ዘንድሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የውጭ ወራሪና ተስፋፊ ኃይሎችን እንቅስቃሴ በዓድዋ ድል የመታበትን ዕለት ማለትም የካቲት 23 ቀንን ለማክበር በመንግሥት በኩል ይህ ጽሑፍ እስከ ተጠናከረበት ጊዜ የጎላ ዝግጅት ሲደረግ በበኩሌ አላየሁም፡፡ ሆኖም አንዳንድ ሙስሊም አክቲቪስቶች የሙስሊሙን ኅብረተሰብ የዓድዋ ዘመቻ አስተዋጽኦ ለማሳወቅ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ስለዓድዋ በዓል ትምህርታዊ መግለጫ የሚሰጡ ምሁራንም በማኅበራዊ ሚዲያ እየታወቁ ነው፡፡ አብዛኞቹም የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. አስታውሶ ለመዋል አዳራሽ ተከራይተዋል፡፡ ታዳሚዎችም የመግቢያ ትኬት እንዲገዙ እየተቀሰቀሱ ነው፡፡
ነገሩን ኢስላማዊ ፖለቲካዊ መልክ ለማስያዝ የሚፈልጉ ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፣ ‹‹ትውልድ እንዳይደናገር እኛም እንናገር›› በሚል ርዕስ ባለ 664 ገጽ መጽሐፋቸው በተለይ ከገጽ 37 እስከ 38 ያሰፈሩትን እንደ አጀንዳ ቀርፀው እያስተዋወቁት ነው፡፡ ወጣት ሙስሊም አክቲቪስቶች ይህንን መረጃ ሙሉ በሙሉ ትክክል እንደሆነ አድርገው በቁጭት እየወሰዱት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የሚዲያ ሰዎች ‹‹ሙስሊም ራሶች፣ ደጃዝማቾች፣ ግራዝማቾች፣ ቀኛዝማቾች ባለመኖራቸው ምክንያት ሙስሊሞች በዓድዋ ጦርነትም ሆነ በፋሽሽት ወረራ ጊዜ ያልተካፈሉ ስለሚመስላቸው፣ ይህ ሳይጻፍ የቀረ የታሪክ ምዕራፍ እንዲጻፍ ትኩረት ሰጥተው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡
ሁለቱም ጉዳዮች ጠቃሚዎች ስለሆኑ ወደፊት ጥናትና ምርምር ተደርጎባቸው በዝርዝር ይቀርባሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የዓድዋ ጦርነትን በሚመለከት ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ ስጽፍ እንደነበረው ሁሉ በ126ኛ መታሰቢያው ዓመት፣ ወርና ቀንም የሚከተለውን ጽሑፍ አጠናቅሬያለሁ፡፡ አቅጣጫ በመጥቀስ ዓድዋ ዘመቻ ምን ይመስል ነበር? ውጤቱስ ምን ሆነ የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይቻል ዘንድ አንድ በአንድ እንመለከታለን፡፡ በቅድሚያም የዓድዋ ወረራ በተካሄደበት ዘመን የአውሮፓን በተለይም የኢጣሊያን ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? የሚለውን እንመልከት፡፡
የዓድዋ ወረራ ከመካሄዱ በፊት የዓለም በተለይም የኢጣሊያና የኢትዮጵያ ሁኔታ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስመ ጥር ከነበሩት ምሁራን አንዱ የነበሩት ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት (እ.ኤ.አ. 1927-2017) በዓድዋ ወረራ ዋዜማ ስለነበረው ዓለም አቀፍ ሁኔታ ሲገልጹ፣ ‹‹ከሁሉ አስቀድሞ መታወቅ ያለበት ወቅቱ የአውሮፓ ኢምፔሪያሊዝም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰበት መሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ የአውሮፓ አገሮች ከኢንዱስትሪ ዕድገታቸው ጋር የተያያዘ ፍላጎታቸውን ለማርካት ማለትም ርካሽ የሰው ጉልበት ለፋብሪካዎቻቸው አስፈላጊ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በገበያ ማግኘት ለህልውናቸው አስፈላጊ እንደነበረም ማስተዋል አስፈላጊ ነው፡፡ አውሮፓውያን አገሮች አንዳቸው ከሌላቸው በኢንዱስትሪ ዕድገታቸው ልቀው መገኝት ስለነበረባቸው ይህንን የበላይነት ለማረጋገጥ በየፊናቸው መሯሯጥ ነበረባቸው፡፡ ታላቋ ብሪታንያና ፈረንሣይ ከደቡብ እስከ ሰሜንና ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት ሲፈልጉ፣ ጀርመንም በምሥራቅና በምዕራብ አፍሪካ አንዳንድ ቅኝ ግዛት አገሮች አግኝታ ነበር፡፡ ቤልጅየም ኮንጎን