Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፋይናንስ ተቋማት የሳይበር ጥቃት መከላከል ስለሚችሉበት ሁኔታ ምክረ ሐሳብ ተሰጠ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም ደረጃ እጅግ አሳሳቢ እየሆኑ ከሚገኙ አደጋዎች መካከል የሳይበር ጥቃት ከመጀመርያዎቹ ረድፍ ይጠቀሳል፡፡ በተለይ እያደገ የመጣው ከቴክኖሎጂ ጋር የተሳሰረ አገልግሎት የሳይበር ጥቃቱን መጠን እየጨመረው መምጣቱ ይታመናል፡፡ ከዚህ በኋላ የሳይበር ጥቃት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ከሌሎች አደጋዎች የቀደመ ሊሆን እንደሚችልም እየተገለጸ ነው፡፡

የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበርና አፍሮ ኤዥያን ኢንሹራንስ አገልግሎት ሊሚትድ በጋራ ባዘጋጁት ዓለም አቀፍ የሳይበር ደኅንነት ኢንሹራንስ ፎረም ላይ የተገኙ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር፣ ‹‹ዲጂታላይዜሽን ሁልጊዜ ዕድገቱ እየጨመረ የሚሄድ እንደመሆኑ፣ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችና የሥጋት ተጋላጭነቶች የማይቀሩ በመሆኑ ጥቃቶቹን መቆጣጠር መሠረታዊ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤›› ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃም ሆነ በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት ትልቅ ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ደግሞ አኃዛዊ መረጃዎች የሚያመላክቱ ሲሆን፣ በተለይ የዚህ ጥቃት ሰለባ በመሆን ደግሞ የፋይናንስ ተቋማት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛሉ፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ዶክተር ሹመቴ ግዛው ገለጻ፣ በኢትዮጵያ እየደረሰ ያለው የሳይበር ጥቃት ከዓመት ዓመት እየጨመረ ነው፡፡ በ2014 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ብቻ ከ3,400 የሳይበር ጥቃቶች መሰንዘራቸውን፣ ከእነዚህ ጥቃቶች አብዛኞቹ በፋይናንስ ተቋማት ላይ የተሰነዘሩ ናቸው፡፡

የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያ ምን ያህል እየጨመረና አሳሳቢ ለመሆኑ ማመላከቻ የሚሆነው፣ በ2014 በጀት ዓመት በግማሽ ዓመት ውስጥ የተመዘገበው ጥቃት ከ2013 ዓ.ም. ሙሉ ዓመት ከደረሰው በ150 በመቶ የሚበልጥ መሆኑን ዳይሬክተሩ መግለጻቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኃይለ ማርያም አሰፋም፣ የሳይበር ጥቃት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመድረሱ ጠቁመው፣ አብዛኛዎቹ ጥቃቶች በፋይናንስ ተቋማት ላይ የደረሱ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2021 በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካ ከደረሱ ጥቃቶች ውስጥ 70 በመቶ በባንኮች ላይ፣ 16 በመቶ ደግሞ በኢንሹራንስ ኩባንዎች እንዲሁም 14 በመቶው  በሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ላይ የደረሰ መሆኑም አሳሳቢ እንደሆነ አቶ ኃይለ ማርያም ገልጸዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት ምን ያህል አሥጊና ኢኮኖሚውን በእጅጉ ስለመጉዳቱ አንድ ማሳያ የሚሆነው፣ ከዓለም ጠቅላላ ምርት አንድ በመቶ የሚሆነው ያህል የሳይበር ጥቃት የሚደርስበት መሆኑን የገለጹት የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ያሬድ ሞላ፣ በዓመት ወደ አንድ ትሪሊዮን ዶላር የሚሆን ገንዘብ በሳይበር ጥቃት ይደርስበታል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የፋይናንስ ተቋማት ከገቢያቸው ወደ ዘጠኝ በመቶ የሚሆነው ወጪያቸው ከዚሁ ከሳይበር ደኅንነት ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች የሚውል መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር የማርኬቲንግ ገበያ ዳይሬክተር አቶ ፍቅሩ ፀጋዬ በበኩላቸው፣ ‹‹የዓለም ሥጋት የሆነውን የሳይበር ጥቃት ዘንድሮ ከወረርሽኝ ቀጥሎ ትልቁ አደጋ ተብሎ በዓለም ደረጃ የተለየ ነው፤›› ብለውታል፡፡

ከዚህ ቀደም በመሬት መንቀጥቀጥና በጎርፍ ሱናሚ የዓለማችን አደጋ ተብሎ ከሚገለጸው ሥጋትና ውድመት በላይ አሁን ላይ የሳይበር ጥቃት ትልቁ ሥጋት ወደ መሆን ተሸጋግሯል ያሉት አቶ ፍቅሩ፣ ወደፊትም የመጀመርያው የዓለማችን አደጋ ይሆናል ተብሎ የሚታሰብ በመሆኑ፣ በዚህ ዙሪያ ብዙ መሠራት እንደሚኖርበት አመልክተዋል፡፡

ብዙ አሠራሮች ኢንፎርሜሽን ቴክሎሎጂ ላይ እየተመሠረቱ በመሆኑም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ወደፊት ለመሄድ መራመድ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ይህንን አደጋ ለመታደግም አንዱ መንገድ የሳይበር ጥቃት የመድን ሽፋን መስጠት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ የጠለፋ መድን አክሲዮን ማኅበር ይህንን ጉዳይ በማሰብ የዕለቱን መድረክ ያዘጋጀ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አንፃር የሳይበር ጥቃት ለምን በዚህን ያህል ደረጃ እየጨመረ መጣ ለሚለው ጉዳይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አገልግሎት የዲቪዥን ኃላፊ አቶ ሃኒባል ለማ፣ ‹‹ካለው የፖለቲካና የማኅበራዊ ሁነት አንፃር በተለያዩ ጉዳዮች ሊጨምርና ሊቀንስ ይችላል፤›› ይላሉ፡፡

ከዚህ በፊት የነበረን ልምድ በምሳሌነት የጠቀሱት አቶ ሃኒባል፣ የኢትዮጵያ የመጀመርያና የሁለተኛ ዙር የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ስታካሂድ የሳይበር ጥቃቱ ይጨምር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በዚያን ወቅት ይደረግ በነበረው ጥቃት ላማ የተደረጉት በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ከዚህ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የሚታሰቡ የመንግሥትና የግል ተቋማት እንደነበሩ ያመለክታሉ፡፡  

በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች ወቅታዊ የፖለቲካና ተያያዥ የሆኑ ትኩሳቶችን ተከትሎ የሚፈጸም ስለመሆኑ የሚያመለክተው የአቶ ሃኒባል ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል በሕግ ማስከበር የህልውና ዘመቻና በመሳሰሉ ወቅቶች ተመሳሳይ ጥቃቶች ይታዩ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ ጥቃቶች ከገንዘብ አንፃር ምን ያህል ጥፋት አድርሰዋል ለሚለው ጥያቄ አቶ ሃኒባል፣ በገንዘብ ደረጃ የጥቃቱን መጠን የሚገልጽ መረጃ ባይኖርም፣ እስካሁን በኢትዮጵያ ላይ የደረሱ የሳይበር ጥቃቶች ግን በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመሩ መምጣት ትልቅ ሥጋት ነው ይላሉ፡፡

ከ2012 ዓ.ም. ወደ 2013 ዓ.ም. ስንገባ የነበረው ጥቃት 150 በመቶ መጨመሩን የገለጹት አቶ ሃኒባል፣ አሁን በ2014 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የደረሰው የሳይበር ጥቃት፣ ዓምና በሙሉ ዓመቱ ከተፈጸመው ጥቃት ወይም ምላሽ ከተሰጠባቸው ጥቃት አንፃር ሲታይ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የ2014 ጥቃት ከ200 በመቶ በላይ ሊጨምር የሚችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የጥቃት መጠኑ በጣም እየጨመረ የመጣበት ምክንያት ደግሞ የተለያየ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ እንደ አገር ያላትን ሀብቶች ዲጂታላይዝድ የማድረግና ቴክኖሎጂ የመጠቀም ፍላጎቱ እየጨመረ መምጣቱ አንደኛው ምክንያት ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶች ምንጭ ከየት ነው ማለት ይቻላል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ሃኒባል፣ ‹‹ይህንን ለመግለጽ ከባድ ሊሆን ይችላል፣ እከሌ የሚባል ጥቃት ከዚህ ቦታ መጣ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ካለው ሁኔታ በመነሳት ምን ዓይነት ጥቃቶች ይፈጸማሉ? ምን ዓይነት ተቋማት ተጠቁ? ሲባል ግን ፍላጎቱን ወይም ጥቃቱን እንዲሰነዝሩ ምክንያት የሆናቸውን ነገር ማየት ይቻላል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ በመነሳት ከዚህ ጥቃቶች ጀርባ እነማን ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው ነገር እንዳለ የሚገመቱ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህም ራሱ ከየት መነጨ? እንዴት ሆነ? የሚለው ኮስት አንሲደንስ ሥራዎች መሠራት አለባቸው፤›› የሚሉት አቶ ሃኒባል፣ እንዲህ ያለውን ጥያቄ ጠቅለል አድርጎ ለመመለስ ግን ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው አካላት ጋር የተሳሰረ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ሁልጊዜ እንዲህ ይሆናል ማለት እንዳልሆነና አንዳንድ ጊዜ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፣ በመሳሳትም አንዳንድ ጥቃቶች ሊፈጸሙ እንደሚችሉም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡  

ይህም የሚሆነው ተቋማት ጋር ባሉ የአሠራር ሥርዓቶች በሠራተኞች የሚፈጸሙ ሆነው የሚገኙ ናቸው፡፡ እንደ ምሳሌ የጠቀሱትም በቅርቡ የሚዲያ ተቋማት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት በሶሻል ሚዲያ አካውንታቸውን እንደ ዲጂታል አሴት ወስደው መከላከል ባለመቻላቸውና ትክክለኛ የአሠራር ሥርዓት ባለመከተላቸው የተፈጸመ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ስለዚህ ዲጂታል ቴክኖሎጂውን ከመጠበቅ አንፃር በተቋማት የሚታየው የግንዛቤ ችግርና የአሠራር ሥርዓት በትክክል ያለመኖር ለጥቃት መነሻ ሆኖ የሚገኝበት ሁኔታም እንዳለ አመልክተዋል፡፡

እንደ አቶ ሃኒባል ገለጻ፣ በኢትዮጵያ ሁኔታ ከሚደርሱ የሳይበር ጥቃቶች ብዙዎቹ የፋይናንስ ተቋማት ሲሆኑ፣ ከዘርፉ የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት ብዙዎች ዒላማ ስለሚያደርጉትም ነው፡፡

እነዚህ ተቋማት ከዚህ ጥቃት ለመዳን በዕለቱ በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ እንደ መፍትሔ ሆኖ የተቀመጠው የሳይበር ጥቃት የመድን ሽፋን ነው፡፡ በዕለቱ ዋነኛ የመወያያ አጀንዳ ይኼው ጉዳይ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ የመድን ድርጅቶች የሳይበር ጥቃት የኢንሹራንስ ሽፋን መስጠት እንዳለባቸው ተመልክቷል፡፡

አቶ ያሬድም አሁን እየሰፋ ከመጣው የሳይበር ጥቃት አንፃር፣ የኢትዮጵያ የመድን ኩባንያዎች ለሳይበር ጥቃት የሚሆን የመድን ሽፋን መስጠት እንዳባቸው ታምኖ፣ በተለያዩ መንገዶች እየተዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ይህንን አገልግሎት ለማስጀመር የሚጠበቅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መኖሩን የጠቀሱት አቶ ያሬድ፣ ይህ መመርያ እንደወጣ ኩባንያዎች እንደ ፍላጎታቸው አገልግሎቱን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ዶ/ር ሹመቴም የፋይናንስ ተቋማት ለሚገዟቸው ቴክኖሎጂዎች የኢንሹራንስ ሽፋን እንደሚያስፈልጋቸው ጠቅሰዋል፡፡

የሳይበር ጥቃት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ የፋይናንስ ተቋማት የሰው ኃይል አቅማቸውን ከማሳደግ ጀምሮ የሳይበር ጥቃትን ሊታደግ የሚችል የመድን ሽፋን ሊኖራቸው እንደሚገባም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ የአፍሮ ኤዥያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሚስተር ኡዲ ፓቴልም፣ አሁን ላለው የሳይበር ጥቃት አንዱ መፍትሔ ይኼው የሳይበር ጥቃት የመድን ሽፋን መሆኑን አመልክተዋል፡፡  

እንደ አቶ ፍቅሩ ገለጻ ደግሞ የኢትዮጵያ የጠለፋ መድንም ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል አንዱ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን እየለየ ግንዛቤ መፍጠር በመሆኑ የኢንሹራስ ኩባንያዎቹ ገበያውን በመለየት አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ይዘው እንዲመጡ ይጠበቃል፡፡ ተቋማት ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅ ሦስት ዋና ዋና ነገሮች ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውና ከእነዚህ አንዱ ቴክኖሎጂ መሆኑን አቶ ሃኒባል ይገልጻሉ፡፡ አሁን የፋይናንስ ተቋማቱ ቴክኖሎጂ እየተጠቀሙ በመሆኑ የሚሰጡትን አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ ለመድረስ ጥረት እየተደረገና መንግሥትም እያበረታታ በመሆኑ ይህ ቴክኖሎጂ መጠበቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንፃር ተቋማቱ ይህንን ቴክኖሎጂ ቀመስ ግልጋሎት ከጥቃት ለመጠበቅ ቴክኖሎጂው ራሱ ይዞ የሚመጣው ሴኪዩሪቲ ኮንፊገር መደረግ የሚኖርባቸው ሲሆን፣ የሚጠብቁ የቴክኖሎጂ አማራጮች ያሉ በመሆኑ ይህም የደኅንነት ቴክኖሎጂዎች አገልግሎት ላይ ማዋል የግድ እንደሚሆንም ተብራርቷል፡፡ እንደ ፀረ ቫይረስና የመሳሰሉትን መጠቀምም አስፈላጊ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡  

ሌላው መጠበቂያ ተደርጎ የሚወሰደው የአሠራር ሥርዓት ሲሆን፣ አንድ ተቋምን ከሳይበር ጥቃት ለመጠበቅ የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ መሆኑንም ያመለከቱት ኃላፊው፣ የሳይበር ደኅንነት ማዕቀፎች ማዘጋጀትና የኮርፖሬት ፖሊሲን መተግበር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ ኢንፎርሜሽን ደኅንነት የሳይበር ደኅንነት ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ እያንዳንዱ ሠራተኛ ሊያውቀውና ጉዳዬ ብሎ ሊይዘው ይገባል ብለው እንደሚያምኑና ለዚህም ትልቁ ድርሻ ያለው ከፍተኛው አመራር ላይ እንደሆነም ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

እያንዳንዱ ሠራተኛና ደንበኛ ከተቋማቱ ጋር ባለው እንቅስቃሴ በተለይ ሠራተኛው ካለው ሥራ ጋር በተያያዘ የሥራ መደቡን ተከትሎ የሥራው ዝርዝር ውስጥ በመጀመርያ የሳይበር ደኅንንት ጉዳይ መቀመጥ ያለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተለይ የሰው ኃይል ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትም በመጠቆም
ተከታታይና ወቅቱን ያገናዘበ ቢቻል በስድስት ወራት ወይም ከዚያም ባነሰ ጊዜ ለሠራተኞቻቸው የሳይበር ጥቃትን በተመለከተ ግንዛቤ በመፍጠር አደጋውን ለመቀነስ ዕድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ከራሳቸው የቢዝነስ ዓላማ ጋር ካልሰፉት ትልቅ ችግር ሊኖር እንደሚችል ጠቁመው፣ ይህንን ጉዳይ የቢዝነሱ አንድ አካል ነው ብለው ሊሠሩበት እንደሚገባም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ እንዲህ ባለው ሁኔታ አሥጊ የመሆኑን ያህል፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ከዚህ ጥቃት ለመጠበቅ ማድረግ ያለባቸውን ተግባር እየፈጸሙ ነው ወይ? የሚለው ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ሲሆን፣ ብዙዎች የአደጋውን የሥጋቱን ያህል እየሠሩ አለመሆኑን የሚጠቁሙ ናቸው፡፡  

አቶ ሃኒባልም በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የሰጡት ምላሽ ‹‹እያደረጉት አይደለም›› የሚል ነው፡፡ ከፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ ካሉ ተዋንያኖች ተብለው ከሚጠቀሱ ባንክ፣ ኢንሹራንስና ማክሮ ፋይናንስ ውስጥ ባንኮች የተሻለ እንቅስቃሴ ያላቸው ሲሆን፣ የሳይበር ደኅንነት ማስጠበቂያ ምሰሶዎች ላይ የሚሠራውን ሥራ ስናስብ ከሰውና ከአሠራር ሥርዓት ይልቅ ቴክኖሎጂ ላይ የሚሠሩ ያደላሉ፡፡ ጅማሬዎቹ አሉ፡፡ ምሳሌ የሚሆኑ ተቋማትም አሉ፡፡ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ግን አይደሉም፣ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡  

እነዚህ የፋይናንስ ተቋማት በሳይበር ጥቃት ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ተመልክተው በሥጋቱ ልክ አለመሥራታቸውን የጠቆሙት አቶ ሃኒባል፣ በተለይ አመራሩ ካልነቃ ይህንን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችል በጀት ላይመደብ ካልቻለ ችግሩ ይኖራል ይላሉ፡፡ ስለዚህ በተለይ ከላይ ያለው አመራር ለዚህ ዝግጁ ሆኖ መገኘቱ እጅግ አስፈላጊ መሆኑም ያምናሉ፡፡  

ይህንን የሳይበር ጥቃት በመድን ሸፋን ለመወጣት የሚደረገው ጥረት አስፈላጊ መሆኑ ላይ አቶ ሃኒባል ቢስማሙም፣ ጥቃቱ እንዳይደርስ በሚያስችሉ የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ መሥራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ 

‹‹ኢንሹራንስ ከአደጋ አያድነንም፡፡ አደጋ ሲፈጠር ግን የፋይናንስ ኪሳራ ምላሽ የሚሆን ነገር ግን ይዞልን ሊመጣ ይችላል፤›› ያሉት አቶ ሃኒባል፣ የሳይበር ጥቃትን ተከትሎ በተቋማት ላይ ያሉ የዲጂታል እሴቶች ላይ የሚደርሰውን አደጋ የፋይናንስ ጉዳት ማካካስ የሚያስችል መሆኑን ይስማሙበታል፡፡ አሁን የተጀመረውም ጥረት ጥሩ ቢሆንም፣ የበለጠ መሠራት ያለበት መሠረታዊ የጥቃቱ መከላከያ ዘዴ ላይ ነው፡፡

ዶ/ር ሹመቴም የፋይናንስና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከሚሰጡት አገልግቶች በተጨማሪ ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት ሊሰጡ እንደሚገባ ይስማማሉ፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ሰዋገኝ ጫኔም፣ ተመሳሳይ ሐሳብ የሰነዘሩ ሲሆን፣ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል አስቻይ የተባሉ ተግባራትን መፈጸም ተገቢ መሆኑን አመላክተዋል፡፡  

አያይዘውም ለመሠረተ ልማቶቻችንና መረጃዎቻቸው ደኅንነት ትኩረት እንዲሰጡ ጭምር ያሳሰቡት ዋና ዳይሬክተሩ የተለያዩ ሳይበር ደኅንነት ማስተግበሪያ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን ተፈጻሚ ሊያደርጉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡ 

አፍሮ ኤዥያን በዚህ መድረክ ላይ በአጋርነት የተሳተፈ ሲሆን፣ በለንደን ትልቁ የኢንሹራንስ ገበያ ላይ የሚሠራና በሳይበር ሪስክና በሳይበር ኢንሹራንስ ላይ የዳበረ ልምድ ያላቸው በመሆኑ በኢትዮጵያም ይህንኑ ለመሥራት መዘጋጀት ታውቋል፡፡

ይህ ኩባንያ ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆነ ፕሮጀክት በመቅረፅና ይኅንን አገልግሎት እንዴት ማስተዋወቅ አለብን የሚለው ላይ እንዲሁም የፖሊሲ ሥራዎች ላይ የሚረዳቸው መሆኑንም አቶ ፍቅሩ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ዓይነት የሳይበር ተጋላጭነት አለ? ይህንን ያህል ተጋላጭነት ካለ ምን ዓይነት መፍትሔ መቀመጥ አለበት ከተባለ፣ ተቋማት ሲስተም መዘርጋት አለባቸው፡፡ የሰው ኃይላቸውን ማሠልጠን አለባቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን አደጋው ቢደርስ ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለዚህ የሚሆን የመድን ሽፋን መስጠት አለባቸው ብለዋል አቶ ፍቅሩ፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች