Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የድንጋይ ከሰል ለማምረት ፈቃድ ለወሰዱ ድርጅቶች አስቸኳይ የውጭ ምንዛሪ እንዲቀርብ ተወሰነ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በታኅሳስ ወር ባሳለፈው ውሳኔ የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ ለማምረት ፈቃድ ለወሰዱ ስምንት ድርጅቶች፣ አስቸኳይ የውጭ ምንዛሪ እንዲቀርብ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወሰነ።

በውሳኔው መሠረትም ብሔራዊ ባንክ የካቲት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደብዳቤ መጻፉን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

እንደ ምንጭቹ ገለጻ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የድንጋይ ከሰል የማምረት ፈቃድ ለተሰጣቸው ስምንት ድርጅቶች፣ የድንጋይ ከሰል ማጠቢያ ማሽን ግዥ የሚውል የውጭ ምንዛሪ ‹‹የቅድሚያ ቅድሚያ›› ሰጥቶ እንዲያስተናግዳቸው ታዟል።

በመሆኑም የድንጋይ ከሰል የማምረት ፈቃድ የተሰጣቸው ስምንት ድርጅቶች አስፈላጊውን የባንክ ፎርማሊቲ አሟልተው ሲመጡ፣ ‹‹የቅድሚያ ቅድሚያ›› እንዲሰጣቸው መታዘዙን ምንጮቹ ገልጸዋል። 

ለስምንቱ ድርጅቶች በአስቸኳይ እንዲቀርብ የተፈቀደው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ መጠንም 25.4 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል።

ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን፣ ኤልኔት ቴክኖሎጂና ኢስት አፍሪካ ማዕድን ኮርፖሬሽን፣ ሰን ማይኒንግ ኤንድ ትሬዲንግ ኩባንያ እያንዳንዳቸው 4.1 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ እንዲሰጣቸው፣ በብሔራዊ ባንክ ደብዳቤ ላይ እንደተጠቀሰ፣ ይህ መጠንም ለስምንቱ ኩባንያዎች በተናጠል ከተፈቀደው የውጭ ምንዛሪ ትልቁ እንደሆነ ምንጮች አስረድተዋል።

የድንጋይ ከሰል የማምረት ፈቃድ የወሰዱት ስምንቱ ኩባንያዎች አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ካፒቴል ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑን፣ በዓመት በአማካይ 4.2 ሚሊዮን ቶን የድንጋይ ከሰል የማምረት አቅም እንዳላቸው መዘገባችን ይታወሳል።

ስምንቱ ኩባንያዎች በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ ያመርታሉ ተብሎ ከሚጠበቀው የድንጋይ ከሰል ምርት 98 ቢሊዮን ብር የሽያጭ ገቢ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

መንግሥት በእያንዳንዱ የድንጋይ ከሰል ፕሮጀክት ውስጥ የአምስት በመቶ ነፃ ድርሻ የያዘ ሲሆንፕሮጀክቶቹ የሚከናወኑባቸው ክልሎች ደግሞ ሁለት በመቶ የነፃ ድርሻ ይኖራቸዋል።

የድንጋይ ከሰልን ለኃይል ምንጭነት ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎች በተለይም የሲምንቶ ፋብሪካዎች ያለባቸውን የድንጋይ ከሰል አቅርቦት ችግር ለመፍታት፣ መንግሥት በየዓመቱ 270 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የድንጋይ ከሰል ከውጭ ሲያስገባ መቆየቱ ይታወቃል።

የድንጋይ ከሰል በአገር ውስጥ እንዲያመርቱ ፈቃድ የተሰጣቸው ስምንት ድርጅቶች፣ ከውጭ የሚገባውን ምርት በአገር ውስጥ የመተካት ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል።

በዚህም ምክንያት መንግሥት የድንጋይ ከሰልን ከውጭ እንዳይገባ ክልከላ መጣሉን፣ ከማዕድን ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኩባንያዎቹ በአንድ ዓመት ውስጥ፣ የአገር ውስጥ የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በማምረት እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ ‹‹የእነዚህ ፋብሪካዎች ግንባታ አገራችንን በየዓመቱ የምታወጣውን የመቶ ሚሊዮን ዶላሮች ወጪ የሚያድን ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት የሆነውን የድንጋይ ከሰል ፍላጎትን በሟሟላት የሲሚንቶ ምርትን የሚያሳድግ ይሆናል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች