Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአርብቶ አደሮችን ነፍስ ያስጨነቀው የቦረና ድርቅ

የአርብቶ አደሮችን ነፍስ ያስጨነቀው የቦረና ድርቅ

ቀን:

  • በስድስት ወራት ውስጥ ከ500 ሺሕ በላይ እንስሳት ሞተዋል
  • ከ600 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ለውኃ እጥረት ተጋልጠዋል

ኡቃላ ህብሩ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግራቸው አቆራርጠው ውኃ ለመቅዳት ከያቤሎ ከተማ 185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ቦርቦር ቀበሌ ሲደርሱ፣ በእጃቸው በያዙት ቢጫ የጄሪካን ቁራጭ የሚቀዳው ውኃ የከብቶቻቸውን ሕይወት ለማዳኑ እርግጠኛ አይደሉም፡፡ አሥር ሰዎች ተቀባብለው በቁራጭ ጄሪካን ከጉድጓድ ውስጥ የሚያወጡትን ውኃ ይዘው ወደ መኖሪያ ቀበሌያቸው ራሮ ሲደርሱ ተረፉልኝ ያሏቸው 42 ከብቶች በከፊል፣ ወይም ሙሉ ለሙሉ ሞተው ይጠብቋቸው እንደሆነ ለመናገር እርግጠኛ አይደሉም፡፡

‹‹በዚህ ሳምንት ውስጥ ዝናብ ካልዘነበ ወይም ዕርዳታ ካልቀረበልን እንኳን ከብት ሰውም አይተርፍም፤›› ከሚለው ንግግራቸው በላይ ፊታቸው ላይ የሚታየው ተስፋ የመቁረጥ ስሜትና ዓይናቸው ላይ የሚታየው የቀረረ እንባ፣ አርብቶ አደርነትን የለመደች ሕይወታቸው የገባችበትን ጭንቅ አጉልተው ያሳያሉ፡፡

ኡቃላ ያጋጠማቸው ተስፋ መቁረጥ እንደ ብሶት ተናግረውት የሚወጣ፣ ዕንባቸውም ፈስሶ የሚደርቅ ዓይነት አይደለም፡፡ ዘመናቸውን በሙሉ ኑሮን ሲገፉበት የነበረው አርብቶ አደርነት የ102 ከብቶች ጌታ አድርጓቸው ሲያበቃ፣ ከስድስት ወራት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ 60 ያህሉን ገድሎባቸዋል፡፡ የቀሩት 42 ከብቶች ደግሞ መነሳት አቅቷቸው በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ ከሆኑ ሰንብተዋል፡፡

- Advertisement -

ይባሱን የካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጠዋት ላይ የተረፉትን 42 ከብቶች ወደ ማደሪያቸው ሄደው ሲጎበኟቸው እንደ ወትሮው በሰው ተደግፈው እንኳን ሊነሱ አልቻሉም፡፡ አቅም አንሷቸው ተዝለፍልፈዋል፡፡ እነዚህ ከብቶች ከሳምንት በላይ ዕድሜ እንደሌላቸው የተረዱት ኡቃላ፣ ራሳቸውን ሊያጠፉ ሲሞክሩ ቤተሰቦቻቸው እንዳስቆሟቸው ይናገራሉ፡፡

ኡቃላ በቦረና ምድር ባሳለፉት የ50 ዓመት ዕድሜ ቆይታ እንዲህ የሚያስጨንቅና ተስፋ የሚያስቆርጥ ፈተና አጋጥሟቸው እንደማያውቅ ያስረዳሉ፡፡ ላለፉት ስድስት ወራት ዝናብ በመጥፋቱ የተከሰተው ድርቅ የራሳቸውንና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወት አመሰቃቅሎታል፡፡

‹‹ያጋጠመንን ችግር ሰዎች በዓይናቸው ካላዩ ሊያምኑት የሚችሉት ዓይነት አይደለም›› በማለት በሚኖሩበት ቦረና ዞን ዳስ ወረዳ ራሮ ቀበሌ ያለውን ችግር ሲገለጹ ተስፋ መቁረጥ ፊታቸው ላይ በጉልህ ይነበብ ነበር፡፡

‹‹ብዙ የቀበሌው ነዋሪዎች ሁሉም ከብቶቻቸው ሞተው ንብረታቸው በማለቁ፣ ራሴን በራሴ እገላለሁ እያሉ ታስረው በሰው እየተጠበቁ ነው፤›› ሲሉ በድርቁ ምክንያት ራስን ለማጥፋት የተጋበዙ ብቸኛ የራሮ ቀበሌ ነዋሪ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በቦረና ዞን የተከሰተው ድርቅ ለሦስት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች በጠፋው ዝናብ ሳቢያ የመጣና የተራዘመ ነው፡፡ በዚህ የዝናብ እጥረት የተነሳ በደቡብና በቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውስጥ 6.8 ሚሊዮን ሰዎች መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) መረጃ ያሳያል፡፡ እንደ ኦቻ መረጃ በሶማሌ አሥር ዞኖች፣ በኦሮሚያ ስምንት ዞኖች፣ በደቡብ ሰባት ዞኖች፣ እንዲሁም በአዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አንድ ዞን በድምሩ 26 ዞኖች ድርቅ አጋጥሟቸዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. ከተከሰተው የከፋ ድርቅ በቅጡ ያላገገሙት እነዚህ አካባቢዎች አሁንም ለከፋ ድርቅ መጋለጣቸውን ያመላከተው የኦቻ ሪፖርት፣ ዝናብ ያልተገኘባቸው ተደጋጋሚ ወቅቶች አጋጥመውም እንኳን ቀጣዩ የዝናብ ወቅት በቂ እርጥበት እንደማይኖረው ትንበያ ማሳየቱ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጿል፡፡

ሕይወታቸውን በአርብቶ አደርነት የሚገፉትና ከነጫጭ ከብቶቻቸውና ፍየሎቻቸው የዘለለ ሕይወት የሌላቸው የቦረና ዞን ቆለኞች ግን፣ የገባውን የበልግ ወቅት እንኳን መሻገር የሚችሉ አይመስሉም፡፡ የቦረና ዞን ዋና ከተማ ከሆነችው ያቤሎ በከተማ ከ100 ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት ላይ ጠውልገው አጥንታቸው በቆዳቸው ላይ የሚታይ ብዙ ከብቶችን መመልከት፣ የሞቱት ደግሞ በየሜዳው ወድቀው መታዘብ የአዘቦት ተግባር ሆኗል፡፡

ረሃብ ያጠወለጋት እርጉዝ ላም ፀሐይ ያነደደው መሬት ላይ ሕይወቷ አልፎና በሆዷ የነበረው ጥጃ ተዘርግፎ ማየት፣ ከብቶቻቸውን ከራሳቸው ነጥለው ለማየት ለማይፈልጉ ለቦረና አርብቶ አደሮች ብቻ ሳይሆን ከመሀል አገር ለመጣ ሰውም ቢሆን ይዘገንናል፡፡

እንደ  ሚዳቋ  ያሉ የዱር እንስሳትም ከዋና የመኪና አስፓልት መንገድ ዳር ባለ ደረቅ ሜዳ ላይ አንገታቸው ቀጥኖ ውኃ ፍለጋ ሲቅበዘበዙ ማየት፣ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ እንግዳነቱ እንዳበቃ የአካባቢው ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡

የቦረና ዞን እንደ ሌሎቹ ቆላማ አካባቢዎች ሁሉ ዝናብ የሚያገኘው ከመስከረም አጋማሽ እስከ ታኅሳስ ወራት በሚቆየው የበጋ ወቅትና ከየካቲት እስከ ግንቦት ላሉት አራት ወራት በሚቆየው የበልግ ወቅት ነው፡፡ የበጋ ወቅት ለአካባቢው ሁለተኛ የዝናብ ወቅት ሲሆን፣ የበልግ ወቅት ደግሞ ከ60 እስከ 70 በመቶ የሚሆነው የዝናብ ድርሻ የሚገኝበት ዋነኛ የዝናብ ጊዜ ነው፡፡

ይሁንና 1.4 ሚሊዮን ሕዝብ የያዘው የቦረና ዞን ባለፉት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች እርጥበት አላገኘም፡፡ በዞኑ የሚገኙት 6.8 ሚሊዮን ከብቶችም በዝናብ የሚያገኙትን ውኃና ግጦሽ ማግኘት ተስኗቸዋል፡፡ ስድስት ወራት ያስቆጠረው የቦረና ዞን ድርቅ እስካሁን ዋጋቸው 7.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት ከ500 ሺሕ በላይ ከብቶችን ገድሏል፡፡ ከ600 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎችም ለውኃ እጥረት ተጋልጠዋል፡፡

አሁንም ይቀጥላል ተብሎ እየተሠጋ ያለው ድርቅ ግን የቦረና ነዋሪዎችን አቅም ጨርሶ፣ ሕይወታቸውን ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ከቷል፡፡ የቦረና አርብቶ አደሮች ባለፉት ስድስት ወራት የከብቶቻቸውን ሕይወት ለማቆየትና ራሳቸውን ለመመገብ ፍየሎቻቸውን ሲሸጡ ከርመዋል፡፡ ከድርቁ በፊት በ700 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ማዳበሪያ መኖ (ፉርሽካ) አሁን ከእጥፍ በላይ አድጎ 1,500 ብር ደርሷል፡፡ የ150 ብር አንድ እስር ሳር ደግሞ ዋጋው ወደ 270 ብር አሻቅቧል፡፡ ከተማ ተሂዶ የሚገዛውን መኖና ሳር ጭኖ ወደ ገጠር ቀበሌዎች ለማድረስ የሚከፈለው ገንዘብም ቢሆን፣ ፍየሉን ሽጦ እህል ለሸመተ ሰው የሚያስመርር መሆኑ ይነገራል፡፡

የዞኑ ነዋሪዎች እንደሚያስረዱት አንድ ፍየል በከፍተኛ ዋጋ ቢሸጥ ከሁለት ሺሕ ብር አይዘልም፡፡ ይህ ሁለት ሺሕ ብር አንድ ማዳበሪያ ፉርሽካና አንድ እስር ሳር ከመግዛት የዘለለ ፋይዳ ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ የፍየል መሸጫ ዋጋም ቢሆን ከፍ ተደርጎ የተሰላ ሆኖ እንጂ፣ ያቤሎ ከተማ ውስጥ አንድ ፍየል በ800 እና በ900 ብር መሸመት አስቸጋሪ አይደለም፡፡

በዳስ ወረዳ ቴሶ ቀሎ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት የ62 ዓመቱ አቶ ሊበን ጎሎ ገልማ፣ ላለፉት ስድት ወራት ለቤተሰቦቻቸውና ለከብቶቻቸው ምግብ ለመሸመት ሲሉ ከነበሯቸው 100 ፍየሎች ውስጥ 94 ያህሉን ሸጠዋል፡፡

ስድስት ፍየሎች ብቻ እስኪቀራቸው ድረስ ያላቸውን እየሸጡ ከብቶቻቸውን ለማኖር የማሰኑት አቶ ሊበን፣ የፍየል ሀብታቸው ተመናምኖ እንኳን ከብቶቻቸው ሙሉ ለሙሉ ከመሞት አልተረፉም፡፡ ከነበሯቸው 75 ከብቶች ውስጥ 60 ያህሉ ሞተው አሁን የቀሯቸው በሰው ድጋፍ የሚንቀሳቀሱ 15 ከብቶች ብቻ መሆናቸውን ዕንባ እየተናነቃቸው ተናግረዋል፡፡

አሁን ከብት ሽጦ ገንዘብ ለመያዝ እንኳን የማያስችል ጊዜ ከአቶ ሊበን ፊት ተጋርጧል፡፡ ከዚህ ቀደም 20 እና 30 ሺሕ ብር ሲሸጡ የነበሩት የቦረና ከብቶች፣ አሁን  በሰው ተደግፈው ገበያ ሲቀርቡ መሸጫ ዋጋቸው ከ700 ብር እንደማይበልጥ ያስረዳሉ፡፡