ይዛለች፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ቀጥለውም፣ ኢጣሊያም ያኔ ገና ወጣት ነፃ አገር ነበረች፡፡ ምንም እንኳን ኢጣሊያ እንደ ሌሎቹ አውሮፓ አገሮች ቅኝ ግዛት እንዲኖራት የሚፈልጉ ክፍሎች ቢኖሩም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥት ተቀናቃኝ ፓርቲ አባላት የቅኝ ግዛት ሐሳብ ፋይዳ እንደሌለው በመግለጽ አጥብቀው ይከራከሩ እንደነበር ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት፣ ‹‹ይልቁኑም ኢትዮጵያን በመውረር የሚገኘው እንደ ናይጄሪያና ሴኔጋል ያሉ አገሮችን በመውረር ከሚገኘው ጥቅም ጋር ሲነፃፀር የማይመጣጠን በመሆኑ፣ ጥቅም ይገኛል ቢባልም ደግሞ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የሚያስፈልግ በመሆኑ የዓድዋን ዘመቻን አጥብቀው መቃወማቸውን ቀጠሉ፡፡ የቅኝ አገዛዝ ጦርነት ከማካሄድ ይልቅ ሌላ የዕድገት መንገድ እንዲፈለግ ወተወቱ፡፡ በዶጋሊ የደረሰው ሽንፈት ትምህርት ሊሆን እንደሚገባም አሳሰቡ፡፡ አሉላንም እንደ ጋሪባልዲ ጀግና መሆኑን እየገለጹ ጦርነት እንዳይካሄድ በቅኔ ጭምር ቅስቀሳ ጀመሩ፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡
የዓድዋማ ዋዜማ የኢትዮጵያ ሁኔታ
አር ኤች ዊልያም ኮፊን (ከሄንሪ ሶልት ጋር በ1801 በራስ ወልደ ሚካኤል ጠያቂነት ወደ ትግራይ የመጣና ዓድዋ ውስጥም ሚስት አግብቶ ይኖር የነበረ እንግሊዛዊ ሲሆን፣ በበርካታ የጦርነት ዓውዶች ተካፋይ ሆኗል፡፡ ዲፕሎማሲያዊ ተልዕኮም ፈጽሟል) ይህ ሰው የምኒልክ ዘመንን በሦስት ከፍሎ ይመለከተዋል፡፡ አንደኛው አውሮፓውያን ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ወደ ሸዋ ገብተው የልማት ሥራ እንዲያከናውኑ ያደረጉበት ሲሆን፣ ሁለተኛውም በሰሜን በኩል የተሰነዘረባቸውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል አቅም የገነቡበት ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ደቡብ፣ ደቡብ ምሥራቅና ደቡብ ምዕራብ ግዛትን አንድ ለማድረግ ያደረጉት እንቅስቃሴ ይሆናል፡፡ አር ኤች ዊልያም ኮፊ እነዚህን ሦስት መሠረታዊ ወቅቶች ሲያብራራ ምኒልክ በ1865 ከአፄ ቴዎድሮስ ቤተ መንግሥት ከወጡበት ጀምሮ ኤደን (የመን) ከሚገኙት የብሪታኒያና የፈረንሣይ ተወካዮች ጋር ግንኙነት የሚከፈትበትን መንገድ ማመቻቸት እንደጀመሩ ገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ ለምኒልክ ጥያቄ እንግሊዞች ወዲያውኑ መልስ ስላልሰጧቸው ፊታቸውን ሙሉ በሙሉ ወደ ፈረንሣይ መለሱ፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ በ1869 ላይም ካቶሊካዊው ሚሺነሪ ማሳያ (አባ ማስያስ የሚባሉት) ሸዋ ገቡ፡፡ የእኚህም ሰው አመጣጥ ደቡብ ወዳለውና ከ1852 እስከ 1864 ባለው ጊዜ ወዳቋቋሙት ሚሽናቸው እንዲሄዱ የምኒልክን ፈቃድ ለመጠየቅ ነበር፡፡ ምኒልክ ግን አቡነ ማሳያ የመጡላቸውን ከአውሮፓ ኃይሎች ጋር ወዳጅነት እንዲፈጥሩ የሚያስችላቸውን ሰው ሲፈልጉ በነበረበት ጊዜ በመሆኑ፣ ከ1868 እስከ 1879 ባለው ጊዜ ለዓላማቸው መሳካት ሲሉ ሸዋ ውስጥ እንዲቀመጡ አደረጓቸው፡፡ በዚህ የሃይማኖት ሰው ምክርም አባ ሚካኤል የተባሉ ሰው በ1872 ወደ ኢጣሊያ ፈረንሣይና እንግሊዝ ተላኩ፡፡ የአባ ሚካኤል መልዕክት እንደታሰበው ባይሳካም ኢጣሊያ በ1879 ላይ አንድ የሳይንስና ምርምር ተልዕኮ ያለው የመልከዓ ምድር ማኅበረሰብ ላከች፡፡ ለዚህም ልዑክ ምኒልክ ‹‹ልጥ ማረፊያ›› የሚባል ሥፍራ ፈቀዱለት፡፡ በታሪክ ሰዎች እንደሚባለው ከሆነ የዚህ ቡድን ሥራ በአመዛኙ ስለላ ለማካሄድ ነበር፡፡ በኢጣሊያና በንጉሥ ምኒልክ መካከል የነበረው ግንኙነት እየተጠናከረ ሲሄድ በወቅቱ የኢጣሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ማንቺኑ አንቶኒሊ የተባለ መስፍን የኢጣሊያ ተወካይ ሆኖ እንዲያገለግል ተሾመ፡፡ አንቶኒሊም እ.ኤ.አ. ኤፕሪል (29) 1883 አንኮበር እንደደረሰም የሹመት ደብዳቤና ለምኒልክ የተላከውን ገጸ በረከት አቀረበ፡፡ ወዲያውኑም ባለ19 አንቀጽ የወዳጅነት ስምምነት በኢጣሊያ መንግሥትና በሸዋው ንጉሥ ምኒልክ መካከል እንዲፈረም አደረገ፡፡
