Sunday, March 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የቁርሾ ፖለቲካ ይወገድ!

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች ሹመት ከፀደቀ በኋላ የተደበላለቁ ስሜቶችን የሚወክሉ ድምፆች እየተሰሙ ነው፡፡ ስሜቶቹ የሚወክሉዋቸው ድምፆች የየራሳቸው ታሪካዊ ዳራ ሲኖራቸው፣ ሀቀኝነትና ቅንነትን የተላበሱ ያሉትን ያህል የቀድሞ ቁርሾዎችን የሚቀሰቅሱ መሰሪነቶችም አሉበት፡፡ የተለያዩ ጎራዎችን የሚወክሉ ፍላጎቶችን በግልጽ በማውጣት ሕዝባዊ ምክክር የማድረግ አስፈላጊነት፣ ኃላፊነት በጎደላቸው ፖለቲከኞችና ከራሳቸው በላይ ምንም ነገር በማይታያቸው ግለሰቦችና ስብስቦች ሲደነቃቀፍ ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶቹ ብሔራዊ ምክክሩን ከድርድር ጋር አያይዘው ውዝግብ ይፈጥራሉ፣ ሌሎች ደግሞ የሽምግልና መድረክ በማስመሰል ያደነጋግራሉ፡፡ በዚህ ሕዝባዊ የምክክር መድረክ የኢትዮጵያን የዘመናት ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በግልጽ ውይይት መልክ እንዲይዙ በማድረግ ዘለቄታዊ ሰላም ማስፈን እየተቻለ፣ ከወዲሁ ተቀምጦ በሰላም ለመነጋገር የማያስችሉ ሰበቦችን መደርደርና የተለመደውን የሴራ ፖለቲካ መጎንጎን መጀመሩ አሳዛኝ ነው፡፡ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችን ጥቆማ ከመስጠት ጀምሮ የዕጩዎች መረጣና በመጨረሻም በፓርላማ እስከ ማፀደቅ ድረስ የተኬደበት ሒደት በተቃውሞ ውስጥ ማለፉ፣ አሁንም በመንግሥትና የአገር ጉዳይ ያገባናል በሚሉ ተቀናቃኞች መካከል ያለውን ቁርሾ የሚያሳይ ነው፡፡ ቁርሾን አስወግዶ በመግባባት ላይ የተመሠረተ ምክክር አለማድረግ የሚጎዳው ግን አገርን ነው፡፡

የአገራዊ ምክክሩ ዋነኛ ዓላማ መሆን ያለበት ኢትዮጵያውያን የዘመናት ችግሮቻቸውን ለመቅረፍ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት በማግኘት፣ በዘርፈ ብዙ ጉዳዮቻቸው ላይ በነፃነት መነጋገር እንዲችሉ መደላድሉን ማመቻቸት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ተቆጥረው የማያልቁ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ተያያዥ ምክክር የሚያስፈልጋቸው ችግሮች አሉ፡፡ ገዥው ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች፣ ይህ የሕዝብ ምክክር በተቀላጠፈ መንገድ ይከናወን ዘንድ እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ መሰናክሎች እንዳይኖሩ ማገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ነገር ግን ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ ሌሎቹም ከጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ የዘለለ ራዕይ የሌላቸው ይመስል፣ ለጭቅጭቅና ለውዝግብ በር የሚከፍቱ ድርጊቶች ላይ መሰማራታቸው አስተዛዛቢ ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ በኩል ያሉ ኃላፊነት ያለባቸው ግለሰቦች ሳይቀሩ ምክረ ሐሳብ ለመቀበል ፍላጎት ሲያጡ ተስተውሏል፡፡ በተቀናቃኞችም በኩል ያሉ እንዲሁ ለሰበብ የሚያመቹ ማፈግፈጎችን ሲመርጡ ታይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከፌዝና ከአሉባልታ ውጪ ቁምነገር የራቃቸውም አሉ፡፡ ለአገራዊ ምክክሩ ሒደት የማይበጁ ቁርሾዎች ሲበዙ፣ ዘለቄታዊ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት አዳጋች እንደሚሆን መረዳት አያቅትም፡፡

በፓርላማው ሹመታቸው የፀደቀላቸው ኮሚሽነሮች ገለልተኝነትና ችሎታ ላይ የሚነሳው ቅሬታ፣ ገና ከወዲሁ ለአገራዊ ምክክሩ የሚደረገውን ዝግጅት እንዳያደናቅፈው ያሠጋል፡፡ አንዳንዶች ብሔርን፣ እምነትን፣ የፖለቲካ ወገንተኝነትን፣ ከዚህም አልፎ ተርፎ ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ የፖለቲካ ልሂቃንን ደም ያቃባ ደመኝነትንና ሌሎች ልዩነቶችን በመደርደር የኮሚሽነሮችን ቅቡልነት ይገዳደራሉ፡፡ ከ110 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለማወያየት የሚያግዙ ኮሚሽነሮችን ለመምረጥ አስቸጋሪና ውስብስብ ችግሮች ማጋጠማቸው አይቀሬ ቢሆንም፣ የመጨረሻዎቹን ዕጩዎች ከማፀደቅ በፊት አንድ መድረክ በማዘጋጀት ለቅሬታ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን በማስቀረት ሌሎች ማግኘት ቢቻል መልካም ነበር፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት ብሔራዊ ምክክር ለማድረግ የሚያስችል ሙከራ ያደረጉ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ ትኩረት ቢደረግም ጠቃሚ ነበር፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ አሁንም ቢሆን በኮሚሽነርነት የተመደቡት ኢትዮጵያውያን ኃላፊነቱን ተረክበው ሥራ እንዲጀምሩ ዕገዛ ቢደረግ፣ እነሱም ከአጠቃላዩ ፍላጎት በመነሳት ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በትጋት ቢሠሩ ተፈላጊው ወጤት ሊገኝ ይችላል፡፡ ዋናው ጉዳይ ኢትዮጵያ ለዘመናት ከምትዳክርበት የቁርሾ ፖለቲካ እንድትላቀቅ ስለሆነ፣ የአገራቸው ጉዳይ የሚመለከታቸው ወገኖች ቢያስቡበት ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም፡፡

እርግጥ ነው ብልሹው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አንድ የፈጠረው ችግር ቢኖር አለመተማመን ነው፡፡ ይህ አለመተማመን ከ1960ዎቹ ትውልድ ጀምሮ እዚህ ዘመን ድረስ በመዝለቁ፣ ቀደም ሲል በቀይና በነጭ ሽብር ጎራዎች ውስጥ ሆነው የተፋጁት ኢትዮጵያውያን ዛሬም በደመኝነት ይፈላለጋሉ፡፡ በሆነ አጋጣሚ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያገናኛቸው መድረክ ሲፈጠር፣ ተቀራርቦ ለመነጋገር ከመፈላለግ ይልቅ የቀድሞው እልኸኝነታቸውና ግትርነታቸው እየቀደመ ጠባቸው ያገረሻል፡፡ የእነሱ አልበቃ ብሎ ይህንን አስቸጋሪ ፀባይ ወደ አዲሱ ትውልድ እንደ ቫይረስ ያስተላልፋሉ፡፡ አለመተማመኑ በዚህ ብቻ አያበቃም፡፡ በገዥው ፓርቲና በተፎካካሪ ፓርቲዎችም መካከል ሥር የሰደደ ነው፡፡ ለብዙዎቹ ተፎካካሪዎች ብልፅግና የኢሕአዴግ ወራሽ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ብልፅግና የሚፈረጀው ሥልጣኑ ተጠናክሮ መቀጠል ሲል ማንኛውንም ዓይነት ኃጢያት ከማድረግ እንደማይቆጠብ ነው፡፡ አገራዊ ምክክሩን ለዚህ ፍላጎቱ ማሳኪያ ለማድረግ ሲልም፣ ከቁጥጥሩ ውጪ እንዳይወጣ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ አይመለስም ይሉታል፡፡ በተፎካካሪው ወገን ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማበብ ከሚሠሩት በተጨማሪ፣ ብሔርንና እምነትን እያጣቀሱ ፋይዳ ቢስ ድርጊቶች ውስጥ የተሰማሩም አሉ፡፡ ይህ ሁሉ ቁርሾ በበዛበት ሁኔታ ውስጥ ነው የአገራዊ ምክክሩ ዕጣ ፈንታ ሥጋት ያጠላበት፡፡