አቶ ሊበን 60 ዓመት በተሻገረው ዕድሜያቸው ውስጥ ይህኛው ድርቅ የከፋው ስለመሆኑ ምክንያቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ተከስተው የነበሩ የድርቅ ጊዜያት ዝናብ ከሰማይ ባይታይም፣ በምድር ውኃና የግጦሽ ሳር የማይታጣባቸው እንደነበሩ ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ባስ ቢልም በሁሉም የቦረና አካባቢዎች ድርቁ ስለማይከፋ፣ አንዱ ቀበሌ ድርቅ የበረታ ድርቅ ሲከሰት ግጦሽ ፍለጋ ወደ ሌላ ቀበሌ መሰማራት የክፉ ቀን ማምለጫ መንገድ ነበር፡፡

አሁን ግን ይህንን ዘዴ መተግበር የሚቻል አልሆነም፡፡ በቦረና ዞን ያሉት 13ቱም ወረዳዎች ያጋጠማቸው ድርቅ ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የሚገኝና አስከፊ መሆኑን የቦረና ዞን አስተዳደር መረጃ ይጠቁማል፡፡

አቶ ሊበንም ይህንን እውነታ ሲያረጋግጡ፣ ‹‹ተሴቀሎ ቀበሌ ድርቁ ሲብስብኝ ከብቶቼን ይዤ ውኃና ሳር ለማግኘት መታርባ ቀበሌ ሄድኩ፣ እዚያም ድርቅ ነው፡፡ አሁን ወደ ተሴቀሎ በመመለስ የቀሩትን ከብቶቼን ይዤ ድርቅ መሀል ተቀምጫለሁ፤›› በማለት የድርቁን መፈናፈኛ አሳጪነት ገልጸዋል፡፡

ሕይወታቸውን በሙሉ በአርብቶ አደርነት ያሳለፉት አቶ ሊበን፣ ከዚህ ቀደም ‹‹ሕይወታችንን የኖርነው ለከብቶቻችን ነው›› ባይ ናቸው፡፡ አሁን ድርቁ ከብቶቻቸውን አንድ በአንድ ሲያረግፍ ቀጣይ የሕይወት ምዕራፋቸው ምን እንደሚሆን ግራ እንደገባቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹ምንም ተስፋ አይታየንም፣ ከብቶቻችን ሞተዋል፣ ጉልበታችን ተሟጧል፣ ሳር እንዳንገዛ ፍየሎቻችን አልቀዋል፣ እኛ ራሳችን እንዳናልቅ ነው ሥጋታችን፤›› በማለት ሲቃ በያዘው ድምፀት ብሶትና ተስፋ መቁረጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በዳስ ወረዳ ቦርቦር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ደኩሱሴ ድርቁ የእንስሳት ሀብታቸውን ሙሉ ለሙሉ ከቀማቸው የቦረና ነዋሪዎች ውስጥ አንዷ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ደኩሱሴ ከ40 በላይ ከብትና ከ50 የሚልቁ ፍየሎች ባለቤት ነበሩ፡፡ አሁን የአንዳቸውም ባለቤት አይደሉም፡፡ ፍየሎቹ ከብቶችን ለመቀለብ ቢሸጡም ሁሉም ከብቶች ከሞት አልተረፉም፡፡

‹‹ከሁለቱ አንዱ እንኳን አልተረፈኝም፤›› በማለት ሐዘናቸውን የሚገልጹት ወ/ሮ ደኩሱሴ፣ አሁን መኖሪያቸው ከተማ የሚገኙት ልጆቻቸው ዘንድ ነው፡፡ ካለፉት ሦስት ወራት ወዲህ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑ ሁለት ልጆቻቸው የሚያደርጉላቸው ድጋፍ ሕይወታቸውን አስቀጥሏል፡፡

ወ/ሮ ደኩሱሴ፣ ‹‹ከብቶቼ በሙሉ ከሞቱ በኋላ ሕይወቴ እንዴት እንደሚቀጥል ፈጣሪ ብቻ ነው የሚያውቀው፤›› በማለት ሐዘናቸውን ቢገልጹም፣ ከተማ ዘመድ የሌላቸው ሌሎች የገጠር ነዋሪዎች ከዚህ የባሰ ችግር ውስጥ እንዳሉ ያስረዳሉ፡፡ ከተማ መጠጊያ ያላቸው ሰዎች ከገጠር ሲወጡ፣ ከተማ ዘመድ አዝማድ የሌላቸው ከብቶቻቸው በሙሉ ካለቁ በኋላ ገጠር ውስጥ በረሃብ ከመቀጣት ውጪ አማራጭ አላገኙም፡፡ ከዚህም ባስ ሲል ምንም ምንም እንኳን ‹‹ሕይወታቸው ያለፈው በበሽታ ነው›› ቢባልም፣ ረሃብ  የገደላቸው የመንደሩ ነዋሪዎች እንዳሉ ወ/ሮ ደኩሱሴ ተናግረዋል፡፡

‹‹አሁን ጭንቀትና ጥያቄያችን ስለጠፋው ሀብታችን ወይም ስለሞቱት ከብቶቻችን  አይደለም፡፡ ለሕይወታችን ነው እየሠጋን ያለነው፡፡ መንግሥት ካለ ይድረስልን፣ አደራ ሕይወታችንን… ሲሉ ወይዘሮዋ ጭንቃቸውን አጋርተዋል፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን ‹‹በረሃብ ሰው ሞቷል›› የሚለውን ሐሳብ አይቀበሉትም፡፡ ባለሥልጣናቱ ድርቁ ባስከተለው ረሃብ የተነሳ የሰው ሕይወት አለማለፉን የሚናገሩት አበክረው ነው፡፡ በጥር ወር መጨረሻ 2014 ዓ.ም. በድርቅ ክፉኛ የተጎዳውን የቦረና ዞን የጎበኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ የካቲት 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ በድርቁ ምክንያት እስካሁን የአንድም ሰው ሕይወት አለማለፉን ለሕዝብ ተወካዮች ተናግረው ነበር፡፡

የቦረና ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩም ይህንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ዋና አስተዳዳሪው እስካሁን በረሃብ የሰው ሕይወት አለማለፉን ገልጸው፣ በዞኑ ያለው ሁኔታ በዚሁ ከቀጠለ ግን የቦረና አርብቶ አደሮች ከከብቶቻቸው የተሻለ ዕጣ እንደማይገጥማቸው ገልጸዋል፡፡

አቶ ጃርሶ እንደሚሉት እስካሁን 108 የቦረና ነዋሪዎች በምግብ እጥረት የተነሳ የሞት አፋፍ ላይ ከደረሱ በኋላ፣ በጤና ጣቢያና በሆስፒታሎች በተደረገላቸው ዕገዛ ተርፈዋል፡፡ አሁንም ግን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው የቦረና ሕፃናት፣ እናቶችና በዕድሜ የገፉ ሰዎች የከፋ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡

ዋና አስተዳዳሪው፣ ‹‹ዝግጅት ስላደረግን እንጂ ስድስት ወራት ሙሉ ሰው ሳይሞት ድርቅን ማስተናገድ በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› ቢሉም የቦረና አርብቶ አደሮች ቅድመ ዝግጅቱ ያመጣላቸው ዕርዳታና ድጋፍ እንደሌለ ይገልጻሉ፡፡

ከብቶቻቸውን ሙሉ ለሙሉ ለማጣት ጫፍ ላይ የደረሱት አቶ ኡቃላ ህብሩ የዚህ ምስክር ናቸው፡፡ አቶ ኡቃላ የሚኖሩበት ቃስ ወረዳን በሚያጎራብቱ ሌሎች አካባቢዎች ዕርዳታ ቢቀርብም፣ በቃስ ወረዳ ውስጥ የሚገኘው ራሮ ቀበሌ ምንም ድጋፍ እንዳላየ ያስረዳሉ፡፡ በአካባቢው በሰው ጉልበት የተቆፈረ የውኃ ጉድጓድ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ጉድጓዱ ብቻ እንጂ ውኃው የለም፡፡

ለሰውም ሆነ ለእንስሳት የሚሆን የመጠጥ ውኃ በሌለበት ራሮ ቀበሌ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውሰጥ ዝናብ ካልዘነበ ወይም ዕርዳታ ካልቀረበ፣ እንኳን ከብት ሰው እንደማይተርፍ ተናግረዋል፡፡

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ በቦረና ዞን ካሉት 1.4 ሚሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ 526 ሺሕ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች የመንግሥትን እጅ የሚጠብቁ መሆናቸውን ገልጸው፣ ወደ ክልሉ የሚደርሰው ዕርዳታ በአንፃሩ በቂ እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡ በዞኑ ድርቅ እንደሚከሰት በመታወቁ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ዝግጅት መደረጉን የሚያስረዱት አቶ ጃርሶ፣ በተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ አለመገኘቱ ድርቁንና ጉዳቱን እንዳባባሰው ያስረዳሉ፡፡

በስድስት ወራት ቆይታው የቦረና አርብቶ አደሮችን ሕይወት ጨለማ ያለበሰው ድርቅ፣ ከዚህም በላይ ክንዱን በቦረና ነዋሪዎች ላይ ሊያሳርፍ ይችላል፡፡ የኢትዮጵያ የሚቲሪዎሎጂ ኢንስቲትዩት አሁን የገባውን የበልግ ወቅት የተመለከተ ትንበያው እንደሚያሳያው የቦረና፣ የጉጂና የባሌ ቆላማ ዞኖች የሚያገኙት ዝናብ መደበኛና ከመደበኛ በታች የሆነ ነው፡፡ ይህም ቢሆን በልጉ ከሚቆይበት አራት ወራት ጊዜ ውስጥ በሁለቱ ወራት አይዘንብም፡፡

ይህ ትንበያ ዕርዳታ ፍለጋ በባለሀብቶችና በተቋማት ደጅ እየባዘኑ ላሉት የቦረና ዞን አስተዳዳሪዎች አስፈሪ እንደሆነ አቶ ጃርሶ ይናገራሉ፡፡ አሁን በዞኑ ውስጥ 481 ሺሕ ከብቶች በሞት አፋፍ ላይ በመሆናቸው የሚንቀሳቀሱት በሰው ድጋፍ ነው፡፡ ዋና አስተዳዳሪው፣ ‹‹በሁለትና በሦስት ሳምንት ውስጥ ካልዘነበ እነዚህ ከብቶች እንደሞቱ ነው የምንቆርጠው፣ አይተርፉም፤›› በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

የድርቁ አዝማሚያ እየከፋ እየሄደ እንደሆነ የሚናገሩት ዋና አስተዳዳሪው፣ ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ ተጨማሪ ከ900 ሺሕ በላይ ከብቶች እንደሚሞቱ ተናግረዋል፡፡

ድርቁ ከብቶቻቸውን የጎዳባቸው የቦረና አርብቶ አደር

የውኃ እጥረት ግማሽ ሚሊዮን ከብቶችን በቀጠፈበት የቦረና ምድር፣ ዝናብ ከምንም በላይ የሚጠበቅ ክስተት የመሆኑን ያህል መምጣቱም በዚያው ልክ ፍርኃትን አጭሯል፡፡ አቶ ጃርሶ እንደሚያስረዱት የቦረና ከብቶች ቆዳቸው በመሳሳቱ ዝናብ ቢዘንብ መቋቋም አይችሉም፡፡ ድርቁ ሰውነታቸውን አመንምኖ አቅም ስላሳጣቸውም ዝናቡ የሚያስከትለው ጭቃ ቢጥላቸው ደግመው አይነሱም፡፡

ዋና አስተዳዳሪው፣ ‹‹ባለፈው ሰሞን ያልተጠበቀ ዝናብ ሌሊት ዘንቦ በማደሩ 76 ሺሕ ከብቶች ሞተዋል፡፡ አሁንም ለተከታታይ አምስት ቀናት ቢዘንብ የሚሞቱ ከብቶች ቁጥር በስንት እጥፍ እንደሚጨምር መገመት ይቻላል፤›› ሲሉ፣ የዝናብ ጉዳይ የዞኑ አስተዳደሮች ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አስተዳዳሪዎቹ  ሥጋታቸው ከከብቶቹና ከአርብቶ አደሮቹም አልፏል፡፡ በዞኑ ውስጥ በሚገኘው የቦረና ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የሚገኙ የዱር እንስሳት ጉዳይ ሌላኛው ራስ ምታታቸው ነው፡፡

‹‹ከብት ባለቤት አለው፡፡ ከዚያ ካለፈም መንግሥት ዕርዳታ ያቀርባል፡፡ እኛን በጣም ያሳሰበን አንዱ ጉዳይ ዕርዳታ ያላገኙ የዱር እንስሳት ሁኔታ ነው፤›› የሚሉት ዋና አስተዳዳሪው፣ የዱር  እንስሳቱ  በየሜዳው  እየወደቁ  መሆኑን ተናግዋል፡፡

ከጥቅምት 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተወጥሮ የከረመው የፌዴራል  መንግሥት፣ ወደ አዲስ አበባ እየተቃረበ የነበረውን ሕወሓት ወደ ኋላ ከገፋ በኋላ ከጥቅምት አንስቶ የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት ወደ ነባር እንቅስቃሴው የተመለሰ መስሏል፡፡

ባለፈው ሳምንት መጀመርያ በፓርላማ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ድርቅ ወደ ተከሰተባቸው አካባቢዎች 750 ሺሕ ኩንታል የዕለት ደራሽ ምግብ፣ 259 ቦቴ ውኃ፣ እንዲሁም የከብት መኖ፣ የሕፃናት ምግብና ክትባት መላኩን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሦስት ቀናት በኋላ የካቲት 18 ቀን 2014 ዓ.ም.፣ ‹‹ድርቅ በተፈጥሮ ቢመጣም ረሃብ ግን የስንፍናችን ውጤት ነው፤›› በሚል ርዕስ ባስተላለፉት ወቅታዊ  መልዕክት፣ ‹‹በድርቅ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ የሶማሌና የቦረና አርብቶ አደር ወገኖቻችን አፋጣኝ ዕርዳታችንን ይሻሉ፤›› ካሉ በኋላ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚገኙ ከብቶች በመኖና በውኃ እጥረት እየረገፉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ ረሃብን ማስከተሉን በመልዕክታቸው ያስታወቁት  ዓብይ (ዶ/ር)፣ በረሃቡ ምክንያት ሕፃናትና አረጋውያንን ሕይወታቸውን እያጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ክረምቱ እስኪደርስላቸው እንጠብቅ ከተባለ ብዙ ወገኖቻችንን እናጣለን፤›› በማለት፣ ለድርቅና ለረሃብ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከሚደረገው ርብርብ ባሻገር አፋጣኝ ምላሽ ለሚሹ ወገኖች ዕርዳታ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የዝናብ ማጣት ከብቶቻቸውን ያሳጣቸው የቦረና አርብቶ አደሮች፣ የዝናብ መምጣትን በተስፋ እየጠበቁ መዝነቡም የጠወለጉ ከብቶቻቸውን እንዳይገድል ፈርተዋል፡፡ እንደ ቤተሰብ አካል የሚመለከቷቸውን ከብቶች በመንፈቅ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ያጡት ሦስት ሺሕ የቦረና አርብቶ አደሮች፣ ዘመናቸውን ያሳለፉበትን የአርብቶ አደርነት ሕይወት እንዴት እንደሚቀጥሉት ግራ ገብቷቸዋል፡፡ ከብቶቻቸውን በእጃቸው እየደገፉ የሚያበሉ አርብቶ አደሮችም ቢሆኑ፣ ተሸጠው ያለቁ ፍየሎቻቸውን እያሰቡ ከብቶቻቸውንም  የማጣት ሥጋት ወሯቸው ተቀምጠዋል፡፡

እንደ አቶ ኡቃላ ህብሩ ያሉት ደግሞ ከብቶቻቸው ሲያልቁ ቁጭ ብሎ ከማየት ይልቅ ራስን ማጥፋት የሚሻል ስለመሰላቸው፣ በቤተሰብ ጥበቃ ሥር ከዚህም የከፋ የሚመስለውን መጪው ጊዜ እየጠበቁ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...