በኢትዮጵያና በኢጣሊያ መካከል ያለው ወዳጅነት በዚህ ሁኔታ በተጠናከረ ወቅት በፈረንሣይና በኢትዮጵያ መካከል እንደዚሁ ግንኙነቱ ቀጥሎ ነበር፡፡ ይልቁኑም ቀይ ባህር በሜዲትራንን በኩል ከአውሮፓ ጋር የሚያገናኝ በገልፍ አድርጎ በህንድ ውቅያኖስ በኩል ደግሞ ወደ ኤስያ የሚወስድ በመሆኑ በእንግሊዝ በኩል ጉዳዩ ለፈረንሣይ የሚተው አልነበረም፡፡ በመሆኑም የኦቶማን ቱርክ መንግሥት የቀይ ባህርን አካባቢ ቢቆጣጠረውም እንግሊዝ ከ1849 ጀምሮ ዕውቅናን እንደማትሰጠው በይፋ አሳውቃ ነበር፡፡ በሁኔታው አስገዳጅነት ጭምር እንግሊዝ የጦር መሣሪያውን ብትልክም እንኳን መልዕክተኞቿን ማሰማራቷ አልቀረም፡፡ በ1869 ስዊዝ ካናል ሲከፈት ሜዲትራንያን ባህር ቀይ ባህርን በማገናኘት እንግሊዝ ከኢትዮጵያ የምታገኘው ጥቅም ከፍተኛ እንደሆነ አወቀች፡፡ የእንግሊዝ ፍላጎት ሲያድግ የፈረንሣይም ማደጉ አልቀረምና በ1874 አረርኖክስ የተባለው ቱጃር በአገሩና በኢትዮጵያ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲፈጠር እንደሚረዳ አስታወቀ፡፡ ይኸው ሰው ገበሬዎች አስተራረሳቸውን እንዲያሻሽሉ፣ ኢንዱስትሪ እንዲስፋፋ፣ የአውሮፓ መድኃኒት እንዲገባ፣ ወታደሮች በአውሮፓ ዓይነት እንዲሠለጥኑ፣ የአካባቢ ፀጥታ በአስተማማኝ እንዲጠበቅ ፍላጎት መሆኑን ይፋ አደረገ፡፡
ታላቁ የረሃብ ዘመን በጦርነቱ ዋዜማ
ፕሬፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ስለኢትዮጵያ ረሃብ በጻፉት መጽሐፍ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ከደረሱት አሰቃቂ የረሃብ ዕልቂቶች መካከል በዓድዋ ዘመቻ ዋዜማ ከ1888 እስከ 1892 (እ.ኤ.አ.) የተከሰተው ነው፡፡ ይኸው ረሃብ አፄ ዮሐንስ ከሞቱበት ጊዜ ጋር በመገናኘቱም በተለይም በትግራይ አካባቢ እግዚአብሔር የላከው ቅጣት እንደሆነ ተደርጎ ይነገር ነበር፡፡ ከታሪክ ማኅደር ለመረዳት እንደሚቻለው ግን የረሃቡ መንስዔ አፄ ዮሐንስ ከመሞታቸው በፊት የተከሰተ የአንበጣና የሌሎች ፀረ ሰብል ነፍሳት ወረራ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ነበር፡፡ ለከብቶቹ ዕልቂትም ቢሆን በ1885 እና በ1887 ለጦርነቱ ማካሄጃ ተብለው ከኢጣሊያ የመጡ በቅሎዎችና ፈረሶች ያመጡት በሽታ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ቸሩሊ የተባለው የታሪክ ጸሐፊ እንደመዘገበውም ኢጣሊያዊው ጄኔራል ማርዞኖ በጥቅምት ወር 1887 ምፅዋ ሲደርስ ከእርሱ ጋር 800 ፈረሶችና አንድ ሺሕ በቅሎዎችን ከኔፕልስ አስመጥቶ ነበር፡፡ አጋሰሶቹም በሽተኞች ነበሩ፡፡ በሽተኞቹን እንስሳት በሚመለከት አንዳንድ ሰዎች ሆን ተብሎ የተዘጋጀ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ሆን ተብሎ አይደለም ይላሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ የከብቶቹ በሽታ ከሰሜን ወደ ደቡብ በከፍተኛ ፍጥነት ተዛምቶ ብዙ ኢትዮጵያውያንን ያለ ከብት አስቀረ፡፡ በመሆኑም ገበሬው ያለ በሬ ቀረ፡፡ በዚህም ምክንያት እርሻ ሊታረስ አልቻለም፡፡ ስለዚህም የአፄ ምኒልክ መንግሥት ሕዝብን ማረጋጋትና ከብቱን ላለቀበት በሽታው ካልደረሰበት አካባቢ አስመጥተው መተካት ስለነበረባቸው ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገባ፡፡ ይሁንና ረሃቡን ለማስወገድ በተደረገው ጥረት ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ንብረት በመንቀሳቀሱ፣ ለዓድዋ ዘመቻ ብዙ ሕዝብ ወደ ግንባር ለማዝመት ለተደረገው ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በአገሪቱ ረሃብ የሰፈነ ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ እንደ ሐረር ያሉ የንግድ ማዕከሎችና ሌሎች የወርቅ ማዕድን የሚገኝባቸው ሥፍራዎች በአፄ ምኒልክ መንግሥት ቁጥጥር ሥር ስለነበሩ ጦርነቱን ለማካሄድ ረድቷቸዋል፡፡
ወደ ዓድዋ ጉዞ
አፄ ምኒልክ የኢጣሊያንን ወረራ በመቃወም ወደ ዓድዋ ሲያመሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሁሉ ለመቀስቀስ ሁኔታው አስገድዷቸው ነበርና የሚከተለውን የክተት አዋጅ መስከረም 7 ቀን 1888 አሳወጁ፡፡ አዋጁም፣ ‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ግን ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፡፡ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠረጥረውም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን አገር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም ዓይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያስፈራራ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምከኝም፡፡ አሁንም ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ አልተውኸም፡፡ ማርያምን!! ለዚህ አማለጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታው ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፤›› የሚል ነበር፡፡
በዚህ ጥሪም እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ጦሩም አምባላጌ ደረሰ፡፡ ስለአምባላጌው ጦርነት በርክሌይ ሲገልጽ፣ ‹‹አምባላጌ በተለይም ቡታ በተባለው ቦታ ላይ በአንድ በኩል በጀግናው በራስ አሉላና በራስ መንገሻ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በራስ መኮንንና በራስ ሚካኤል የሚመራው ጦር የጠላትን ወገን እንዲሸሽ አደረጉት፤›› ይላል፡፡ ቀጥሎም ‹‹የኢጣሊያ ጦር በጀግንነት የተዋጋ ቢሆንም፣ ሁኔታውን የሚቋቋመው አልሆነም፡፡ ከዚህ መዓት የተረፉት ኢጣሊያኖች እንዳሉት የሐበሾች ቁጥር ከመጠን በላይ ብዙ ነው፡፡ ብዙ ይሞታል፣ ነገር ግን ሌላው ወደፊት ይገፋል፡፡ የምድሩም ተኩስ አይገታቸውም፡፡ ሁኔታው ከመሬት የሚፈሉ አስመሰላቸው፡፡ ጦሩ እየተኮሰ ይገድላቸዋል፣ ነገር ግን ቁጥራቸው እየበረከተ ይሄዳል፤›› ማለታቸውን አሥፍሯል፡፡ ‹‹መድፈኞች ተኩሱን እንዳያቆሙ በየአቅጣጫው የራስ አሉላ ጦር ፈጥኖ እየደረሰ ጨፈጨፈው፡፡ ጄኔራል ቶዘሊም አምባለጌ ላይ ተገደለ፡፡ መቀሌም ከአርባ ቀን ጦርነት በኋላ ተያዘች፤›› በማለት በርክሌይ ስለጦርነቱ ገጽታ ጽፏል፡፡ ምንም እንኳን ኢጣሊያኖች ሽንፈት ቢደርስባቸውም ታኅሳስ 10 ቀን 1887 የኢጣሊያ ፓርላማ ባደረገው ስብሰባ ለጦርነቱ መቀጠል ከፍተኛ በጀት መመደቡ ይታወሳል፡፡ ምፅዋ ወደብ የሚደርሰው መሣርያ ወደ አዲግራት ለማድረስ 21 ሺሕ ግመል ያስፈልግ የነበረ ሲሆን፣ አረሞንዲ ባደረገው ጥረት 8‚200 ግመልና 3‚000 በቅሎ ተገኝቶ እንዲጓጓዝ አደረገ፡፡ 38‚000 የሚሆኑ ወታደሮች፣ 8‚584 በቅሎዎችንና 100,000 በርሜሎች ከመርከብ ወርደዋል፡፡ ምንም እንኳን ይህ ስንቅና ትጥቅ ለጊዜው ፋታ የሰጣቸው ቢመስልም፣ ጦርነቱ ቀጥሎ መቀሌ ሙሉ በሙሉ ጥር 4 ቀን 1888 ከኢጣሊያኖች ፀዳች፡፡ የአፄ ምኒልክም ጦር አቅጣጫውን ወደ አዲግራት በማድረግ ፋንታ ፊቱን ወደ ሰሜን ምዕራብ በማዞርና ጥር 22 ቀን ከሐውዜንም ጉዞውን ወደ ዓድዋ ቀጠለ፡፡
የዓድዋ የጦር አሠላለፍ
የዓድዋ ጦርነት ዓለሜ እሸቱ (ዶ/ር) እንዳጠናቀሩት አፄ ምኒልክ፣ የጦርነቱን ክተት አውጀው ከአዲስ አበባ የተነሱት ጥቅምት 2 ቀን 1888 ነበር፡፡ ኅዳር 28 ቀን 1888 አምባላጌ ላይ፣ ታኅሳስ 1888 መቀሌ ላይ በተደረገው ዘመቻ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ የፍልሚያው ሥፍራ ዓደዋ ላይ የነበረ ሲሆን የካቲት 23 ቀን 1888 ያዘመቱት ጦር ቁጥር ግን በልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተሰላው በተለያየ ቁጥር ነው፡፡
የኢንጂነር ካፑቺ ግምት — 85 ሺሕ ባለጠመንጃ ሲገመት ከዚህ ውስጥ
ራስ መኰንን (ሐረር) – ስምንት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ሚካኤል (ወሎ) – ስምንት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ተክለ ሃይማኖት (ጎጃም) – አምስት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ወሌ — አምስት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ መንገሻ ዮሐንስ — አምስት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ መንገሻ አቲከም — ሦስት ሺሕ ጠመንጃ
ዋግ ሹም ጓንጉል — ሃያ ሺሕ ጠመንጃ
እቴጌ ጣይቱ — አራት ሺሕ ጠመንጃ (ከደጃዝማች ጣሰው ጭምር)
የአፄ ምኒልክ የክብር ዘበኛ ጦር — ሦስት ሺሕ ጠመንጃ
በጅሮንድ ባልቻ — ሦስት ሺሕ ጠመንጃ
ሊቀመኳስ አባተ — ሁለት ሺሕ ጠመንጃ
ዕቃ ቤት፣ ጠጅ ቤት፣ ሥጋ ቤት — አሥራ አምስት ሺሕ ጠመንጃ
በዓድዋ ጦርነት ላይ በኢትዮጵያ ወታደሮች ከተማረኩና ከተያዙ በኋላ ነፃነቱን አግኝቶ ኢጣሊያ የተመለሰው የጄኔራል አልቤሮቶኒ ግምት ኢትዮጵያ ከ111 ሺህ እስከ 122 ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሠለፈች ሲሆን ከዚህም ውስጥ፣
ራስ መኮንን (ሐረር) ከ15 ሺሕ እስከ 16 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ሚካኤል (ወሎ) ከ14 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ተክለሃ ይማኖት (ጎጃም) ከአምስት ሺሕ እስከ ስድስት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ ወሌ ከስድስት ሺሕ እስከ ሰባት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ መንገሻ ዮሐንስ ከሦስት ሺሕ እስከ አራት ሺሕ ጠመንጃ
ራስ አሉላ ከሦስት ሺሕ እስከ አራት ሺሕ
የአፄ ምኒልክ ከሰላሳ ሦስት ሺሕ እስከ ሰላሳ ስምንት ሺሕ ጠመንጃ
እቴጌ ጣይቱ ከአምስት ሺሕ እስከ ስድስት ሺሕ ጠመንጃ
በወቅቱ ኢትዮጵያን ሊጎበኝ የመጣው ሩሲያዊው የካውንት ሊኦንትየፍ ግምት 85 ሺሕ እግረኞች፣ 22 ሺሕ ስድስት መቶ ፈረሰኞች፣ 42 መድፈኞች ሲሠለፉ ከእነዚህም ውስጥ፣
ራስ መኮንን…15 ሺሕ ጠመንጃዎችንና አራት መድፎች
ራስ ሚካኤል … ስድስት ሺሕ ጠመንጃዎችና አሥር ፈረሰኞች
ራስ ወሌ … አሥር ሺሕ ጠመንጃዎች
ራስ መንገሻ አቲከም … ስድስት ሺሕ ጠመንጃዎች
ራስ መንገሻ ዮሐንስ … ስድስት ሺሕ ጠመንጃዎችና ስድስት መድፎች
ራስ አሉላ … ሦስት ሺሕ ጠመንጃዎች
አፄ ምኒልክ … 30 ሺሕ ጠመንጃዎች፣ 12 ሺሕ ፈረሶችና 32 መድፎች፣
እቴጌ ጣይቱ … ሦስት ሺሕ ጠመንጃዎችና ስድስት ሺሕ ፈረሰኞች ነበሩ፡፡
አፄ ምኒልክ በዓድዋ ካሠለፏቸው ወታደሮች ሌሎች የራስ ወልደ ጊዮርጊስ (ከስድስት እስከ ስምንት ሺሕ)፣ የራስ ተሰማ ናደው (ከአራት እስከ አምስት ሺሕ)፣ የራስ ዳርጌ ሦስት ሺሕ፣ የደጃዝማች ወልደ ፃዲቅ ሦስት ሺሕ፣ የደጃዝማች ልዑል ሰገድ ሦስት ሺሕ፣ ወዘተ. ግማሹ አዲስ አበባን ሲጠብቁ ሌላው ኢጣሊያኖች በአፋር በኩል ያስገቡትን ጦር ለመግጠም በመዝመቱ ዓድዋ ሳይዋጉ መቅረታቸው፣ እንዲሁም ከአፋሮቹ ሌላ ኢጣሊያኖች በዘይላ በኩል ሱማሌዎችን አነሳስተው ኢትዮጵያን እንዲወጉ ለማድረግ የነበራቸው ዕቅድ የእንግሊዝና የፈረንሣይ መንግሥት ሳይስማሙ በመቅረታቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
ያም ሆነ ይህ በጦር መሣሪያውና የተሠላፊው ብዛት በሚመለከት የተለያዩ ጸሐፊዎች የተለያየ አቆጣጠር እንደነበራቸው ሁሉ፣ በአሠላለፉም ቢሆን ተለያይተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ኢጣሊያውያን፣ እንግሊዛዊው አውጎስት ዋይልድና ግራዝማች ዮሴፍ የተባሉት ጸሐፊዎች ያቀረቡት አሠላለፍ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የኢጣሊያ ጸሐፊዎች እንዳቀረቡት
አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ‹‹ዓዲ ማህላሽ›› በተባለው ሥፍራ ዓደዋ ከተማ አጠገብ ነበሩ፡፡
ራስ ወሌ ‹‹ማይ ደላዕታ›› ላይ በመሠለፍ የኋላ ደጀን ነበሩ፡፡
ራስ ሚካኤል ግንባር ቀደም በመሆን በሠናይ ፀባህና በእንዳ ሚካኤል መሀል ነበሩ፡፡
ፊታውራሪ ገበየሁ ከራስ ሚካል በስተቀኝ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ከ22 ወንዝ በስተግራ ከፊታውራሪ ገበየሁ በኋላ፣ ራስ መኮንን አዲ አቡን በስተሰሜን ዳዕሮ ተክሌ አጠገብ፣
ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ዋግ ሹም ጓንጉል በገራዓና በማርያም ሸዊቶ አጠገብ ነበሩ፡፡
ኦገስት ዋይልድ የተባለው እንግሊዛዊ ጸሐፊ ደግሞ
አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በፍረሞና ኮረብታ ላይ
ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አፄ ምኒልክ ጦር ፊት ለፊት
ራስ መኮንን በዓድዋ አካባቢ
ራስ ሚካኤል ከሶሎዳ ኮረብታ በስተደቡብ
ራስ መንገሻ ዮሐንስ – ከሰሎዳ ኮረብታ በስተሰሜን
ራስ አሉላ በአዲ አቡን አካባቢ
ራስ ወሌ ከዓድዋና ከራስ መኰንን ጦር ደቡብ ምዕራብ
ዋግሹም ጓንጉል – ከዓድዋ (ከራስ መኮንን ጦር) ሰሜን ምዕራብ
ደጃዝማች በሽር ከራስ ወሌና ከዋግሹም ጓንጉል በስተኋላ ነበሩ በማለት መዝግቧል፡፡
በዓድዋ ጦርነት የኢጣሊያ የጦር አሠላለፍ
በዓድዋ ጦርነት ሃያ ሺሕ ያህል የኢጣሊያ ጦር የተከማቸው ሳውሪያ (ኢንቲጮ) ላይ ሲሆን፣ ይህም ከዓድዋ በስተምሥራቅ 16 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ የሚገኝ ሥፍራ ነው፡፡ የኢጣሊያ አሠላለፍ በአራት የተከፈለ ነበር፡፡ እርሱም፡–
ጄኔራል ዳቦርሜዳ… የቀኝ ብርጌድ – 3‚500 ወታደሮችና 18 መድፎች
ጄኔራል አልቤርቶኒ …የግራ ብርጌድ – 8‚300 ወታደሮችና 12 መድፎች
ጄኔራል አሪሞንዲ … የመሀል ብርጌድ – 2‚900 ጠመንጃዎችና 12 መድፎች
ጄኔራል ኤሌና … ተጠባባቂ (ሪዘርቭ) ብርጌድ 3‚350 ወታደሮችና መድፎች ነበሩት፡፡ አፄ ምኒልክ ከእነ ጦራቸው ዓድዋ ላይ የካቲት ሰባት ቀን 1888 ኢጣሊያኖች ደግሞ ኢንቲጮው ላይ የካቲት ስድስት ቀን ካሰፈሩ በኋላ፣ የሁለቱ ወገን ሠራዊት ተፋጠው እስከ የካቲት 23 ቀን 1888 ድረስ ቆዩ፡፡ እስከዚያ ዕለትም ሁለቱም የተፋጠጡ ወገኖች ሌላውን ሲሰልለው ሰነበቱ፡፡ በመጨረሻም ኢጣሊያውያን ‹‹ኢትዮጵያ ሠራዊት ገሚሱ ቀለብ ፍለጋ ወደ ሽሬና ወደ ተንቤን፣ እንዲሁም ተከዜን ተሻግሮ ወደ ፀለምት ተበትኗል፡፡ ሌሎች በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ወታደሮች ወደ አክሱም ፅዮን እሑድ የሚውለውን የጊዮርጊስ በዓል ለማስቀደስ ሄደዋል›› የሚል መረጃ ደረሳቸውና በዚሁ ዕለት ማለትም የካቲት 23 ቀን እሑድ የጊዮርጊስ ዕለት በአጥቂነት የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመውጋት ወሰነ፡፡ የአፄ ምኒልክ ዋነኛ ጸሐፊ ገብረ ሥላሴ እንደሚሉትም (ገጽ 262) ቀለብ ፍለጋ አክሱም ፅዮን ከሄዱት እሑድ ለጦርነቱ የተመለሱት ከሦስት እጅ ሁለት እጅ ነበሩ፡፡
የዓድዋ ጦርነት በጆርጅ ኤፍ በርክሌይ ዕይታ
ጆርጅ ኤፍ በርክሌይ የተባለ ጸሐፊ ‹‹የዓድዋ ዘመቻን የምኒልክ አነሳስ›› በሚል ርዕስ ያሳተመው መጽሐፉ በዳኛው ወልደ ሥላሴ ተተርጉሞ እንደምናነበው፡፡ … አፄ ምኒልክ ሆኑ የኢጣሊያው የጦር መሪ ባራቲየሪ ቀድመው ለማጥቃት ሳይሽቀዳደም አንዱ የሌላው ጠላት ስንቅ እንዲያልቅ እየተመኘ ጦርነቱን ሳይጀምር በመቆየቱ፣ ሁለቱም ስንቃቸውን ወደ መጨረሱ ተቃርበው ነበረ፡፡ ድል በመምታት መበቀልን የፈለገው የሮማ ሕዝብ ውሎ ባደረ ቁጥር ተስፋ እየቆረጠ በመሄዱ የባራቲየሪም ክብርና ዝና ወደቀ፡፡ የካቲት 15 ቀን 1888 በሚስጥር ባራቲየሪ ተሽሮ ጄኔራል ባልዲሴራ የጦሩ አዛዥ እንዲሆን ተሾመ፡፡ ይሁንና ይኸው የጦር መሪ የካቲት 21 ቀን 1888 በማይ ገበታ በኩል ወደ ማይ ማረት ለማፈግፈግ ወስኖ መንገድ ከጀመረ በኋላ፣ በዚሁ ምሽት አራቱን ጄኔራሎች ሰብስቦ ያለው ምግብ እስከ የካቲት 23 ቀን ወይም የካቲት 24 ቀን ድረስ ብቻ የሚያቆያቸው መሆኑን ካስረዳ በኋላ ወደ ሰንአፌ ለመሸሽ ወይም አስፈላጊው ጥናትና ዝግጅት እንዲያደርጉ አማከራቸው፡፡ (በዚህ ጊዜ) ጄኔራል ዳቦር ሜዳ፣ የጄኔራል ባራቲየሪን ንግግር ከሰማ በኋላ መሸሹ የማይደረግ ነው ብሎ ስሜቱን ገልጾ ምክንያቱን ማስረዳት ጀመረ፡፡ አንደኛ የኢጣሊያ ሕዝብ ከምናሳፍር ሦስት ሺሕ ወታደር ቢሞትብን ይመረጣል፡፡ ሁለተኛ የወታደሩ ሞራል በጣም ይወድቃል፡፡ ሦስተኛ ጠላቶቻችን ከእኛ ፈጥነው ለመጓዝ ስለሚችሉ አሁንም በመሸሽ ላይ ሳለን ደርሰው ለራሳቸው ከሚያመቻቸውና ከመረጡት ቦታ ላይ አደጋ ሊጥሉብን ይችላሉ፡፡ ይህ ከሚሆን ወጥተን ማጥቃቱ ይሻላል ሲል አሳሰበ፡፡
ጄኔራል አልቤርቶኒም የጄኔራል ዳቦርሚዳን ሐሳብ ደግፎ ‹‹የጠላት ጦር ምግብ ለመሰብሰብ የተበታተነ ከመሆኑም በላይ፣ ብዙውም ወደ አገሩ በመመለስ ላይ ነው፤›› በማለት የሐበሻ ጦር ሠፈር በሁለት መሪዎች የተከፈለ ከመሆኑም በላይ ከ14 ሺሕ ወይም ከ15 ሺሕ ጦር በላይ እንደማይኖረው ገለጸ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በሁኔታው አፄ ምኒልክም በጣም ተጨንቀዋል፡፡ የቀራቸው ሦስት ወይም ለአራት ቀን የሚሆን ስንቅ ብቻ ነበር፡፡ ጠላት ከምሽጉ ወጥቶ ማጥቃት እንዲጀምር ብርቱ የሆነ ፀሎታቸው ነበር፡፡ ይህንንም ዕድል ለማግኘት ለባራቲየሪ እንዲደርስ የሚያስወሩት ፕሮፓጋንዳ፣ ‹‹በአፄ ምኒልክ የጦር ሠፈር ችግርና ረሃብ ፀንቶ ሠራዊቱ እየሸሸ በመሄድ ላይ መሆኑና ዙሪያውም የሚገኘው ሕዝብ ተነስቷል፤›› የሚል ነበር፡፡ አፄ ምኒልክ እንደተመኙትም የካቲት 22 ቀን 1888 ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጄኔራል ባራቴሪ ወጥቶ ለማጥቃት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጠ፡፡ የባራቴሪ ዓላማ በሦስት አቅጣጫ ሌሊቱን ሲጓዝ አድሮ የጠላት ጦር ሳያውቅ በተራራው ገመገም ሥር ለመመሸግና የመከላከያ ቦታ ለመያዝ ነበር፡፡ ከዚያም በኋላ የጠላት ጦር ቢያጠቃ መልካም፣ ካልሆነም የሐበሻን ጦር ፍርኃት እንዲያድርበት በዙሪያው ለሚገኘው ሕዝብ ማሳየት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢጣሊያ ጦር ተንቀሳቅሶ የነዚህን ተራራዎች ገመገም በሚይዝበት ጊዜ፣ የሐበሻው ጦር በርግጎ ወደ ኋላ ይመለሳል የሚል እምነትና ተስፋ ነበረው፡፡ ይህም ከሆነ ዓድዋን በሰላም (ያለ ችግር) ለመያዝ እንደሚችልም ገምቶ ነበር፡፡ የጦሩ አሠላለፍም፣
ሀ. በቀኝ በኩል በጄኔራል ዳቦር ሜዳ የሚመራው የበላህን ተራራ አምባ፣ የበላህን ጎጥና በዙሪያው ያለውን ቦታ፣
ለ. በመካከል በጄኔራል ኦሪሞንዴ የሚመራው የበላህን ተራራ፣
ሐ. በግራ በኩል ‹‹በጀኔራል አልቤርቶኒ የሚመራው ኪዳነ ምሕረት ብለው የጠሯትና (ለዚች ተራራ የተሰጠው ስም በትክክል አልነበረም) ራይ የተባሉትን ተራራዎች እንዲይዝ፣
መ. በጀኔራል ኤልና የሚመራው ተጠባባቂው ጦር ረቢ አርኧየኒ በተባለው ቦታ ሆኖ እንዲጠባበቅ፣ የቀኑ ትዕዛዝም ‹‹የካቲት 22 ቀን 1888 ቁጥር 87 ዛሬ ማታ ጦሩ በሦስት አቅጣጫ ወደ ዓድዋ በሚከተለው ሁኔታ ይንቀሳቀሳል፡፡
… የቀኙ ክፍል ጄኔራል ዳቦርሚዳ ሁለተኛ እግረኛ ጦር ብርጌድ የሞባይል (ተንቀሳቃሽ) ሻለቃ ጦር የሁለተኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ የአምስተኛ፣ የስድስተኛና የሰባተኛ ከባድ መሣሪያ ጓድ፡፡
…ግራው መስመር በጄኔራል አልቤርቶኒ (የሚመራ ሆኖ) አራት የአገሬው ተወላጅ ሻለቃ ጦር የአንደኛ ባትሪ ብርጌድ አባሎች፣ ከአንደኛ፣ ከሁለተኛ፣ ከሦስተኛና ከአራተኛ ከባድ መሣሪያ ክፍል ጋር፡፡
ተጠባባቂ ጄኔራል ኤሌና፣ ሦስተኛ እግረኛ ብርጌድ፣ ሦስተኛ የአገሬው ተወላጅ ያለቃ ጦር ሁለት የመትረየስና የከባድ መሣሪያ ጓድና አንድ ኮፖኒ መሐንዲሶች፡፡
…ጄኔራል ዳቦር ሜዳ፣ በአርሞንዲና በአልቤርቶኒ የሚመራው ጦር ከሌሊቱ ሦስት ሰዓት ከቦታው እንዲንቀሳቀስ ሲታዘዝ ከአንድ ሰዓት በኋላ ደግሞ ተጠባባቂው ጦር የመካከለኛውን መሥመር ተከትሎ ይንቀሳቀሳል፡፡
…የቀኙ ረድፍ በዛሃላ ጎጥ አድርጎ ጎልደም ጎጥን አልፎ ወደረቢ አርእየኒ ጎጥ ይጓዛል፡፡ የመካከለኛው ተጠባባቂ ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንድብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ረድፍ በአዲ ዳኪ አድርጎ በጉንደብታ በኩል ረቢ አርእየኒ ይጓዛል፡፡ የግራው ደግሞ ከሶሎዳ በአዲ ቸራይራ በኩል ወደ ኪዳነ ምሕረት ይጓጓል፡፡…›› የሚል ነበር፡፡ (በዚህም ዓይነት ኢጣሊያኖች ብዛቱ 100 ሺሕ የሚሆን የጦር መሣሪያ ጦርና ጋሻ የያዘውን የአበሻን ሠራዊት ለመግጠም 17 ሺሕ ሰባት መቶ ወታደርና 56 መድፍ ጠምደው ተሰናድተዋል፡፡
በአፄ ምኒልክ ግንባር የተሠለፈው ጦር፡– በዶ/ር እሸቴ ዓለሜ ጥንቅር መሠረት፣ አፄ ምኒልክ ከእነ ጦራቸው ዓድዋ ላይ መጋቢት 3 ቀን 1888 በጻፉት ደብዳቤ አፄ ምኒልክ ኢጣሊያኖችን ኢንቲጮ ድረስ ሄደው ለመውጋት ያልፈለጉበት ምክንያት፣ ቦታው ለአጥቂ ጦር የማያመች መሆኑን ገብረ ሥላሴ ለሞንድ ቬዳይሌት በየካቲት 7 ቀን 1888 ላይ ሠፍረዋል ሲሉ በዚያን ጊዜ ገልጸዋል፡፡ ከዚያም ጊዜ አንስቶ እስከ የካቲት 23 ቀን ቆይተዋል፡፡
የካቲት 22 ቀን 1888
…አልቤርቶኒ የታዘዘለትን ትክክለኛ ጦር ሠፈር በመፈለግ ከሌሎቹ የኢጣሊያ ብርጌዶች ተነጥሎ ኪዳነ ምሕረት ኮረብታ ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት አካባቢ ሲደርስ፣ በሜጀር ቱሪቶ ይመራ የነበረው የብርጌዱ ግንባር ቀድሞ ጦር ቀደም ብሎ በመድረሱ በዚህ ቀን በጥበቃ ተራ ላይ ከነበረው ከራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ እንዲሁም ጥቂት ቆይቶም ከዋግ ሹም ጓንጉል፣ ከደጃች ገሠሠና ከበጅሮንድ ባልቻ ሠራዊት ጋር ውጊያ እንደ ጀመረ ኮንቲሮዘኒ የተባለው የታሪክ ጸሐፊ መዝግቦታል፡፡ ይኸው ኮንቲሮዚ የተባለው ጸሐፊ ዓድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማቴዎስ ጋር ያስቀድሱ የነበሩት አፄ ምኒልክ፣ የኢጣሊያ ወታደር በዚህ ቀን ጦር ለማድረግ መወሰኑን በተረዱ ጊዜ ሠራዊታቸውን በያለበት ቀስቅሰው ከእቴጌ ጣይቱና ከአቡነ ማትያስ ጋር ሆነው ከዓድዋ ተነስተው በምሥራቅ በኩል በሚገኘው አባ ገሪማ ኮረብታ ላይ ሰፍረው ነበር፡፡ የአልቤርቶኒ ብርጌድ ኪዳነ ምሕረት እንደ ሠፈረና ግንባር ቀደሙም ጦር አልፎ መምጣቱን እንደ ሰሙ በእነ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ በእነ ደጃዝማች በሻህ አቡ የሚመራውን የራሳቸው ጦር ፊት ለፊት፣ የእቴጌ ጣይቱንና የጎጃሙን ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ጦር በስተግራና በስተቀኝ እንዲዘምቱ አዘው ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ሲሆን ጦርነቱ ተጀመረ፡፡
…ከዚያ በኋላ ነጋሪት መቺው ‹‹ውጋ! ውጋ!›› እያለ እየተበረታታ፣ ኢትዮጵያ ሠራዊት በግራና በቀኝ በሁሉም አቅጣጫ ከቦ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ አብረው በሚያዙት ላዳት (አባ ገሪማ አጠገብ) ሦስት ኪሎ ሜትር ከጠላት ሠፈር ርቆ ይገኝ የነበረውን የኢትዮጵያ ከባድ መሣሪያ (መድፍ) እየተደገፈ፤ በጄኔራል አልቤርቶኒ ይመራ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ደመሰሰው፡፡ ከዚህ በኋላ ከጠዋቱ 4፡30 ሰዓት ሲሆን ጄኔራል አልቤርቶኒ የተረፉ የኢጣሊያ ወታደሮች መድፈኞች ወደኋላ እንዲሸሹ አዞ ነበር፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ ሠራዊት ማየል ጄኔራል አልቤርቶኒ ከብዙ መቶ ኢጣሊያኖች ጋር ተማረከ፡፡ …
ጦርነቱም ከጠዋቱ 5፡00 ሰዓት አካባቢ ሲሆን አበቃ፡፡ ኤርትራንና ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ የመግዛት ሕልምም ዕውን ሳይሆን ቀረ፡፡
ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