ላለፉት 50 ዓመታት ሳይሻሻል ‹‹የሚዛንና መስፈሪያ ደንብ›› ተብሎ ሲተገበር የቆየው የሥነ ልክ አሠራር፣ በአዋጅ ደረጃ ተሻሽሎ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡ ሕጋዊ ሥነ ልክ በአስገዳጅነት ተግባራዊ የሚደረግ የሕግ ማዕቀፍ ሲሆን፣ ይህም ከሌሎች የሥነ ልክ ዓይነቶች በተለየ ከመለኪያ መሣሪያዎች ጋር የሚያያዝ ስለሆነ ነው፡፡
ሳይንሳዊ፣ ኢንዱስትሪያዊና ሕጋዊ የሚባሉ የሥነ ልክ ዓይነቶች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን፣ ሕጋዊ የሚባለው የሥነ ልክ ዓይነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ እንደ ንግድ ባሉት መስኮች ተግባራዊ ሲደረግ የቆየ የልኬት ዓይነት ነው፡፡
በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጥራት መሠረተ ልማትና ማረጋገጫ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንዳለው መኮንን ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በሕግ ሥርዓት ውስጥ የሚታዩት የሚዛን ማጭበርበር ተግባራት፣ ምርት ላይ ያልተገባ ነገር መለጠፍ፣ ከምርት መጠን በታች በማቅረብ ሸማቹን የማጭብርበር ባህሪዎች ቁጥጥር ካልተደረገባቸው አምራቹ ሸማቹን እንደፈለገው እንዲጠቀምበት የሚያደርገው ይሆናል፡፡
ከዚህ ቀደም የሚዛንና መስፈሪያ ደንብ ቁጥር 431/1965 በኢትዮጵያ ደረጃ ባለሥልጣን አስፈጻሚነት ተግባራዊ እነደሚደረግ ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህ ደንብ ላለፉት 50 ዓመታት ሳይሻሻል ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዚህ ወቅት ደንቡን ለማሻሻል አስገዳጅ ሁኔታዎች አሉ ያሉት አቶ እንዳለው፣ ምክንያቱም ከቴክኖሎጂ ዕድገቶች ጋር ተያይዞ የዓለም አቀፍ ሁኔታ የተቀየረ መልክ ይዟል፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ሚዛንና መስፈሪያን የተመለከተው ደንብ ባለመቀየሩ ኅብረተሰቡ ሲበዘበዝ እንዲቆይ አድርጎታል ያሉት አቶ እንዳለው፣ ይህ ደንብ በአዋጅ ደረጃ ሆኖ የቅጣት ሕጎችን አካትቶ ረቂቁ እንደተዘጋጀ አስረድተዋል፡፡
የሥነ ልክ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ግብዓቶችን መሰብሰብ አስፈላጊ ስለሆነ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ እንዳካሄደ ያስታወቁት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ይህም የተጠናቀቀውን ረቂቅ አዋጅ በፍጥነት ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ከማሰብ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በቅድመ እሸጋ ወቅት አምራቹ ሸማች በሌለበት ወቅት ምርቶችን ስለሚያሽግ፣ ሸማቹ ምርቱ በትክክለኛው ልኬት መታሸጉን የሚረዳው በተቀመጠለት አኃዝ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በመክተት መንግሥት በተለይ የቅድመ እሸጋ ምርቶች ቁጥጥር ላይ ከፍተኛ ሥራዎችን ለመሥራት እንዳሰበ ተገልጿል፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ ቡድን ተቋቁሞ በየግብይት ማዕከላት ታሽገው ለሸማቹ የቀረቡ ምርቶችን በተቀመጠው ደረጃ መሠረት ይቆጣጠራል፡፡
ልኬቶች ላይ በትክክል ቁጥጥር የማይደረግ ከሆነ በተለይም አምራቹ በሚፈጥራቸው የልኬትና የመጠን ግድፈቶች ሸማቾች ይበዘበዛሉ ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ለምሳሌ ሲሚንቶ 50 ኪሎ ግራም ተብሎ ለገበያ ቢቀርብም በትክክል የምርቱ መጠን ምን ያህል እንደሆነ ልኬቱን የሚቆጣጠረው አካል ማረጋገጥ አለበት፡፡
የአዋጁ መውጣት በትክክል ኅብረተሰቡ ወይም ሸማቹ ለከፈለው ዋጋ ማግኘት ያለበትን የምርት መጠን እንዲያገኝ ያስችለዋል የተባለ ሲሆን፣ ገበያው ላይ የሚታየውን ጉድለትም የሚሸፍን ይሆናል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የጤናው ዘርፍ ላይ ለአብነትም አንድ የመለኪያ መሣሪያ በትክክል ስለመለካቱ መረጋገጥ ይገባዋል ያሉት አቶ እንዳለው፣ ይህም የሚረጋገጠው በሕጋዊ የሥነ ልክ አሠራር ነው ብለዋል፡፡
አቶ እንዳለው እንዳሉት፣ የደም ግፊትን የሚለካ መሣሪያ ሁልጊዜም ትክክለኛነቱ መረጋገጥ አለበት፡፡ ምክንያቱም መለኪያው በብልሽትና በተለያዩ ጉዳዮቸ ሊሠራ የሚገባውን ተግባር በትክክል ካላመላከቱ ልኬቱን ተከትሎ የሚወሰነው ውሳኔ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ ላይ አደጋ ሊፈጠር ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ወደ ውጭ አገሮች የሚላኩ የኢትዮጵያ ምርቶች መጠናቸው በርካታ ሲሆን፣ ከልኬት መጠን ጋር ተያይዞ በትክክለኛው መጠን ካልቀረቡ ከተፈለገው ምርት በላይ ቢላክ የአገር ጥቅም ያሳጣል፣ ከመጠን በታች ከሆነ ደግሞ የአገርን ገጽታ የሚያበላሽ ይሆናል፡፡
የሕግ ማዕቀፉን በፓርላማ ከማፅደቅ ባሻገር ዘርፉ በብቃት ባለሙያዎች እንዲመራ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ተግባዕረ ዕድ የፖሊቴክኒክ ኮሌጅና ከብሔራዊ የሥነ ልክ ኢንስቲትዩት የሦስትዮሽ ስምምነት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