የታዳጊና የወጣቶች ሴቶች እግር ኳስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ የጀመረው እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ ነው፡፡ የዓለም እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ታዳጊና ወጣት ሴቶች ከ20 ዓመት በታች እንዲሁም ከ19 እና ከ17 ዓመት በታች በእግር ኳሱ ከወንዶች ባልተናነሰ በየሁለት ዓመቱ አንድ ጊዜ ውድድሮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማዘጋጀት መጀመሩ የዚህ አንዱ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
በዚሁ መሠረት ዕድሜያቸው ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች፣ ፊፋ በሚቀጥለው ዓመት በሕንድና በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚያከናውነው የዓለም ዋንጫ ውድድር ማጣሪያዎች በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በአሠልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ እና ረዳቶቹ የሚዘጋጀው የሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ የካቲት 25 ቀን 2014 ዓ.ም. የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታውን ከዑጋንዳ አቻው ጋር ካምፓላ ላይ ያደርጋል፡፡ ቡድኑ መቀመጫውን በካፍ የልህቀት ማዕከል በማድረግ ከየካቲት 11 ቀን ጀምሮ ዝግጅቱን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በሌላ በኩል ለኮስታሪካው የዓለም ዋንጫ አንድ የደርሶ መልስ ጨዋታ የሚጠበቀው ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን መቀመጫውን በጁፒተር ሆቴል አድርጎ ዝግጅቱን እያደረገ ስለመሆኑ መዘገባችን አይዘነጋም፡፡