Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ወደ ባንክነት ለመሸጋገር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማይክሮ ፋይናስ ተቋማት ወደ ባንክነት እንዲሸጋገሩ የሚያስችል መመርያ ይፋ ካደረገ በኋላ፣ የባንክ አገልግሎት ይጀምራሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተቋማት አንዱ የሆነው አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ በቅርቡ ወደ ባንክነት ለመሻገር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

የአዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው ዓለማየሁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ተቋሙ በባለሀብቶች ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ መሠረት ወደ ባንክነት ለመሸጋገር ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርቦ የባንኩን ይሁንታ በመጠባበቅ ላይ ነው፡፡ ይህ ሒደትም በቅርብ ጊዜ የሚጠናቀቅ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የወሰኑ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብሔራዊ ባንክ እንዲያሟሉ የሚጠይቃቸው እነርሱም ሊያሟላቸው የሚገቡ መሥፈርቶች እንዳሉ የገለጹት አቶ ዳምጠው፣ በዚህም መሠረት አዲስ የብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበር ከካፒታል፣ ከአክሲዮን ባለድርሻዎች ብዛት፣ ከስያሜ ጋር የሚያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ አቅርቦ ግብረ መልስ እንደተሰጠው አስረድተዋል፡፡

“ከብሔራዊ ባንክ የተሰጠውን ምላሽ መሠረት በማድረግ የሚስተካከሉ ነገሮችን በማስተካከል በቅርብ ጊዜ ውስጥ አስፈለጊውን ጉዳዮች እናጠናቅቃለን የሚለን እምነት አለን፤” ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ ይህም ሒደት ከሦስት ወራት ያልዘለለ ጊዜ እንደማይጠይቅ ተናግረዋል፡፡

የማይክሮ ፋይናስ ተቋሙ የተከፈለ ካፒታሉን 4.2 ቢሊዮን ብር፣ የተመዘገበ ካፒታሉን ደግሞ አሥር ቢሊዮን ብር ለማድረስ በጠቅላላ ጉባዔ እንደተወሰነ ያስታወሱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ ይህም ወደ ባንክነት እንዲሸጋገር የተወሰነውን ውሳኔ መሠረት በማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

ወደ ባንክነት ለሚደረገው ጉዞ አስፈላጊ ከሆኑት ጉዳዮች ውስጥ ቴክኖሎጂ አንዱ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋሙ ቅርንጫፎቹን በኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር ለማስተሳሰር፣ እንዲሁም አገልግሎቱን በቴክኖሎጂ ለማገዝ የሶፍትዌር ግዥ ፈጽሞ ተግባራዊ ማድረግ እንደ ጀመረ ተጠቁሟል፡፡ 30 ሚሊዮን ብር ወጪን የጠየቀው የሶፍትዌር ግዥ ሌሎች ባንኮች በዚህ ወቅት ቅርንጫፎቻቸውን ለማስተሳሰር የሚጠቀሙበት የኮር ባንኪንግ ሶፍትዌር እንደሆነ፣ ይህንንም በ40 ቅርንጫፎች ላይ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም አዲስ የብድርና ቁጠባ ተቋም ባለፉት ሰባት ወራት 505 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታውቆ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 2.4 ቢሊዮን ብር ቁጠባ ለመሰብሰብ አቅዶ  4.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡

በሰባት ወራት ውስጥ 37,000 የሚደርሱ አዳዲስ የቁጠባ ደንበኞችን እንዳፈራ ያስታወቀው ተቋሙ፣ ከዚህ በተጨማሪ ለ23,291 ደንበኞች 1.9 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሰጠ ተገልጿል፡፡

 

በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለመሰብሰብ ካቀደው 1.9 ቢሊዮን ብር ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር የሚያህለውን እንዳስመለሰ ተገልጾ፣ ይህም ጠቅላላ ውጭ ካለው ብድር መጠን ውስጥ፣ ሥጋት ውስጥ ያለ የብድር መጠን (Portfolio at Risk) 4.6 በመቶ እንደሆነ አቶ ዳምጠው አስረድተዋል፡፡

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በ2013 ዓ.ም. 490 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ እንዳገኘ ያስታወቁት አቶ ዳምጠው፣ በዚህ ዓመት ይህንን ትርፍ ከ600 እስከ 700 ሚሊዮን ብር ለማድረስ መታቀዱን ተናግረዋል፡፡

የማይክሮ ፋይናን ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ የቡድን ብድር እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ዳምጠው፣ በተለይም በዝቅተኛ ሥራ ለሚተዳደሩ እንዲሁም በተለያየ አደረጃጀት ለተሰባሰቡ እንስቶች እርስ በርሳቸውና በቡድን ዋስትና የሚበደሩት ብድር ይገኝበታል ብለዋል፡፡

አዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም በአዋጅ ቁጥር 40/1988 ዓ.ም. መሠረት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በማግኘት በስድስት የአክሲዮን ባለቤቶች የብድርና የቁጠባ አገልግሎት ለመስጠት እ.ኤ.አ. ጥር 27 ቀን 2000 የተቋቋመ ሲሆን፣ በተሻሻለው አዋጅ ቁጥር 626/2009 የአክሲዮን ባለቤቶቹን ቁጥር 110 አድርሶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች