Tuesday, November 28, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዕድን ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን የ41.3 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ደረሰበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማዕድን ማውጣት ፈቃዶቹ የተሰረዘበት የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን በስድስት ወር አፈጻጸሙ የዕቅዱን 25 በመቶ ብቻ ከማሳካቱ ባሻገር፣ 41.3 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደደረሰበት አስታወቀ፡፡ ኮርፖሬሽኑ በግማሽ የበጀት ዓመቱ 52.7 ሚሊዮን ገቢ ለማግኘት አቅዶ ማሳከት የቻለው 13 ሚሊዮን ብር ያህሉን ነው፡፡

ተጠሪነቱ ለቀድሞው ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሆኖ በ2012 ዓ.ም. በድጋሚ የተቋቋመው ኮርፖሬሽኑ፣ በማዕድን፣ በነዳጅና በባዮፊዩል ሥራዎች ላይ በቀጥታ በመሳተፍ እነዚህን የተፈጥሮ ሀብቶች ለማልማት የተቋቋመ ቢሆንም፣ አሁን ግን የወርቅና የታንታለም ፈቃዱን ሚኒስቴሩ ሰርዞበታል፡፡ በነዳጅና በባዮፊዩል ዘርፎችም ያከናወናቸው ሥራዎች ባለመኖራቸው ዕቅዱን ማሳካት ሳይችል ኪሳራ አጋጥሞታል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ደርሚዳማ ወረዳ ቀንጢቻ አካባቢ የነበረው የታንታለም የምርት ፈቃድና በሥሩ ያለው የአዶላ ወርቅ ልማት ድርጅት ፈቃድ ቢሰረዝበትም፣ በሁለቱ ቦታዎች ያሉ ሠራተኞቹን የደመወዝ ክፍያ እስካሁን እየፈጸመ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን መምርያ ተወካይ አቶ ባጫ ፋጂ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቀንጢቻ አካባቢ በነበረው በታንታለም ምርት ተሰማርተው የነበሩት ሠራተኞች በሥራ ላይ ባይሆኑም ደመወዝ እየተከፈላቸው ያለው ኮርፖሬሽኑ ፈቃዱ ከተሰረዘ በኋላ በቀንጢቻ ያሉት ማሽኖች፣ የተለያዩ መገልገያዎችና የሰው ኃይል ቀጣይ ዕጣ ፋንታ በተመለከተ ውሳኔ ላይ ባለመደረሱ ነው ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ የኮርፖሬሽኑ አመራሮች ከማዕድን ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታ፣ አስተዳደርና አሁን የቀንጢቻን ፈቃድ ከያዘው የኦሮሚያ ማይኒንግ አክሲዮን ማኅበር ጋር ንግግር እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በቀንጢቻ ያለው የቁሳቁስና የሰው ሀብት ዋጋው እየተጠና መሆኑንና ግምታቸው ሲጠናቀቅ፣ ወደ ኦሮሚያ ማይኒንግ አክሲዮን ማኅበር ይዛወራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

በአዶላ የነበሩት ሠራተኞች ደግሞ የተወሰኑት ወደ ኮርፖሬሽኑ የካዎሊን ፋብሪካ ሲዘዋወሩ፣ ቀሪዎቹ ወደ ዋና መሥሪያ ቤቱ መምጣታቸው ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በሥራ ላይ ያልሆኑና ያረጁ ማሽነሪዎች መኖራቸውም፣ ኮርፖሬሽኑ ለኪሳራ የተጋለጠበት አንድ ምክንያት ሆነው ተጠቅሰዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ለሦስት ዓመታት ቆሞ የነበረውን ለመጠጥ ውኃ ማጣሪያ የሚውል የካዎሊን ማዕድን የሚያመርት ፋብሪካውን ሥራ ማስጀመሩ ተገልጿል፡፡ ፋብሪካው ከዚህ ቀደም ለውኃ ማጣሪያ ብቻ ሲመረት የነበረውን ካዎሊን ለወረቀት፣ ለቀለም፣ ለጎማና ለሴራሚክ ምርቶች ግብዓትነት የማምረት ዕቅድ አለው፡፡ ይሁንና በፋብሪካው ውስጥ ያሉት ማሽኖች በማርጀታቸው ሳቢያ፣ ካዎሊን የማምረት ሒደቱ መስተጓጎል እንደተፈጠረበትና ይኼም በግማሽ ዓመቱ ይዞ የነበረውን ዕቅድ እንዳያሳካ ማድረጉን አቶ ባጫ አስረድተዋል፡፡

