Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የኢኮኖሚ ዕድገቱ የዋጋ ንረትን እንዲገታልን እንሻለን!

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ማክሰኞ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. ፓርላማ ተገኝተው፣ የፓርላማ አባላት ላቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች ውስጥ የኢኮኖሚው ዘርፍ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአብዛኛው ኅብረተሰብ ክፍል ራስ ምታት በሆነው፣ በወቅታዊው የዋጋ ንረት ዙሪያም መንግሥት ሠራ ያሉትን አብራርተዋል፡፡

 ከአገራዊ ኢኮኖሚ አንፃር እየተሠራ ያለው ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ያመላከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ነበሩ ያሏቸውንም ተግዳሮቶች አመላክተዋል፡፡  

በአብዛኛው ግን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መገንዘብ የሚቻለው በብዙ ችግር ውስጥ ቢኮንም፣ አሁንም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው መሆኑን ነው፡፡ በአኃዝ ተደግፎ በቀረበው መረጃ ዋና ዋና በሚባሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ ከቀደሙት ዓመታት የተሻለ ውጤት ተገኝቷል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱን ከሚያመላክቱ በአኃዝ ከተጠቀሱ ውጤቶች መካከል፣ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ያሳየው ዕድገት፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ዕድገት፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ወደ ተሻለ አገልግሎት መግባታቸው ተጠቅሷል፡፡ የግብርና ዘርፉ ውጤታማ ስለመሆኑም አመልክተዋል፡፡

የውጭ ዕዳን ከማቃለል አኳያ የተመዘገበውንም ውጤት ማመላከታቸው አገር በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና ማሳካት የቻለችው ክንውኖች በርካታ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አፈጻጸም በመልካም የሚታይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከእያንዳንዳችን ኑሮ አንፃር ሲመዘን ምን አስገኝቶልናል? የሚለው ጥያቄ ብዥታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡

በኢኮኖሚ ባለሙያዎች ትንታኔም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ ያስቀመጡት አኃዛዊ መረጃ፣ የኢትዮጵያን ዕድገት የሚያሳይ ቢሆንም፣ የዋጋ ንረትን ማስተካከል ያልቻለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡

ሥር እየሰደደ የሄደውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነትን ለማከም ተብሎ መንግሥት የወሰዳቸው ዕርምጃዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጠቅሰው ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን እንዲህ ያሉ የተለያዩ ዕርምጃዎች ከተወሰዱና ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱም እንደቀጠለ ከሆነ ለምን ገበያውን ማረጋጋት አልቻለም? የሚለውን ጥያቄ የብዙዎች ነው፡፡ የቱንም ያህል እየተሠራ ቢሆን ገበያው የሚነግረን የዋጋ ንረቱ ከመርገብ ይልቅ ወደላይ እያሻቀበ መምጣቱ ነው፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር ጆሯችን የሚደርሰው ዋጋው ‹‹ጨመረ›› እንጂ፣ ‹‹ቀነሰ›› የሚባል ምርት የለም፡፡

ይህ የዋጋ ንረት በሁሉም የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ምርት ላይ የሚታይ በመሆኑ፣ በኢኮኖሚ ዕድገቱ እየሰው የማለታችንን ያህል፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ያልቻለ ዕድገት እንዴት እንደሚታሰብ ግራ ማጋባቱ አይቀርም፡፡ ዕድገቱ የዛሬ ኑሯችን ላይ ሊገለጽ ካልቻለ፣ ቢያንስ የዋጋ ንረቱ ከዚህም በላይ እንዳይሄድ ማድረግ እንዴት ተሳነው? ብንል ትክክል ነው፡፡

መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለማርገብ እየወሰደ ያለው ዕርምጃ ወይም የወሰደው ዕርምጃ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ አፍስሶ እንዲሠራጭ የሚያደርጋቸው ወይም ያደረጋቸው ምርቶች ገበያውን ለማረጋገት ሌላው ቢቀር የዋጋ ንረቱ ባለበት እንዲቆም ያላደረጉበት ምክንያት ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው፡፡

ሌላውን ትተን የምግብ ዘይትን ዋጋ ብቻ በምሳሌነት እንጥቀስ፡፡ በቅርብ ዓመታት የአገራችንን የምግብ ዘይት ፍላጎት ለመሸፈን የሚችሉ ትልልቅ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ ሲገቡ ትልቅ ተስፋ ተደርጎ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ የእነዚህ ፋብሪካዎች መከፈት ከውጭ የሚገባውን ዘይት ከመተካት ባሻገር እየተሰቀለ የመጣውን ዋጋ ይቀንሰዋል የሚል እምነት አሳድሮ ነበር፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በደመቀ ሁኔታ በተመረቁበት ወቅት ከ400 ብር እስከ 450 ብር ይሸጥ የነበረው አምስት ሊትር ፈሳሽ ዘይት አሁን ላይ ከ750.00 ብር በላይ ሲቸበቸብ መስማት ግራ ቢያጋባን ወይም ደጋግመን ጥያቄ ብናነሳ አይገርምም፡፡  

በማክሰኞው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ላይ እንደተደመጠውም፣ የዘይት አምራቾች እንዲያመርቱ ከተያዘላቸው የውጭ ምንዛሪ በላይ እንደተሰጣቸው ሁሉ ተናግረው፣ ይህም ተጠቃሚው ላይ ዋጋ እንዳይጨምርና በቅናሽ ዋጋ እንዲገዛ ታስቦ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

እውነታው ግን ይቀንሳል የተባለው የምግብ ዘይት ጭራሽ ዋጋው ጣራ ነክቷል፡፡ ስለዚህ ዋጋን ከማረጋጋት አንፃር እየተደረገ ያለው ጥረት፣ ተደርጓል ተብሎ የሚገለጸው ሁሉ ውጤቱ ይህ ከሆነ ችግሩ ምንድነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

በተመሳሳይ ሌሎች መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ከፍተኛ ወጪ ተደርጎባቸው ወደ ገበያ እየገቡ ከሆነ፣ የዋጋ ንረቱን ለምን ማከም አልተቻለም የሚባለውን ጥያቄ አሁን ላይ በአግባቡ መፍታት ካልቻለ የቱንም ያህል ቢደከም የዋጋ ንረቱ ሊቀጥል እንደሚችል መግለጹ ስህተት አይሆንብንም፡፡

ስለዚህ አሁንም በዚህ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ለምን ዋጋን ለማረጋጋት አልቻሉም ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን የችግሩን ምንጭ ለይቶ መፍትሔ መፈለግ የግድ ይላል፡፡ አሁን ላይ ያለው የዋጋ ንረት ሄዶ ሄዶ ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ ከወዲሁ ግምት ውስጥ ማስገባትና ለዕርምት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በአገር ውስጥ ካለው ምርት ባሻገር ገበያውን ለማረጋጋት መንግሥት አስገብቻለሁ ያለው ምርት ገበያ ውስጥ ገብቶ ለውጥ ያልመጣው የሆነ ችግር ቢኖረው ነው በሚል ስለሚያሳስብ ነው፡፡ በመሆኑም ለመፍትሔ ተብለው የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ለውጥ ካላመጡ ወይም ገበያውን ካላረጋጉ ነገም ተመሳሳይ ዕርምጃ ቢወሰድ ያው ሊሆን ስለሚችል ችግሩ ምንድነው? ለሚለው የብዙዎች ጥያቄ መልስ እንፈልጋለን፡፡ የኢኮኖሚው ዕድገቱ የዋጋ ንረትን እንዲገታልን እንሻለን፡፡ ጥያቄያችንም ቀጥላል፡፡   

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት