Thursday, May 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊያልተፈቱት የተሽከርካሪ መንገድ አጠቃቀም ችግሮች

ያልተፈቱት የተሽከርካሪ መንገድ አጠቃቀም ችግሮች

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ፍሰቱን ለማስተካከል መንግሥት ዘርፈ ብዙ ሥርዓቶችን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ ችግሩ አሁንም እየታየ ይገኛል፡፡

በተለይም መደበኛ በሆኑ ትራፊክ ፖሊሶች፣ በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶችና በመንገድ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ትራፊኮች መካከል የሚታየው አለመግባባት የትራንስፖርት ፍሰቱንና አሽከርካሪዎችን እየፈተነ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ኤጀንሲው የትራንስፖርት ፍሰቱን ለማስተካከል በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን አሠልጥኖ ወደ ሥራ ቢያስገባም፣ በሥነ ምግባር ችግርም ሆነ በሌሎች ከአሽከርካሪዎች ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲገቡም ይታያል፡፡

ሁሉም አሽከርካሪዎች ሥነ ምግባር የጠበቁ ናቸው ማለት ባይቻልም፣ አሽከርካሪዎች ቅሬታ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ በታክሲ ሹፍርና ከ14 ዓመታት በላይ የሠሩት አቶ የሺጥላ ዳምጠው፣ በታክሲ ሹፍርና መሥራት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በርካታ ችግሮች እንዳጋጠሟቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በሠሩበት ዓመታት ውስጥ የትራፊክ ሕጉን ሳይጥሱ ብዙ ጊዜ መቀጣታቸውን የሚናገሩት አቶ የሺጥላ፣ የተለይም በሥነ ምግባር ጉድለት የሚታይባቸው የትራፊክ ፖሊሶች ሥራቸው ላይ ጫና እንዳሳደሩባቸው ገልጸዋል፡፡

- Advertisement -

በእርግጥ የሕዝብ ትራንስፖርት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ላይ ብዙ ችግሮች እንዳሉ፣ ያንንም ለመታደግና መሠረታዊ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት ኤጀንሲው መሥራት አለበት ብለዋል፡፡

በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ሥምሪቶች ላይ ተዘዋውረው መሥራታቸውን ያስታወሱት አቶ የሺጥላ፣ ሥራቸውን በሚሠሩ ጊዜ በኤጀንሲው በኩል ሥልጠና ወስደው ወደ ሥራው ከገቡ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች አንዳንዶቹ የሥነ ምግባር ችግር ይታይባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የትራንስፖርት ፍሰቱን ለማስተካከል በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች መሰማራታቸው የሚበረታታ መሆኑን፣ ነገር ግን ብዙ ችግር እንደገጠማቸው አስታውሰዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ያለው የተሽከርካሪ ቁጥርና ተጠቃሚው የማይመጣጠን እንደሆነ፣ አብዛኛውን የማኅበረሰብ ክፍልም ትራንስፖርት ተጠቃሚ መሆኑን አቶ የሺጥላ ገልጸዋል፡፡

አብዛኛውን የታክሲ ሾፌሮች ያለውን የትራንስፖርት ችግር በመረዳት ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እየሰጡ ቢሆንም፣ በከተማዋ ላይ የሚታየው የመንገድ ዝርጋታ መጓተት ምክንያት ቶሎ ቶሎ ለማጓጓዝ መቸገራቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በተለይም ከመደበኛ የትራፊክ ፖሊሶች ውጪ ያሉ በዘርፉ ሥራ የተሰማሩ ባለሙያዎች ላይ የሚታየው የአሠራር ችግር የትራንስፖርት ፍሰቱን ከባድ አድርጎታል ብለዋል፡፡

በመገናኛ፣ በአቦ፣ በሳሪስ፣ በቦሌ፣ በቦሌ ሚካኤልና በሌሎች ቦታዎች ላይ ከፍተኛ የትራንስፖርት ፍሰት ችግር እንዳለ፣ አሁንም ቢሆን ችግሩ እንዳልተቀረፈ ገልጸዋል፡፡

ኑሮን ለማሸነፍና የልጆቻቸውን የዕለት ጉርስ ለመሙላት ደፋ ቀና እያሉ መሆኑን የሚናገሩት አቶ የሺጥላ፣ የታክሲ ሹፍርና ሥራ ከትራፊክ ፖሊስ ጋር ያለው ውጣ ውረድ የሚያማርር ነው ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሌላኛው በኪሎ ሜትር የሚሠራው ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገው የራይድ አሽከርካሪ ወጣት ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ የትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ በሚታየው ክፍተት ምክንያት አብዛኛው ደንበኞች እያማረሩ ነው፡፡

በተለይም ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ የሚሠሩ ሰዎችን የትራንስፖርት አገልግሎት በሚሰጥበት ጊዜ መንገድ ከመጠን በላይ ስለሚዘጋጋ ሥራቸውን እንደሚያስተጓጉል ወጣቱ ተናግሯል፡፡

ሥራ በሌለበት ወቅት መንገድ ዳር ለትንሽ ሰዓት ፓርኪንግ በሚያደርግበት ጊዜ መደበኛ ትራፊክ ፖሊሶችም ሆኑ በኤጀንሲው ሥር የተሰማሩ ባለሙያዎች ሕጉን ባለመከተል ቅጣት እንደሚቀጡት ይናገራል፡፡

የመንገድ መጨናነቅ በሚፈጠርበት ጊዜ በትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ማኔጅመንት ኤጀንሲ በሚያስተዳድራቸው የአውቶቡስና የልዩ ተጠቃሚ መንገዶች ሌሎች ሠራተኞች ጋር በሚታየው አለመግባባት የተነሳ የትራፊክ ፍሰቱ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዲታይ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ አሽከርካሪዎች ያላግባብ ቅጣት ይገጥማቸዋል ብሏል፡፡

አንዳንድ ትራፊክ ፖሊሶች ደግሞ በሕገወጥ መንገድ ሲተላለፉ የተገኙ አሽከርካሪዎችን ቅጣት ከመቅጣት ይልቅ ጉቦ እንደሚቀበሉና ሕጉን እንደሚጣረሱ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

አብዛኛውን ከመደበኛ ትራፊክ ውጪ በዘርፉ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሕግን ከማስከበር ይልቅ ጉቦ አሳዳጅ ሆነዋል ያለው ወጣቱ፣ ይህንንም ለመግታት መንግሥት ክትትል ማድረግ አለበት ሲል አስረድቷል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በኤጀንሲው ሥልጠና ወስደው የተሰማሩ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የሚሠሩት ሥራ የሚበረታታና የትራንስፖርት ፍሰቱን በተወሰነ መልኩ የሚቀርፍ እንደሆነ አብራርቷል፡፡

መንግሥት የትራንስፖርት ፍሰቱን ካስተካከለና በዘርፉ ላይ ያሉ መሠረታዊ ችግሮችን መቅረፍ ከቻለ፣ የትራፊክ አደጋውን በተወሰነ መልኩ መቅረፍ እንደሚቻል ተናግሯል፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ ማኅበረሰቡ በትክክለኛው መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኝ መንግሥት መሥራት እንዳለበት፣ በተለይም በከተማዋ የሚታየው የመንገድ ዝርጋታ በታቀደለት ጊዜ በማጠናቀቅ ፍሰቱን መቀነስ ይኖርበታል ብሏል፡፡

አብዛኛውን ጊዜም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያስፈልገው ጠዋትና ማታ በሠራተኞች መውጫ ሰዓት እንደሆነ ገልጾ፣ በዚህም ወቅት መንግሥት ትራንስፖርት ሥምሪቱን በማስተካከል ማኅበረሰቡን ከእንግልት መታደግ እንደሚገባው ጠቁሟል፡፡

በእርግጥ መንግሥት በአሁኑ ወቅት ሰፊ የሆኑ የመንገድ ግንባታዎችን መጀመሩን፣ ይህም ወደ ፊት የትራንስፖርት ፍሰቱን ችግር በይበልጥ ሊፈታ እንደሚችልና ለብዙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችም መፍትሔ እንደሚያቃልል ተናግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራፊክ ማኔጅመት ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ኩማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኤጀንሲው በዋናነት የመንገድ ደኅንነት ፍሰትና ፍሰቱን ማረጋገጥ ላይ እየሠራ ሲሆን፣ በዚህ ውስጥ አምስት ተግባሮችን እያከናወነ ይገኛል፡፡፡

የትራፊክ ፖሊሶችና የመንገድ ተቆጣጣሪዎች በጋራ በመሆን በቅንጅት እንደሚሠሩ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰትና ቤቶች ሲዘጉ የመንገድ አጠቃቀም መጨናነቅ እንደነበር፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ትምህርት ቤቶቹ በመከፈታቸው ትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ ችግር እንዳይከሰት በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉን አብራርተዋል፡፡

እነዚህም በጎ ፈቃደኞች በዋናነት የሚሠሩት የትራፊክ ሕጉን ማስከበር ላይ ነው የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ በዘለለ ሕጉን ሲጥሱ የተገኙ አሽከርካሪዎችን የመቅጣት መብት እንደሌላቸው አቶ ብርሃኑ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር መደበኛ የትራፊክ ፖሊሲዎችና በኤጀንሲ ሥር ተቀጥረው የሚሠሩ አረንጓዴ ለባሽ ሠራተኞች መካከል በሚፈጠረው ጊዜ የትራንስፖርት ፍሰቱ ይጨናነቃል የሚለውን ጥያቄ ለዳይሬክተሩ አቅርቧል፡፡ ዳይሬክተሩም እንደዚህ ሲሉ ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በከተማዋ እየታየ ያለውን የትራንስፖርት መጨናነቅ ለመቀነስ መደበኛ የትራፊክ ፖሊሶችም ሆኑ በኤጀንሲው ሥር ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች በጋራ እንደሚሠሩ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ አለመግባባት ቢፈጠር እንኳን አፋጣኝ የሆነ ምላሽ ይሰጣል፡፡

አብዛኛውን ጊዜም የትራንስፖርት ፍሰቱ ላይ መጨናነቅ የሚታየው መሀል ከተማ እንደሆነ ይኼም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት በየቦታው የሚሠሩ የመንገድ ማሳለጫዎች በጊዜያቸው አለመጠናቀቃቸው መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን ትራንስፖርት ፍሰት ችግር ለመቅረፍ ኤጀንሲው የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ወጣቶች የትራንስፖርት ፍሰት የበዛባቸው ቦታዎች ላይ የሚሠሩ መሆናቸውን፣ በተለይም ደግሞ የሥራ መውጫና መግቢያ ሰዓት ላይ በዘርፉ ላይ የሚታየውን መጨናነቅ ለመቀነስ እየሠሩ እንደሆነ አክለዋል፡፡

በከተማዋ መውጫና መግቢያ በሆኑ በሮች አካባቢ የትራንስፖርት ፍሰት የሚበዛባቸው መሆኑን፣ በእነዚህም ቦታዎች ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ጠዋት 4፡00 ሰዓት እንዲሁም ደግሞ ከ10፡00 ሰዓት ጀምሮ መኪና ማቆም ክልክል እንደሆነና ይህንንም ሲተላለፍ የተገኘ አሽከርካሪ ቅጣት እንደሚጣልበት አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በከተማዋም የሚገኙ አሽከርካሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ሕግ የሚተላለፉ እንደሆኑ ገልጸው፣ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ኤጀንሲው በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሠራቱን አክለዋል፡፡

የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ ሲባል ከ600 በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ወደ ሥራ መግባታቸውን፣ እነዚህም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች ትራንስፖርት ፍሰት የበዛባቸው ቦታዎች ላይ ተሰማርተው እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በኤጀንሲው ሥርም ከ900 በላይ የሚሆኑ መደበኛ ትራፊክ ፖሊሶች እንደሚገኙ ያስታወሱት አቶ ብርሃኑ፣ በዘርፉም የትራንስፖርት ሥምሪትን የሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. ጥቅምት ወር ላይ ከፍተኛ የሆነ የትራፊክ መጨናነቅ እንደነበር፣ ይህንንም ለመታደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገርና ኮሜቲ በማዋቀር ችግሩን መፍታት እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርት ፍሰቱን በተመለከተ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር እየተሠራ መሆኑን፣ በይበልጥም ይህ ችግር የሚታየው መሃል ከተማ የሚባሉ ቦታዎች ላይ እንደሆነ ለሪፖርተር ጠቁመዋል፡፡     

የትራፊክ ፖሊስ፣ የመንገዶች ሥምሪትና ሌሎች የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሠሩት ሥራ የተለያየ ሲሆን፣ በዘርፉ ላይ በሚፈጠሩ ችግሮች ላይ እርስ በርስ በመተጋገዝና ለችግሩ በፍጥነት መፍትሔ በመስጠት እየሠሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ አሽከርካሪዎች ሕግ ሲጥሱና ያላግባብ ትርፍ ጭነው ሲጓዙ ማየት የተለመደ መሆኑን፣ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ለአውቶብስ ብቻ የተፈቀደ መንገድ እንዳለ፣ በእነዚህ መንገዶች ላይ በርካታ አሽከርካሪዎች እንደሚጓዙና በዘርፉም የተሰማሩ ባለሙያዎች ክትትል አድርገው አስፈላጊውን ቅጣት እንደሚቀጧቸው የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አረጋዊ ማሩ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

መኪና አቁመው ለብዙ ሰዓት የሚቆዩ ተሽከርካሪዎች ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ቅጣት እንደሚጣልባቸው ለዚህም 300 የሚሆኑ ሠራተኞች በተለያዩ ቦታዎች መመደባቸውን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ከ500 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችም በትራንስፖርት ሥምሪት ላይ ታፔላ ሳይለጥፉ እንዲሁም ደግሞ ከተፈቀደላቸው መስመር ውጪ ጭነው ሲንቀሳቀሱ የሚገኙ አሽከርካሪዎችን የሚቆጣጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...