Sunday, June 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ዓድዋ የነበረ… ዓድዋ የቀጠለ››

‹‹ዓድዋ የነበረ… ዓድዋ የቀጠለ››

ቀን:

ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በ1928 ዓ.ም. ከመከሰቱ በዋዜማው ዓመት ላይ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማኅበር ሀገርን ከባዕዳን ወራሪዎች ለመታደግ የአዲስ አበባ ሕዝብን ይቀሰቅስ፣ ያነሳሳ ነበር፡፡ እርመኛ አርበኝነትንም ያስታጥቅ ነበር፡፡ በኋላ ዘመን ላይ ድኅረ ድል የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ሆኖ ከመጣ በኋላም ጎጆው በድል ትዕምርትነት እየታየ እስተዚህ ዘመን ዘልቋል፡፡

በግርማዊ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት ወራሪው የጣሊያን ሠራዊት በዓድዋው የውሎ ጦርነት የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ድል የተመታበት፣ ሽንፈት የተከናነበበት 126ኛ ዓመት ለማክበር፣ ለመዘከር የታደለው ይኸው ታሪካዊው ጎጆ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ነው፡፡

ዕድሳቱ እየተገባደደ በመጣው ቴአትር ቤቱ አዳራሽ የኮቪድ-19 ፕሮቶኮል በጠበቀ መልኩ ታዳሚያንን ቀደምት አርበኞችን ጨምሮ ታዳሚያን ተራርቀው በተቀመጡበትና የሁሉንም ቀልብ ወደ አንድ አቅጣጫ ያደረገ የመለከት ድምፅ፣ የጥሩምባ ድምፅ  ተስተጋባ፡፡

‹‹ዓዋጅ ዓዋጅ›› እያለ የገባው ታዳጊ ወጣት የንጉሠ ነገሥቱን ዳግማዊ ምኒልክ የክተት ዓዋጅ እንዲህ ያንበለብለው ገባ፡፡

‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላትን አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፋ፣ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም የአገሬን ከብት ማለቅ፣ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘንህ እርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፡፡ አልምርህም፡፡ ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም።››

የዓድዋው ጦርነት ጠቅላይ አዝማች ዳግማዊ አፄ ምኒልክ

በዓውደ ውጊያው ዘመን ሲስተጋቡ የነበሩ ቃል ግጥሞችን ክራሩን እየገረፈ የጦርነቱን ድባብ በሚያስታውስ መልኩ ያንጎራጎረ ድምፃዊም ነበር፡፡

‹‹ዓድዋ ሥላሴ ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው፤

ሐበሻ ጉድ አለ ጣሊያን ወተወተ

ዓይነ ጥሩ ተኳሽ ቧ ያለው አባተ…››

 በታሪክ ድርሳናት ተጽፎ እንደምናገኘው፡-

 «ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ

በጀልባ ተሻግሮ ሐበሻን ሊገዛ» ይሉነበሩት በዓውደ ውጊያው የተሳተፉ አዝማሪዎች፣ ለጦር አዝማቾችም ማንቂያም መግጠማቸው አልቀረም፡፡

‹‹ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ

አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡

እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው

አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው፡፡

ዳኛው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ እይ

አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡

ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት

ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት፡፡››

ይህ ለጥቁሩ ዓለም ፋና ወጊ የሆነ በአውሮፓ ላይ የበላይነት የታየበት የዓድዋ ጦርነት ድል (ቀዳሚው የ1979ኙ የዶጋሊ ድል ሳይዘነጋ) ለመዘከር የውይይት መድረክ ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ነው፡፡

በመድረኩ ላይ ወረቀት ካቀረቡት አንዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ  ተባባሪ ፕሮፌሰር ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

‹‹ዓድዋ የነበረና ዓድዋ የሚቀጥል ነው›› ያሉት ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የጦር መሪዎች ፅኑ የአገር ወዳድነት፣ የንጉሠ ነገሥቱ ዳግማዊ ምኒልክ ቆራጥ ውሳኔ ከመልክዓ ምድሩ ጋር ለድሉ ስኬት ማብቃታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ ከዓድዋ ውርስ የጀግንነት ሥነ ልቦናን፣ አሸንፎ መዋልን መቅሰም እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የዓድዋው የድል ውሎ ለኢትዮጵያውያን ኅብረት አንዱና ዋናው ማሳያ ነው ያሉት ሌላው ተናጋሪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ የዓድዋው ድል የዘር እና የቀለም ታሪክን የቀየረና ዓለም ያልገመተው ነፃነትና ፍትሕ የተመሠረተበት መሆኑንም ዮናስ (ዶ/ር) ሳያሰምሩበት አላለፉም፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላሉ ጥቁር ሕዝቦች ጭምር መሆኑን ካወሱ በኋላ፣ ‹‹ዓድዋ አፍሪካን ማማ ላይ አውጥቶ ስማችንን በወርቅ ቀለም ያስከተበ የአንድ ቀን ክስተት ነበር፤›› ሲሉ አንፀባርቀዋል፡፡

126 ዓመታት በፊት፣ዛሬዋ የካቲት 23 ቀን 1888 .. ዓድዋ ላይ የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ድል የተመታበት ዕለት ነው፡፡ ቅድመ ዓድዋ ከአምባላጌ እስከ መቐለ ሽንፈትን የተከናነበው ወራሪው አውሮፓዊው ጦር፣ በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት የከተቱት ኢትዮጵያውያን እርመኛ አርበኞች ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ነው ዓድዋ፡፡

ይኸው የመታሰቢያ በዓል በኢትዮጵያ በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ሐውልትና አደባባይ እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት ከአራዳው አከባበር በመቀጠልም ንጉሠ ነገሥቱ ከነሠራዊታቸው ወደ ዓድዋ ሲጓዙ ያለፉበትን ‹‹የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ›› (በአጭር አጠራሩ ዓድዋ ድልድይ) ድረስ የእግር ጉዞ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡

የየካቲት 23 ውሎ

ጣሊያን 1888 .. የቅኝ ግዛት ህልሟንውን ለማድረግ በተነሳሳች ጊዜጦርነቱ መንሥዔ የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 በጣሊያንኛ ትርጉሙ ‹‹ኢትዮጵያ የጣሊያን ጥብቅ ግዛት ነች፤ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል፤›› የሚለው የተጭበረበረ ሐረግ ነበር ፍልሚያ ውስጥ የከተታቸው፡፡

ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ችግራቸውን ወደ ጎን ትተው ከየማዕዘኑ ተጠራርተው በዳግማዊ ምኒልክ መሪነት ከፍልሚያው ዓውድማ ተሠለፉ፡፡

የዓድዋውን ጦርነት ከመሩት የጦር አዛዦች መካከል እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኙበታል፡፡
የዓድዋ ጦርነት ሲነሳ ሁሌም የሚነሳው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ በስለላ ሙያው ተጠቅሞ የጣሊያንን የጦር ዕቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር አከናውኗል፡፡ የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረው አውዓሎም በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡

እንደ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ጽሑፍ፣ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን ዕቅድ ለዤኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ አውዓሎምና ብላታ ገብረ እግዚአብሔር ጊላ ማርያም ከጣሊያውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከጣሊያን መኰንኖች አንዱ ነገሩን ተገንዝቦ ‹‹አውዓሎም አውዓሎም›› እያለ ሲጣራ አውዓሎምም ሰምቶ፣ ‹‹ዝወኣልካዮ ኣያውዕለኒ›› (ከዋልክበት አያውለኝ) ብሎ አፌዘበት ይባላል፡፡

በታሪክ ጸሐፊው በአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አገላለጽ፣ የጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የጣሊያን ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ጀመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡ ወዲያው ተነስቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሳት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት፡፡

‹‹የ1ኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ራአዮ ከሚባለው ሥፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንዲ እዚያው እጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡

‹‹ከዚህም በኋላ በመጨረሻ ያለው የጣሊያን ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ሥፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ፡፡ ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር የቀለጠፉ ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ ኢጣሊያኖች ተስፋ በቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ ባንዲት ጠብታ ውኃ ማነው አፌን የሚያርሰኝ እያለ እንደ ተኮነነው ነዌ ሲጮኽ ጥቂት ቆይቶ ሞተ፡፡

‹‹ጣልያን ገጠመ ከዳኛው ሙግት

አግቦ አስመስለው በሠራው ጥይት

አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም፣

ጣልያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም

ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባሕር

የዳኛው ጌታ ያበሻ ባሕር፤» ተብሎም ስለዓድዋ ድል ስንኞች ታሰሩለት፡፡
   የታሪክ ጸሐፊው ቤርክሌይ ስለ ዓድዋ ዓውደ ውጊያ የጻፈውን ጳውሎስ ኞኞ፣ ‹‹ዐጤ ምኒልክ›› ብሎ ባሳተመው መጽሐፉ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

‹‹ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮጳ ጦር በአፍሪቃ ሰዎች ለመጀመርያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በዕልቂቱ በኩል 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ . . . ሐበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ ሐበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ናቸው፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

 መፍትሔ  ያላዘለው  የጎዳና  መደብሮችን  ማፍረስ

በአበበ ፍቅር ያለፉት ስድስት ዓመታት በርካቶች በግጭቶችና በመፈናቀሎች በከፍተኛ ሁኔታ...

የተናደው ከቀደምቱ አንዱ የነበረው የአዲስ አበባ ታሪካዊ ሕንፃ

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን...

የአከርካሪ አጥንት ሕክምናን ከፍ ያደረገው ‘ካይሮፕራክቲክ’

በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል...

ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው ራሚስ ባንክ ዛሬ ሥራ ይጀምራል

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመው...