በከተሞች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለሚጠቀሙበት መንገድ፣ የአገልግሎት ክፍያ የሚከፍሉበት ሥርዓት ሊዘረጋ መሆኑ ተገለጸ።
ከተሞች ገቢያቸውን ለማሳደግ ሊሠሯቸው ይገባል ተብለው በዕቅድ ከተያዙ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነውን ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ የመጨረሻው የጥናት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ በከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የከተሞች ገቢ ሪፎርም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስተባባሪ ወ/ሪት አፀደ ኃይሉ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
የከተማ መንገድ የአገልግሎት ክፍያ ሥርዓትን ለመዘርጋት የሚደረገው ጥናት የአዳማ፣ የድሬዳዋና የባህር ዳር ከተሞችን ናሙና በመውሰድ እየተከናወነ እንደሚገኝ አክለዋል። መቀሌ ከተማን በጥናቱ ውስጥ ለማካተት ዕቅድ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ማካተት ሳይቻል ቀርቷል ብለዋል።
በጥናቱ በአጠቃላይ በከተሞች ውስጥ ያለው የተሽከርካሪዎች ምልልስና በመንገዶች ላይ የሚያሳድሩት ጫና የሚዳሰስ ሲሆን፣ መንገዶቹ ጥገናም ሆነ መልሶ መገንባት ሲያስፈልጋቸው ከተጠቃሚዎች በሚያገኙት ገቢ የሚሠሩበትን ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ መሆኑን ወ/ሪት አፀደ ገልጸዋል።
የአከፋፈል ሥርዓቱም ከሌሎች የመንገድና የማዘጋጃ ቤት ክፍያ ሥርዓቶች ጋር በተናበበ መንገድ ተግባራዊ እንዲደረግ ላለፉት ሰባት ወራት ጥናት ሲደረግ መቆየቱን የገለጹት አስተባባሪዋ፣ የመጨረሻ ሒደት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በሦስቱ ከተሞች በሚወሰደው ናሙና መሠረት አዲስ አበባን ጨምሮ በሁሉም ከተሞች፣ የከተማ መንገድ ተጠቃሚዎች ክፍያ ይጠይቃሉ ብለዋል።
«ሁሉም ተሽከርካሪዎች ተመሳሳይ ክፍያ ባይከፍሉም በጥናቱ ግኝት መሠረት በመንገዶች ላይ እንደሚኖራቸው ተፅዕኖ ክፍያ ይጠየቃሉ፤» በማለት፣ ክፍያው ሁሉንም ባለ ሞተር ተሽከርካሪዎች ብቻ እንደሚያካትት አስረድተዋል። ሞተር የሌላቸው ተሽከርካሪዎች በዚህ ሥርዓት ውስጥ አልተካተቱም ብለዋል።
ጥናቱ ሲጠናቀቅ የትኞቹ ተሽከርካሪዎች ምን ያህል መክፈል አለባቸው የሚለውም ሆነ መቼና የት ይከፍላሉ የሚለው እንደሚለይ፣ ሥርዓቱም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ወ/ሪት አፀደ ጠቁመዋል።