Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሁሉንም ተጠያቂነት የሚሻው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

የሁሉንም ተጠያቂነት የሚሻው የኢትዮጵያ እግር ኳስ

ቀን:

በእግር ኳስ ለትልቅ ስኬት የበቁ አገሮች ተሞክሮ የሚያሳየው ሁሉም ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ በቀላሉ ካሰቡበት መድረስ እንዳልቻሉ ነው፡፡ ሙያተኞችም ሒደቱ መውደቅና መነሳት የሚጠይቅ፣ እጅግ አድካሚ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ትክክለኛ የአሠራር ሥርዓት እንዲሁም በዕቅድ የሚመራ፣ ዕውቀትና ክህሎት የሚጠይቅ ስለመሆኑ ጭምር ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሒደት ግን ትልቁ ቁም ነገር ከውድቀት መማር መቻልና የማሻሻያ መንገዶችን ነድፎ ጉዞን ማቃናት መቻል ጭምር እንደሆነም ያምናሉ፡፡

በቅርቡ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ ከውጤት ጋር ተያይዞ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የትችት ናዳ ሲወርድበት ቆይቷል፡፡ የትችቱ ዋነኛ መነሻ ደግሞ ቡድኑ ከወትሮው በተለየ መልኩ ዝግጅት እንዲያደርግ ነገሮች ተመቻችተውለት እንዴት ውጤታማ ሊሆን አልቻለም የሚለው በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡

በአፍሪካ ዋንጫ የተሳትፎ ታሪክ 31 ዓመታት ሲባል የነበረው የኋላ ታሪክ በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከተቀየረ ከስምንት ዓመት በኋላ፣ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ አሠልጣኝነት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ33ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በቅቷል፡፡ ቡድኑ ከውድድሩ በፊት ከምድብ ማለፍ የሚለው በዕቅድ ደረጃ የተቀመጠ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ጨምሮ የካሜሩን የአየር ፀባይ በሚገባው ልክ መለማመድ ይችል ዘንድ ውድድሩ ከመጀመሩ ከ15 ቀን በፊት ቀድሞ ወደ ካሜሩን እንዲያመራ የተደረገውም ለዚያ ሲባል መሆኑ ልብ ይሏል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቡድኑ የካሜሩን ቆይታውን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ የቡድኑን አጠቃላይ ደካማና ጠንካራ ጎን እንዲሁም በቀጣይ ዕርምት ሊወሰድባቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች ከገመገመ በኋላ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማስቀመጡ ተነግሯል፡፡

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንትና የካሜሩኑ የልዑካን ቡድን መሪ አቶ አበበ ገላጋይ፣ ግምገማው ከውጤት ጋር ተያይዞ አሁን ላይ ምክንያት መደርደሩ ብዙም ጥቅም እንደሌለው ነው የሚናገሩት፡፡

ይሁንና ኃላፊው ከውድድር በፊት ‹‹ዕቅዴ እስከዚህ ድረስ ነው›› ያለን አካል ደግሞ እንደ ተቋም ለምን ብሎ መጠየቅ ስለሚገባ፣ የብሔራዊ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ተደርጎ የነበሩ ደካማ ጠንካራ ጎኖች ተለይተው በእያንዳንዱ ጉዳይ ውይይትና ግምገማ ስለመደረጉ ጭምር ይናገራሉ፡፡

እንደ ኃላፊው ከሆነ፣ በግምገማው ወቅት የቡድኑ አጠቃላይ ክፍተት ፌዴሬሽኑ ማሟላት የሚጠበቅበትን አቅርቦት ጨምሮ በዲሲፕሊን፣ በሥነ ልቦናው፣ በአካል ብቃቱ፣ በተጫዋቾች ምርጫና በሌሎችም ማለትም ተጫዋቾች ባላቸው ችሎታና ክህሎት ታክቲክን መነሻ በማድረግ የቦታ አጠቃቀም ላይ የነበሩ ክፍተቶችና ጠንካራ ጎኖች ምን እንደሚመስሉ ተለይተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቡድኑ ላይ ከፍተኛ የሆነ የብቃት ማነስ እንደነበረበት፣ በማሳያነትም ትልልቅ ቡድኖችን አግዝፎ በመመልከት በራስ ሜዳ ላይ ለረዥም ደቂቃዎች ኳስ ይዞ መቆየትን አማራጭ አድርጎ መውሰድ የቡድኑ ተጨማሪ ክፍተት ተደርጎ በግምገማው መታየቱንም አቶ አበበ ተናግረዋል፡፡

ከምርጫ ጋር ተያይዞ እያንዳንዱ ተጫዋች ብሔራዊ ቡድኑን በሚገባው ልክ ማገልገል በሚችልበት አቋም ላይ የነበረ ነው ወይ የሚለውን ጨምሮ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይትና ግምገማ ተደርጎ ቀጣይ አቅጣጫ መቀመጡን ጭምር ኃላፊው ያስረዳሉ፡፡

34ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከአንድ ዓመት በኋላ በአይቮሪ ኮስት አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ ካፍ ወደዚያ የሚያመሩትን 24 ቡድኖች ለመለየት ደግሞ ከሁለት ወር በኋላ የየአገሮቹን ቅድመ ማጣሪያ መርሐ ግብር ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ከስምንት ዓመት በፊት በደቡብ አፍሪካ ከነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ትምህርት ወስዶ ካሜሩን ላይ ማሻሻያ ማድረግ ሲገባው ተመሳሳይ ስህተቶችን በመሥራት፣ በተለይ የዲሲፕሊን ጉዳይና በራስ ሜዳ  ለደቂቃዎች ኳስ ይዞ መቆየት ግምገማውን መነሻ ባደረገ መልኩ ከወዲሁ ዝግጅት ሊያደርግ እንደሚገባው ነው አቶ አበበ የሚናገሩት፡፡

ምክንያቱም በቀጣይ እንደ እነዚህ የመሰሉ ጥቃቅን ስህተቶች ‹‹የአሠልጣኙ ፍልስፍና›› በሚል ብቻ ሊታለፉ እንደማይገባ የሚናገሩት ኃላፊው፣ ችግሮቹ ከወዲሁ ሊያስከትሉ የሚችለውን ጉዳት ቀድሞ በመረዳት ዕርምት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ኃላፊው እግር ኳሱ የሁሉንም ተጠያቂነት የሚሻ መሆኑን በመረዳትና የዕቅዱ አካል በማድረግ የሚቀጥለው የአፍሪካ ዋንጫ ምክንያት የማይቀርብበት እንዲሆን ከወዲሁ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ቀጣዩ የመፍትሔ አቅጣጫ ስለመሆኑ ጭምር ነው የተናገሩት፡፡

ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን መገንባት የሚቻለው አንዱ በሌላው ጣት በመቀሳሰር ሳይሆን፣ የሊጉን ደረጃ ቀረብ ብሎ መፈተሽና የውድድር ጥራትን መጠበቅ ሲቻል እንደሆነ የሚናገሩት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አሠልጣኞች በዋናነት ለጊዜያዊ ውጤት በሚል ብቻ ዕድሜያቸው በገፉ ተጫዋቾች የሚኖራቸውን እምነት ያህል ለታዳጊ ወጣቶች ትኩረት በመስጠት ለሙያቸው ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ከፌዴሬሽን ኃላፊዎች ጀምሮ የክለብ አመራሮች ወደ ታች ወርደው ለሚሠሩ አሠልጣኞችና ሙያተኞች ተገቢውን ክትትልና ዕገዛ ማድረግ መቻል እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...