በግንባታ ዋጋ ጭማሪ ሳቢያ ፕሮጀክቶች ተቋርጠዋል
በግንባታ ዘርፍ ችግሮች ላይ የሚያተኩርና ለአንድ ወር የሚቆይ የምክክር መድረክ ከዛሬ የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በድሬዳዋ ከተማ ማካሄድ መጀመሩን፣ የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን አስታወቀ።
የምክክር መድረኩ ከዛሬ እሑድ የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መጋቢት 21 2014 ዓ.ም. የሚካሄድ መሆኑን፣ በግንባታ ዘርፍ ውስጥ በሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች ላይ ትኩረቱን እንደሚያደርግ የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ማተቤ አዲስ ገልጸዋል።
የምክክር መድረኩ በአራት ከተሞች የሚከናወን እንደሆነና በድሬዳዋ ከተማ ተጀምሮ በአዳማ፣ በሐዋሳና በደሴ ከተሞች በተከታታይ ይካሄዳል ብለዋል። ‹‹ግንባታ ለአገር አለኝታ›› በሚል መሪ ቃል የሚደረገው ይህ መድረክ የግንባታ ጥራት፣ የመጠናቀቂያ ጊዜ፣ የግዥ ሒደት፣ በጀትና ተያያዥ ጉዳዮች የሚዳሰሱበት እንደሆነ ባለሥልጣኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገልጿል።
በግንባታ ዘርፍ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል የግዥ ሒደቱ አንደኛው መሆኑን የጠቀሱት አቶ ማተቤ፣ ይህም በተለይ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ መጓተት እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል። የግዥ ሥርዓቱን ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት እንዲሆን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ያደረገውን ጥናት መሠረት በማድረግ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ምክክር ያደርጉበታል ብለዋል።
ከ1,500 በላይ ባለድርሻ አካላት ምክክር እንደሚያደርጉበት፣ በተለይ በመንግሥት ፕሮጀክቶች ላይ እያጋጠሙ ያሉ መጓተቶች በሚፈቱባቸው መንገዶች ላይ የክልሎችና የፌዴራል ተቋማት መግባባት ላይ እንደሚደርሱም ተገምቷል። በተለይ የዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ግንባታዎች፣ በግንባታ ዋጋ መጨመር ምክንያት መቋረጣቸውን ያወሱት አቶ ማተቤ፣ መቀጠል የሚችሉትን በመለየት እንዲቀጥሉ ለማድረግና አቅም የማይኖራቸውን ውላቸው እንዲቋረጥ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
ከ40 በላይ በሚሆኑ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ ከ700 በላይ ፕሮጀክቶች እንደሚገኙ፣ ግንባታቸው የተቋረጠባቸው ምክንያቶች ተለይተው ወደ ሥራ ለመመለስ በጥናት ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በኮንስትራክሽን ዘርፉ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የሚያጋጥሙ የአተገባበር ክፍተቶች ዋነኛ ችግር መሆናቸውን፣ በተለይ ጥራታቸውን የጠበቁና ለአካባቢ ተስማሚ ሆነው እንዲከናወኑ ለማስቻል ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር መግባባት ላይ እንደሚደረስ ይጠበቃል ብለዋል።
ለዚህም በግንባታ ባለቤቶች፣ አማካሪዎች፣ ሥራ ተቋራጮችና በመንግሥት መካከል ያለውን አለመግባባት በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንደሚታይ አክለዋል።
የግንባታ ቦታ ደኅንነትን በተመለከተ አሁን ያለው ሕግ በአግባቡ እየተተገበረ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ማተቤ፣ ባለሥልጣኑ እንደ አዲስ የሕግ ማዕቀፉን ለማዘጋጀት በጥናት ላይ ይገኛል ብለዋል።