Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፈሳሽ ማዳበሪያን በአማራጭ የግብርና ምርት ግብዓትነት ለመጠቀም ሙከራ እየተደረገ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለግብርና ምርቶች ምርታማነት ወሳኝ ግብዓት ይሆናል የተባለውን የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ለመጠቀም፣ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ጨምሮ የግብርና ባለድርሻ አካላት የሙከራ እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆናቸው ታወቀ፡፡

የፈሳሽ ማዳበሪያው ጠቀሜታ ከምርትና ምርታማነት አኳያ ውጤቱ ከተረጋገጠ፣ በመደበኛ የአቅርቦትና ሥርጭት ሥርዓት ውስጥ እንደሚካተት እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ኦርጋኒክ ኢንተርናሽናል ኤልኤልሲ (Organix International LLC) በተባለ የአሜሪካ ኩባንያ የቀረበውባዮጎልድ (ባዮሬድ)” የተሰኘው ኦርጋኒክ ፈሳሽ የአፈር ማዳበሪያ፣ በጊቤ የምርጥ ዘር እርሻ ልማት በተመረጡ ሰብሎች ላይ በሙከራ ደረጃ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ በቀጣይ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሥሩ ባሉት ሰፋፊ ማሳዎች ላይ ለመሞከር በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ የፈሳሽ ማዳበሪያው ከዚህ ቀደም በድንችና ፎሶሊያ ምርቶች ላይ የተሞከረ መሆኑን፣ በዚህ ወቅት ደግሞ በሽንኩርትና በስንዴ ምርቶች ላይ መሞከሩን ተናግረዋል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኦርጋኒክ ኢንተርናሽናል ኤልኤልሲ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት የሙከራ ምርቱ ለዕይታ በቅቷል፡፡ በቀጣይ የግብዓቱን ውጤታማነት ለመፈተሽ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በራሱ ሥር ባሉት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ላይ ሙከራ ካደረገ በኋላ፣ ወደ ሙሉ ትግበራ ይገባል ተብሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ አሜሪካ ከሚገኘው ኦርጋኒክ ኢንተርናሽናል ኤልኤልሲ (Organix International LLC) ድርጅት ጋር በመተባበር፣ ባዮጎልድ የተባለ ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባትና በቀጣይ በአገር ውስጥ በጋራ ለማልማት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት እንዳደረገ ይታወሳል፡፡ በቀጣይ ወደ ውል ከመገባቱ በፊት የሙከራ ሥራ እንደሚከናወን የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ለመኸር እርሻ እንዲሆን ታስቧል፡፡

አቶ ጋሻው እንዳስታወቁት የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያው በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት በኩል ውጤታማነቱ እየተመረመረ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ምርቱን ለማስተዋወቅ በተደረገው የምርት ገለጻ ወቅት ለየትኛውም የአፈር ዓይነትና የግብርና ምርት ተስማሚ እንደሆነ፣ በቀጣይም ምርቱን በአገር ውስጥ ለግብርና ግብዓትነት እንዲያገለግል የማስመዝገብ ሥራ እንደተጀመረ ተገልጿል፡፡

ፈሳሽ ማዳበሪያው ከማዳበሪያነት ባለፈ የተጎዳ መሬትንም የመጠገን ብቃት እንዳለው የአስመጪ ኩባንያው ተወካዮች የመስክ ሙከራ በተደረገበት ወቅት ገልጸዋል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በመሆኑ በተለይ ኤክስፖርት ለሚደረጉ ምርቶች ውጤታማነት፣ እንዲሁም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ተወካይ በመስክ ጉብኝቱ ወቅት እንዳስታወቁት፣ በቀጣይ በሚካሄዱ ተጨማሪ ሙከራዎች የፈሳሽ ማዳበሪያው ለምርትናምርታማነት ያለው ጠቀሜታ ከተረጋገጠ በመደበኛ አቅርቦትና ሥርጭት ሥርዓት ውስጥ ይካተታል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ስለማዳበሪያው ብቃትና ጥራት ማረጋገጫ ማቅረብ ስለሚገባ፣ በአገር ውስጥ ማዳበሪያውን የማስመዝገብ ሒደት መጀመሩ ተገልጿል፡፡

ምርቱ ከዋጋ አኳያ ምን ያህል አዋጭ ነው የሚለው በሙከራ ላይ ያለው ምርት ውጤታማነት በተግባር ከታየ በኋላ የሚወሰን መሆኑን፣ በዚህ ወቅት የተዘሩትም ሆነ በመኸር ወቅት የሚዘሩት የሰብል እህሎች ከተሰበሰቡ በኋላ የሚገኘውን ውጤት መመልከት እንደሚገባ አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ሚኒስቴር በሚያቀርበው የሥራ ዝርዝርና የፍላጎት ጥናት መሠረት በተለምዶ ጠጣር የሆነውን የአፈር ማዳበሪያ አገር ውስጥ የሚያስገባ ተቋም ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ከውጭ የተገዙ የአፈርናፈሳሽ ማዳበሪያ፣ አግሮ ኬሚካልና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች ለአርሶና አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሀብቶች ማቅረቡ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች