Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናቦዴፓ ዕጩው ሕግ ተጥሶ እንደታሰሩበት አስታወቀ

ቦዴፓ ዕጩው ሕግ ተጥሶ እንደታሰሩበት አስታወቀ

ቀን:

  • ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንዲፈቱ ጠይቋል

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፌዴራል ፖሊስና የፌደራል ዓቃቤ ሕግ፣ ‹‹ሕግ በመጣስ›› በመተከል ዞን ዳንጉር ምርጫ ክልል ፓርቲውን በመወከል ለክልል ምክር ቤት ዕጩ ሆነው የቀረቡትን አቶ ከበደ ኢተፋን ማሰራቸውን አስታወቀ፡፡

ፓርቲው በ2011 ዓ.ም. የወጣውን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን ጠቅሶ ዕጩው መታሰራቸው አግባብ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡ በፓርቲው የተጠቀሰው አዋጅ አንቀጽ 42 (1) ድንጋጌ እንደሚያስረዳው ለምርጫ የተመዘገቡ ዕጩዎች ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ፣ እጅ ከፍንጅ ካልተያዙ በስተቀር ምርጫው፣ እስከሚጠናቀቅ ድረስ በወንጀል ተጠርጥረው እንደማይያዙ ይደነግጋል፡፡ በተጨማሪም አዋጁ ዕጩዎች እጅ ከፍንጅ ሳይያዙ ሕገወጥ ድርጊት የፈጸሙ ቢሆን እንኳን፣ ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችለው የምርጫው ውጤት በቦርዱ አማካይነት በይፋ ለሕዝብ ከተገለጸ በኋላ ብቻ መሆኑን ደንግጓል፡፡

አቶ ከበደ ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም. በመተከል ዞን ዳንጉር ከተማ ላይ በፌዴራል ፖሊስ ተይዘው መታሰራቸውን የሚገልጹት የዕጩው ጠበቃ አቶ ጥበቡ ጉድሬ፣ የቀረበባቸው ክስ ከሁለት ዓመት በፊት ተፈጽሟል የተባለ ወንጀል ላይ እንደሚያጠነጥን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ ጠበቃው በተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ የካቲት 17 ቀን 2012 ዓ.ም. በዳንጉር ወረዳ በተከሰተ ግጭት ላይ ‹‹አቶ ከበደ ኢተፋ ከሌሎች ግብረ አበሮች ጋር በመሆን ሰዎች እንዲገደሉ ሲያነሳሱና ሲያስተባብሩ ነበር፤›› እንደሚል ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

የአዋጁን አንቀጽ 42 (1)ን በመጥቀስ፣ አቶ ከበደ ከባድ ወንጀል ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ እስካልተያዙ ድረስ በምርጫ ሕጉ መሠረት ሊከሰሱ እንደማይገባ በመግለጽ መቃወሚያ ማስገባታቸውን የተናገሩት አቶ ጥበቡ፣ የዓቃቤ ሕግን ምላሽ የሰማው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመተከል አካባቢ ተዘዋዋሪ ችሎት ብይን መስጠቱን አስታውቀዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ለቀረበው መቃወሚያ ምላሽ ሲሰጥ፣ ተከሳሽ የምርጫ ዕጩ ሆነው የቀረቡት የወከሉት ቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ‹‹ከተጠያቂነት ሊያስመልጣቸው በማሰብ›› እንደሆነ በመናገር ተከራክሯል፡፡ ፍርድ ቤቱም ይህንን በመያዝ መቃወሚያውን ውድቅ እንዳደረገው አቶ ጥበቡ አስረድተዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ፣ ‹‹ፌዴራል ዓቃቤ ሕግና የፌዴራል ፖሊስ ዕጩ ተወዳዳሪ በመሆኑ የተሰጠውን ያለ መከሰስ ጥሰው ነው ያሰሩብን፤›› ካሉ በኋላ፣ አቶ ከበደ መታሰራቸው ሕጋዊ አለመሆኑን ለክልሉ መንግሥት ማመልከታቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይሁንና ‹‹ጉዳዩን ያያዘው ፍትሕ ሚኒስቴር በመሆኑ ከክልሉ አቅም በላይ ነው፤›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡

ቀጥሎም ፓርቲው ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቱን የሚናገሩት ኃላፊው፣ በማመልከቻው ላይ ሕጉ ለዕጩው ያለ መከሰስ መብት እንደሚሰጥ ከመጥቀስ ባለፈ፣ ፓርቲው ሌላ ዕጩ ማቅረብ እንደማይችል መጠቀሱን አብራርተዋል፡፡

ምርጫ ቦርድም የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለፌዴራል ፖሊስና ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ እንዲሁም ለመተከል ዞን ፖሊስ በጻፈው ደብዳቤ በኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅን መሠረት ዕጩው ሊታሰሩ እንደማይገባ ከገለጸ በኋላ፣ ሕጉ ለዕጩው የሰጠው ያለ መከሰስ መብት ሊጠበቅ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

ቦርዱ በደብዳቤው፣ ‹‹በመተከል ዞን ዳንጉር ምርጫ ክልል በወቅቱ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ አልተካሄደም›› ካለ በኋላ፣ ዕጩው እጅ ከፈንጅ ያልተያዙበትን ወንጀል ቢፈጽሙ እንኳን ሕጋዊ ዕርምጃ ሊወሰድባቸው የሚችለው፣ ቦርዱ የምርጫውን ውጤት ገልጾ መሆኑን አስፍሯል፡፡ አክሎም ደብዳቤው የተጻፈላቸው አካላት የፓርቲውን አቤቱታ በሚመለከት ‹‹አፋጣኝ›› ማብራሪያ ለቦርዱ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምርጫ ቦርድ የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ፍትሕ ሚኒስቴር ሥር ለሚገኘው የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት በጻፈው ደብዳቤ፣ እንዲሁ የዕጩውን ያለመከሰስ መብት በመጥቀስ፣ አቶ ከበደ ከእስር እንዲለቀቁ ጠይቋል፡፡

አቶ ከበደ ለእስር የተዳረጉት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የምርጫ ሒደት ሲቀጥል ‹‹እንዳይወዳደሩ ለማድረግ ነው›› የሚል ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ዕጩ ስናደርገው ሆን ተብሎ ነገር ፍለጋ ካልሆነ በቀር መጠየቅ የነበረበት ድርጊቱ በተፈጸመት ጊዜ ነው፡፡ የፖለቲካ ሁኔታን ጠብቀው አይደለም መጠየቅ የነበረባቸው፤›› ብለዋል፡፡

የአቶ ከበደን ጉዳይ የያዘው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በዋለው ችሎት፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃዎች መመልከት ጀምሯል፡፡ ዓቃቤ ሕግ ቀሪ ማስረጃዎቹን እንዲያቀርብም ለመጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...