Wednesday, February 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት አንድም ሰው አለመሞቱን አስታወቀ

የሶማሌ ክልል በድርቅ ምክንያት አንድም ሰው አለመሞቱን አስታወቀ

ቀን:

በሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ የእንስሳት ሞት ቢያስከትልም፣ እስካሁን አንድም ሰው አለመሞቱን የክልሉ መንግሥት አስታወቀ፡፡ በክልሉ ድርቁ ባስከተለው የውኃና የእንስሳት መኖ እጥረት የሞቱ እንስሳት ቁጥር ከ300 ሺሕ በላይ ቢገመትም፣ የሰዎች ሕይወት ግን እስካሁን አለመጥፋቱን የክልሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል፡፡

የክልሉ አደጋ መከላከል ቢሮ የሚመራው ከፍተኛ የክልሉ ቢሮ ኃላፊዎችን ያካተተ የልዑካን ቡድን ድርቁ በተከሰተባቸው ዞኖች የመስክ ክትትልና ምልከታ እያደረገ መሆኑን፣ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ኃላፊው አቶ አብዱልፈታ መሐመድ አክለውም ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የዕለት ደራሽ ዕርዳታ በድርቅ ለተጎዱ ዜጎች እያከፋፈሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የመስክ ምልከታና የዕርዳታ ሥርጭት ባደረጉባቸው አምስት ዞኖች የሞተ ሰው አለመኖሩንና በሌሎችም ቦታዎች በሰዎች ላይ የተከሰተ የሞት አደጋ ሪፖርት አለመደረጉን ምክትል ኃላፊው በተለይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹የሶማሌ ክልል መንግሥት የመደበውን፣ ከፌዴራልና ከሌሎች ክልሎች የተላከውን የዓይነት ዕርዳታ በአግባቡ መከፋፈሉን፣ በሁሉም ወረዳዎች በአካል ተገኝተን እየተከታተልን እንገኛለን፡፡ ዝናብ የሚዘንበው ከመጋቢት መጨረሻ በኋላ ነው ተብሎ ስለሚገመት የድርቁ ተፅዕኖ በክልሉ እንደሚሰፋ ይጠበቃል፡፡ አሁንም ቢሆን በድርቁ ለተጎዱ እንስሶችና ዜጎቻችን ተጨማሪ ዕርዳታ እንዲደረግ እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ ውጪ ባልተጨበጠ መረጃ ለራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ሲሉ፣ ድርቁ የሰው ሕይወት እያጠፋ ነው የሚሉ ወገኖች የተፈጥሮ ክስተት ከሆነው ድርቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የቋመጡ ናቸው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ አብዱልፈታ፣ ጉዳዩ የሰብዓዊነት አጀንዳ እንጂ ከዚህ የሚገኝ ትርፍ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡

ድርቁ በክልሉ ካሉ 11 ወራዳዎች በዘጠኙ የተከሰተ ሲሆን፣ ከ93 ወረዳዎች 78ቱን ማዳረሱንም የክልሉ መንግሥት ይናገራል፡፡ ባለፈው ወር ባቀረበው የዕርዳታ ጥሪም የድርቁ አድማስ መስፋቱንና አደጋው ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም የተለያዩ የክልል መንግሥታትና ለጋሽ አካላት የከብቶች መኖና ሌሎች ዕርዳታዎችን ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

በሌላም በኩል የድርቁን አደጋ አስመልክቶ ከፌዴራል መንግሥቱ ተጨማሪ ድጋፍ እንዲቀርብ፣ ከሶማሌ ክልል የሕዝብ እንደራሴዎች ተወካይ በአቶ ፋራህ መሐመድ ባለፈው ሳምንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥያቄ ቀርቦ ነበር፡፡

በድርቅ ለተጠቁ የሶማሌ ክልልና የቦረና አካባቢዎች ወደ 750 ሺሕ ኩንታል የምግብ ዕርዳታና 259 ውኃ ማመላለሻ ቦቴ ተሽከርካሪዎች መከፋፈሉን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)፣ ድርቁን ለመቋቋም በተደረገው ርብርብ የሰዎችን ሕይወት ከሞት አደጋ ለመታደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡

በሌላም በኩል ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ለክልል ምክር ቤት አባላት የመንግሥታቸውን የግማሽ በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ያቀረቡት የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር፣ ክልላቸው ለድርቁ ቅድሚያ በመስጠት ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት እንዲመደብ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከ305 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ዕርዳታ ከሌሎች ክልሎችና ለጋሽ አካላት መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በ87 ወረዳዎች በ1,873 ቦታዎች ውኃ በቦቴ የማቅረብ ሥራ እየሠራን ነው፤›› ያሉት አቶ ሙስጠፋ፣ ድርቁ ከእንስሳት አልፎ በሰዎች ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል ሰፊ የዕርዳታ ማከፋፈል ሥራ መንግሥታቸው እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በሶማሌ ክልል የደረሰውን ከባድ ድርቅ ተከትሎ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ዓምደኞች፣ ድርቁ የሰዎችን ሕይወት እየነጠቀ ነው የሚል ዘገባ በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ፡፡ ይህንኑ በመጥቀስ ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ የቀረበላቸው የአደጋ መከላከል ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱልፈታ፣ ‹‹የቅጥፈት ፕሮፖጋንዳ ነው›› በማለት ነበር ያስተባበሉት፡፡ አቶ አብዱልፈታ የድርቁን አደጋ ለመቋቋም መንግሥትም ሆነ ለጋሽ አካላት ርብርብ እያደረጉ መሆኑን፣ ከአደጋው ስፋት አንፃር ግን ክልሉ ተጨማሪ ዕርዳታ ይፈልጋል ብለዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የካቲት አብዮት – ጥያቄዎችሽ ዛሬም እየወዘወዙን ነው!

በበቀለ ሹሜ አጭር መግቢያ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከ1960ዎች ወጣቶች ርዝራዦች አንዱ...

የሰሞኑ የ“መኖሪያ ቤቶች” የጨረታ ሽያጭ ምን ዓይነት ሕጋዊ መሠረት አለው?   

በዳዊት ዮሐንስ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አየር ላይ ከሚንሸረሸሩ ዜናዎች...

ሁለቱ ወጎች፡ ከሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! እስከ በዓሉ ቤርሙዳ

በተክለ ጻድቅ በላቸው ሰማየ ሰማያት አድርሶ መላሹ ቋንቋ! ከሁለት ሦስት ዓመት...

ለትግራይ ክልል ድርቅ ተፈናቃዮች አፋጣኝና ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንዲደረግ ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዩች ቋሚ...