራች ኢንዱስትሪዎች የገንዘብ ብድር በሚጠይቁበት ጊዜ ፈጣን ምላሽ ባለማግኘታቸው ኢንዱስትሪው ሊጎዳ ችሏል፡፡
ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው የጤና ጉባዔ ዘጠኝ የሕክምና ሙያ ማኅበራት የሚሳተፉበት መሆኑን የፕራና ኤቨንስ ዳይሬክተር አሰፋ ዓለም (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
እነዚህም ማኅበሮች የተለያዩ ሥልጠናዎች የሚሰጡ ሲሆን፣ በተለይም በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ከሌሎች አገሮች ጋር ውይይት በማድረግ የወደፊት ሥራዎች ላይ አቅጣጫዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይታሰባል ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 16,600 የጤና ኬላዎች፣ 3,778 የጤና ጣቢያዎችና 4,110 የመንግሥት ሆስፒታሎች አገልግሎት እየሰጡ ሲሆኑ፣ የጤና ባለሙያዎችን በማፍራት በተደረገው ጥረት በሺዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችን በየዓመቱ በማስመረቅ፣ የባለሙያዎችን ምጣኔ ወደ 2.1 በመቶ ማሳደግ መቻሉን መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ተገልጿል፡፡
የኢትዮ ኸልዝ ዓውደ ርዕይና ጉባዔ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ በማሰባሰብ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ያለ ሁነት ሲሆን፣ በዘርፉ ለተሰማሩ አምራቾች፣ አስመጪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የምርምርና የትምህርት ተቋማት ከአዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶቻቸውና አገልግሎቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትና አቅጣጫዎችን የሚመለከቱበት ነው ተብሏል፡፡