አገራዊ ምክክሩ ሁሉን አሳታፊ መሆን እንዳለበት በተደጋጋሚ ተነግሯል፡፡ ነገር ግን የአደባባይ ሰዎችን የማያበረታታው የፖለቲካ ባህል እንቅፋት እንዳይሆን ያሳስባል፡፡ በአገራዊ ምክክሩ ሁሉም አገራዊ ችግሮች ተነስተው ውይይት ሊደረግ ይገባቸዋል እየተባለ፣ ሰዎች አስተያየቶቻቸው እንዲገደቡ የመፈለግ አዝማሚያዎች ከተወሰኑ ወገኖች በኩል ይታያሉ፡፡ ለፌዴራል ሥርዓቱ አዎንታዊ አመለካከት ያላቸው እንዳሉ ሁሉ፣ ከዚህ አመለካከት በተቃራኒ የተሠለፉም አሉ፡፡ ሁለቱም ወገኖች መገንዘብ ያለባቸው በእውነተኛ ፌዴራሊዝም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባት እንደሚቻል ነው፡፡ ፌዴራሊዝምን ለአገር አንድነትና ለእኩልነት መጠቀም እንደሚቻል ተቀምጦ አለመነጋገር አለመቻል፣ ትልቅ ጉዳት እንደሚያስከትል ሊሰመርበት ይገባል፡፡ አገራዊ ምክክሩ የሕዝብ ተሳትፎ እንዲጎላበት ከተፈለገ፣ ከሰማይ በታች ያለው የአገሪቱ ችግር በሙሉ መደመጥ ይኖርበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ልፋቱ ሁሉ ለኢትዮጵያ ህልውና እስከሆነ ድረስ ትዕግሥት፣ አርቆ አሳቢነት፣ ቅንነት፣ ትሁትነትና ሆደ ሰፊነት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ሊከበር የሚችለው፣ ከራስና ከቡድን ፍላጎት በላይ ለጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ትኩረት ሲሰጥ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ከራሳቸው ፍላጎት በታች ለማድረግ የሚሹ ካሉ ከታሪክ ቢማሩ ይጠቅማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንም ከቁርሾ ፖለቲካ ርቀው ለአገራቸው ሲሉ ቢተባበሩ ይመረጣል፡፡

ኢትዮጵያ ለዝንተ ዓለም የጥልና የግጭት ዓውድማ የሆነችው ብዙኃኑ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ጉዳይ ባይተዋር በመሆናቸው ነው፡፡ በፊውዳሉ ዘመን በገዛ አገሩ ገባር የነበረው ሕዝብ፣ የመደመጥ ዕድሉ እጅግ በጣም የተመናመነ ነበር፡፡ ግፋ  ቢል ‹‹እረኛ ምን አለ?›› ከሚል መረጃ ፍለጋ ውጪ ውስጡ ምን እንደሚብላላ ለማወቅ ፍላጎት አልነበረም፡፡ በዘመነ ደርግ ደግሞ ምንም እንኳ በስመ ሶሻሊዝም በወዝ አደሩና በአርሶ አደሩ ስም ብዙ ቢባልም፣ ጎልቶ የወጣው ግን የቀይ ሽብርና የነጭ ሽብር ተዋናይ ልሂቃን መተራረድ ነበር፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ያለፉ የዘመኑ ወጣቶችም የገጠማቸው ዕልቂት፣ እስራትና መሰደድ እንደነበር አይካድም፡፡ በዚህ መሀል ግን ሰፊው ሕዝብ የመከራ ገፈት ቀማሽ ሆነ እንጂ፣ በቁምነገር ያዳመጠው ማንም አልነበረም፡፡ የተተካው ኢሕአዴግ ደግሞ ምን ሲሠራ 27 ዓመታት እንደነጎዱ ለዚህ ትውልድ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ጎስቁሎና መንምኖ ብሔርተኝነት የገነገነበት ይህ ዘመን፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተናቀበትና ጥቂቶች እንዳሻቸው ሲጨፍሩበት የነበረ መርገምት ነበር፡፡ ከዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ውጥንቅጥ ውስጥ በመውጣት አገራዊ ምክክሩ እንዲሳካ የቁርሾ ፖለቲካ ይወገድ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ተቀማጭ ያለው ሦስተኛው ከግል ባንክ ሆነ

የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ከ100 ቢሊዮን...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

ብሔራዊ ባንክ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን ይፋ ሊያደርግ ነው

የፋይናንስ ዘርፉን ለማረጋጋት የሚረዳ ሪፎርም ማጠናቀቁን የገለጸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ግልጽነትና ተጠያቂነት የጎደለው አሠራር ለአገር አይበጅም!

ሰሞኑን የአሜሪካና የኢትዮጵያ መንግሥታት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተፈጽመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና የጦር ወንጀሎች መግለጫ ላይ አልተግባቡም፡፡ አለመግባባታቸው የሚጠበቅ በመሆኑ ሊደንቅ አይገባም፡፡ ነገር ግን...

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...