Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበጉጂ ዞን ቆላማ ወረዳዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማድረስ እንዳልተቻለ ዞኑ አስታወቀ

በጉጂ ዞን ቆላማ ወረዳዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ለማድረስ እንዳልተቻለ ዞኑ አስታወቀ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ቆላማ ወረዳዎች በፀጥታ ችግር ምክንያት ለዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ማድረስ እንዳልተቻለ፣ የዞኑ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡

በዞኑ ረሃብ ተከስቶባቸዋል ከተባሉ ዘጠኝ ወረዳዎች ውስጥ ስድስቱ ከፍተኛ የፀጥታ ችግር ስላለባቸው፣ ዜጎች 60 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ዕርዳታ እንደሚወስዱ፣ የጉጂ ዞን ኮሙዩኒኬሽን ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ አልኮ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ወረዳዎቹ ያሉባቸው ችግሮች የዝናብ እጥረት ብቻ አይደለም፤›› ያሉት አቶ ዮሐንስ፣ በመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚቀርቡ የዕለት ተዕለት ተደራሽ የምግብ ዕርዳታ በፀጥታ ችግር ማድረስ አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ እንዳስረዱት፣ በዞኑ ከሚገኙ 18 ወረዳዎች በዘጠኙ የሚኖሩ ዜጎች ለከፍተኛ ረሃብ ተጋልጠዋል፡፡ በዚህም ከ23,417 በላይ አባ ወራዎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ ሴቶች፣ እናቶች፣ ሕፃናትና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉበት ጠቁመዋል፡፡

ዕርዳታ የሚሰጥበት የራሱ የሆነ የሕግ አሠራር እንዳለው የገለጹት ኃላፊው፣ ተረጂዎች ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው መውሰድ እንደማይችሉ በሕግ ቢከለከልም፣ ዜጎች ከዚያ በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው ዕርዳታ እየወሰዱ ናቸው ብለዋል፡፡

አርብቶ አደሮቹና አርሶ አደሮቹ ዕርዳታውን መጥተው ሲወስዱ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ይቀሟቸዋል ተብሎ ስለተሠጋ፣ በመንግሥት በኩልም ዕርዳታው እንዳይሄድ አለመፈለግ ችግር እንዳለ አስረድተዋል፡፡

አንዳንድ ተረጂዎች 60 እና 70 ኪሎ ሜትር ተጉዘው የወሰዱትን ዕርዳታ ወደ መጡበት ይዘው መሄድ ስለማይፈቀድላቸው፣ ዕርዳታውን ሸጠው አነስተኛ ነገሮችን ሸምተው እንደሚሄዱ ገልጸዋል፡፡

ከወረዳ በታች ባሉ መዋቅሮች የተረጂዎችን ቁጥር በአግባቡ ለይቶ አለማወቅ፣ ከስድስቱ ወረዳዎች በታች በሚገኙ የቀበሌዎች መዋቅሮች የፈረሱ በመሆናቸው፣ የዜጎችን የዕለት ምግብ ተደራሽ ለማድረግ በእጅጉ ፈታኝ አድርገውታል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ በዘጠኙ ወረዳዎች 459,172 ዜጎች ለምግብ ዕጦት የተጋለጡ ናቸው ብለው፣ መንግሥት ዕርዳታ እያደረሰ ቢሆንም ካለው ሕዝብ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡  

በአካባቢው የድርቁ ሁኔታ ከቀጠለ ከአንድ ወር በኋላ ተጨማሪ ዜጎች ለረሃብ ይጋለጣሉ ተብሏል፡፡

በዘጠኙ ወረዳዎች 65,746 ከብቶችና ግመሎች መሞታቸውን፣ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንስሳት ደግሞ መኖና ውኃ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል፡፡

መንግሥት 65,930 ኩንታል ሳር ዕገዛ ማድረጉንና ከእንስሳቱ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. እና 12014 ዓ.ም. የምርት ዘመን በወረዳዎቹ የሚጠበቀው ሁለት የዝናብ ወቅት፣ ዝናብ ባለመገኘቱ የምርታማነት መጠኑ በእጅጉ መቀነሱን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የመጀመርያ የዝናብ ወቅት 21 በመቶ፣ በሁለተኛው ወቅት ደግሞ 37 በመቶ ብቻ ምርት መገኘቱን አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡

ከየካቲት አጋማሽ እስከ ግንቦት ወር ድረስ በሚቆየው የበልግ ወቅት ዝናብ እንደሚዘገይና ከመደበኛው በታች ይሆናል የሚል ትንበያ በመኖሩ፣ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ የሚቲዎሎጂ ኢንስቲትዩት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...