- በአገራችን ፖለቲካ ላይ ራሳችን ተወያይተን በጋራ የተስማማንበትን ለመወሰን መዘጋጀታችን ለምን እንደዚህ ተቃውሞ እንዳስነሳ ሊገባኝ አልቻለም?
- ክቡር ሚኒስትር በአገራችን ጉዳይ ራሳችን ተወያይተን ለመወሰን ማቀዳችን ትክክልና ተገቢ ቢሆንም፣ ይህንን ማድረግ የምንችልበት ሁኔታ ላይ ያለን አልመሰለኝም።
- ለምን? ማን ይከለክለናል?
- እኛ ለማካሄድ ላሰብነው አገራዊ ምክክር ከእኛ በላይ እየተሰናዱ የሚገኙትን ካስተዋሉ የምክክሩ ውጤት የእኛ ፍላጎት ይሆናል ለማለት ያስቸግራል።
- ከእኛ ውጪ ማን እየተሰናዳ ነው?
- አሜሪካኖቹ ሰሞኑን ያደረጉትን አልሰሙም?
- ምን አደረጉ?
- ከተሾሙ አንድ ዓመት ያልሞላቸውን የአዲስ አበባ አምባሳደር አንስተው ሌላ ተክተዋል።
- ይህንን ማድረጋቸው ምን ችግር አለው? እኛስ አዳዲስ አምባሳደሮችን እየቀየርን አይደለም እንዴ?
- ልክ ነው፣ እነሱ ግን በተነሱት አምባሳደር ምትክ አምባሳደር አልሾሙም።
- ምንድነው ታዲያ የሾሙት?
- ጉዳይ አስፈጻሚ፡፡
- ጉዳይ አስፈጻሚ? ምን ማለት ነው?
- ጉዳይ አስፈጻሚ ከአምባሳደር በታች ያለ እርክን ነው፣ አገሮች ከአገሮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት መሻከር ለመግለጽ ሲፈልጉ ኤምባሲያቸውን በጉዳይ አስፈጻሚ እንዲመራ ማድረግ የለመዱት ነው።
- እና አሜሪካኖቹ ከእኛ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያላሉ ነው ማለት ነው?
- አይደለም፣ አሜሪካኖቹ አምባሳደር አንስተው ጉዳይ አስፈጻሚ ከመደቡ ትርጉሙ ሌላ ነው።
- ምንድነው?
- መፈጸም የሚፈልጉት ጉዳይ አለ ማለት ነው፣ ይህንን ደግሞ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ላይ አድርገውታል።
- መቼ?
- ምርጫ 97ን ተከትሎ የተፈጠረውን የፖለቲካ ውጥረት በሚፈልጉት መንገድ የፈቱት ጉዳይ አስፈጻሚ በመላክ ነው።
- ያኔ የተላኩትን ጉዳይ አስፈጻሚ አስታወስኳቸው፣ ወ/ሮ ቪኪ ሃድልስተን መሰለኝ ስማቸው ካልተሳሳትኩ አይደል?
- ትክክል፣ እሳቸው ዛሬ ጡረታ ላይ ሆነውም ቀጥለውበታል፣ በቅርቡ በአገራችን ጉዳይ ውይይት ሲያደርጉ በተለቀቀው ቪዲዮ ውስጥ ከሚታዩት መካከል አንዷ ሴትየዋ ናቸው።
- እና አሁን አዲስ የተመደቡት ጉዳይ አስፈጻሚ ምን የሚያደርጉ ይመስልሃል?
- ጉዳይ ከማስፈጸም ውጪ ሌላ ተልዕኮ አይኖራቸውም።
- እኮ የምን ጉዳይ?
- ጉዳዩን የሚያውቁት አስፈጻሚዋ ናቸው፣ ነገር ግን ከሁለት አንዱን ነው ሊያስፈጽሙ የሚችሉት።
- ከሁለት አንዱ ማለት?
- ወይ የቀድሞውን ነው፣ ካልሆነም አዲስ ጉዳይ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ የቴሌቪዥኑን ቻናል እየቀያየሩ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ስለተከሰተው ጦርነት መረጃዎች እየተከታተሉና አንዳንድ ታሪኮችንም ለባለቤታቸው እየተረኩላቸው ነው]
- አይ ሩሲያ… እንዲያው ዝም ብዬ ሳስበው አገሬ ትመስለኛለች።
- ማን? ሩሲያ?
- አዎ፣ ለነጮች አልበገር ባይነቷ ከኢትዮጵያ ጋር ይመሳሰልብኛል፡፡
- ሩሲያውያን ነጮች አይደሉም እንዴ?
- እሱማ ናቸው… ለኃያላኖቹ ማለቴ ነው።
- እንዴ ሩሲያ ከኃያላኖቹ አንዷ አይደለችም እንዴ?
- እንዲያው ለነገሩ እንጂ… ኃያልማ ናት፡፡
- እንዲያው ለነገሩ ማለት?
- አልበገር ባይነቷን ማለቴ ነው፣ በቃ በአውሮፓ ምድር የበቀለች ኢትዮጵያ ትመስለኛለች።
- የተወረረችውስ?
- ተወራ አታውቅም፣ መቼ ተወረረች?
- ወዲህ ነው… ዩክሬንን ማለቴ ነው፡፡
- እ… ስለዩክሬን እንኳ ብዙ አላውቅም፡፡
- ምን? አንዴት?
- ያው የዓለም ኃያላን ሽኩቻ ድንገት የወደቀባት አገር እንጂ፣ ምንም የምታውቅ አይመስለኝም፣ ብቻ ብዙም ስለዩክሬን አላውቅም።
- እንዴት?
- እንዴት ማለት ምንድነው? ያው ብዙም የምትታወቅ አገር አይደለችም፣ ከእኛም ጋር ብዙ ግንኙነት የላትም።
- ዩክሬን?
- አዎ፡፡
- እናንተ አትወቋት እንጂ ዩክሬንማ የችግራችን ደራሽ ነች፡፡
- እንዴት ሆኖ?
- ከዩክሬን አይደለም እንዴ እየገዛችሁ የምታቀርቡልን?
- ምን?
- ስንዴው ብትል… ዘይቱ ምን የማትልክልን አለ? ከዚያ አይደል እንዴ የምትገዙት?
- በጨረታ ስለሚገዛ ከየት አገር እንደሚገባ አላውቅም፣ እንዳልሽው ከዩክሬንም ሊሆን ይችላል።
- ሊሆን ይችላል?
- አዎ፣ ሊሆን ይችላል፡፡
- ናት እንጂ፣ ዩክሬን ናት ስልህ? ስንዴና ዘይት ብቻ መሰለህ እንዴ?
- እ…?
- በገበያው ያለው የፍጆታ ዕቃ በተለይ ምግብ ነገሮች ከዚያ ነው የሚመጡት፡፡
- አትቀልጂ እንጂ?
- እውነት ስልህ? ለምሳሌ የዩክሬን ምስር ታውቃለህ?
- ምስር?
- አዎ፣ እንዴት ጥራት ያለው መሰለህ? አንድ ቅንጣት ልቃሚ የለውም፡፡
- ወይ ጉድ፣ ምስር ከዩክሬን?
- ምስር ብቻ መሰለህ እንዴ?
- እ…?
- ለምሳሌ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ገበያውን ሞልቶት የነበረው የዩክሬን እንቁላል ነበር።
- እንቁላል?
- አዎ፣ አሁን ግን ሊጠፋ ይችላል፡፡
- ለምን? በጦርነቱ መጀመር?
- በሁለቱም።
- ሌላ ምን ተጀመረ?
- እዚህ ዓብይ ፆም ተጀምሯላ፡፡
- ወይ ጉድ… እንቁላል ከዩክሬን?
- አለማወቅህ ይገርማል፣ የተገላቢጦሽ ከሆነ እኮ ቆየ፡፡
- ምኑ ነው የተገላቢጦሽ?
- የእንቁላል ነገር ነዋ!
- እንዴት?
- የእኛ በእግሩ ይሄዳል ስንል፣ የዩክሬኑ በእግሩ መጣ!