ነዳጅን በተመለከተም በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በኩል ከፍለጋ እስከ ልማት ድረስ የሚሠሩ ተቋማት እየተደራጁ በመሆናቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በነዳጅ ላይ የሚኖረው ድርሻ ባለመወሰኑ በዘርፉ ላይ አልተሠራም፡፡ ኮርፖሬሽኑ የባዮፊዩል ምርትን በተመለከተ ከስኳር ፋብሪካዎች ጋር እሠራለሁ የሚል ዕቅድ የነበረው ቢሆንም፣ እንደታሰበው ባለመሄዱ ምንም አለመሠራቱ ተገልጿል፡፡

በ16.7 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን ያለበት የገንዘብ እጥረት ሌላው ፈተናው ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ 30 ዓመታት ያገለገሉ ማሽኖች እንዳሉት የሚናገሩት አቶ ባጫ፣ እነዚህ ማሽኖችን ለመጠገን የሚሆን መለዋወጫ ማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይሁንና ከፀጥታ ሥጋት ጋር በተያያዘ ምክንያት ኮርፖሬሽኑ ለሦስት ዓመታት ያህል ብዙ ሥራዎቹን ሲያቋርጥ የሚያገኘው ገቢ ስላልነበረ፣ ማሽኖቹን የማደስም ሆነ አዲስ የመግዛት አቅም የለውም፡፡

ኮርፖሬሽኑን በ2012 ዓ.ም. በድጋሚ ያቋቋመው አዋጅ እንደሚደነግገው 16.7 ቢሊዮን ብር ከሆነው አጠቃላይ ካፒታሉ ውስጥ 4.17 ቢሊዮን ብር በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ የተከፈለ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት የተከፈለው የማቋቋሚያ ካፒታል እንዲለቀቅ ከመንግሥት ጋር መግባባት ላይ መደረሱ ተገልጿል፡፡

ካለፈው ዓመት ወዲህ አዲስ አመራርና ቦርድ ያገኘው ኮርፖሬሽኑ ለ30 ዓመታት ገደማ ትኩረት ካደረገበት የታንታለም ምርት ውጪ ወደ ሌሎች አማራጮች ፊቱን እያዞረ መሆኑን አቶ ባጫ ተናግረዋል፡፡ ያለውን ቤተ ሙከራ በመጠቀም ለተለያዩ ድርጅቶች የማዕድን ናሙና ምርመራ ማድረግ፣ ማሽኖቹን ተጠቅሞ ለማዕድን አውጪዎች የቁፋሮ አገልግሎት መስጠት፣ ከውጭ የሚገቡ እንደ ዕምነበረድና ዶሎማይት ያሉ ማዕድናትን በአገር ውስጥ መተካት፣ እንዲሁም የከበሩ ድንጋዮችን አስውቦ በጌጣጌጥነት ማቅረብ ኮርፖሬሽኑ ገቢውን ለማስፋት ያቀደባቸው ዘርፎች ናቸው፡፡

ከዚህም ባሻገር በኦሮሚያ ክልል ተወስኖ የቆየውን ወርቅ የማውጣት ሥራ ወደ ሌሎች ክልሎችም ማዞር በአማራጭነት ተይዟል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች ወርቅ፣ በአማራ ክልል ሰቆጣ አካባቢ ደግሞ የብረት ማዕድን ለማውጣት ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ንግግር ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች