Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዘመናዊ ግብርናን ለዘመናዊ ወጣት

መንግሥት ግብርናን ለማዘመን የኢኮኖሚ ማሻሻያን መሠረት ያደረገ የአሥር ዓመታት መሪ ዕቅድ ይፋ አድርጎ ወደ ተግባር ከገባ አንድ ዓመትን ተሻግሯል፡፡ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችን ያቀፈው የደቡብ ክልል የብዙ ሥነ ምኅዳር ቀጣና መሆኑን ተከትሎ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ በተለያዩ ሰብሎችና የእንስሳት ሀብት ፀጋ የታደለ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ሰፋፊ የውኃ አቅም፣ ሐይቆች እንዲሁም በአነስተኛ የጉድጓድ ውኃ ሊለሙ በሚችሉ አካባቢዎችም የታደለ ነው፡፡ ለግብርና አመቺ የሆነው ሥነ ምኅዳር ቢኖረውም፣ በአግባቡ ሳይጠቀመው መቆየቱ ይነሳል፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ ሲነሱ የነበሩት የክልልነት ጥያቄዎችና አለመረጋጋቶች፣ የግብርናውን ልማት አንቀው መያዛቸው ይጠቀሳል፡፡ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ውኃን ማዕከል ያደረገ የመስኖ ስንዴ የማልማት ሥራ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች ሲከናውን የቆየ ቢሆንም፣ በአንፃሩ በደቡብ ክልል ‹‹አይሳካም›› በሚል እምነት ሳይለማ መቆየቱ ይነገራል፡፡ ግብርናን ከባህላዊ አሠራር በማውጣት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ፣ የአርሶ አደሩን ሕይወት ለማሻሻል በተቀመጠው የአሥር ዓመታት ዕቅድ መሠረት፣ ደቡብ ክልልም ያለውን የውኃ አቅም ተጠቅሞ በበጋ መስኖ ልማት ላይ መሰማራት ችሏል፡፡ በክልሉ ከአራት ወራት በፊት የጀመረውን የበጋ መስኖ ውኃን ተጠቅሞ ግብርናን የማልማት ሥራና አጠቃላይ በክልሉ ስላለው የግብርና እንቅስቃሴ ዳዊት ቶሎሳ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩርን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ደቡብ ክልል ያለውን የግብርና አቅም በመጠቀም፣ ቀድሞ የነበረውን የአርሶ አደሩን ግብርና መንገድ ለማሻሻል ምን አቅዳችኋል?

አቶ ዑስማን፡- መንግሥት በዘንድሮ ምርጫ ለሕዝብ ያቀረበው ማኒፌስቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይም የኢትዮጵያን ሕዝብ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እንዲሁም በሰላሙም ዘርፍ ሁለንታዊ ዕድገትና ብልፅግናን አመጣለሁ ብሎ መነሳቱ ነው፡፡ በዚህም ውስጥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ከድህነት አወጣለሁ የሚለው ዋነኛው ነው፡፡ ይኼን ለማሳካት በይሆናል መንፈስ ብቻ ሳይሆን፣ ያለንን አቅም አሟጠን ተጠቅመን መሥራት እንዳለብን ተረድተናል፡፡ በተለይ ግብርናውን ከባህላዊ አሠራር አውጥተን፣ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘመናዊ የግብርና አሠራርን ለመከተል አቅደናል፡፡፡ በቴክኖሎጂ በመታገዝ ዘመናዊ ግብርናን ለዘመናዊ ወጣት በማዋል፣ ውኃ ተኮር የግብርና ልማቶች ላይ በመሰማራት በዓመት አንዴ ጊዜ ብቻ ከማምረት ከሁለት እስከ ሦስት ጊዜ ማምረት አለብን ብለን ተነስተናል፡፡ ይኼንንም ለማሳካት አርሶ አደሩን፣ አርብቶ አደሩን፣ በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እንዲሁም ወጣቱን በማስተባበር ያሉትን አቅም በመጠቀም ግብርናውን እንቀይራለን በሚል ዘንድሮ በሰፊው ማልማት ጀምረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ግብርናን ለማሻሻል የተቀመጠውን አዲስ መሪ ዕቅድ ተከትሎ በክልላችሁ የተጀመሩ ልማቶች አሉ፡፡ ዕቅዱን ወደ ተግባር ለመቀየር ክልሉ የተጓዘበትን መንገድ ቢያብራሩልን?

አቶ ዑስማን፡- መንግሥት ግብርናውን ቀይሮ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ እሠራለሁ ብሎ፣ የቃል ኪዳን ሰነድ አቅርቦ፣ በምርጫ የሕዝብን አዎንታዊ ምላሽ አግኝቷል፡፡ ስለዚህ ከምርጫ ማግሥት በአገር አቀፍ ደረጃም እንዲሁም በእኛ ክልል ለሕዝቡ በተጨባጭ እንዲደርስ በአዲስ መንፈስ፣ በአዲስ ዕይታ እንዲሁም በአዲስ የአገልግሎት አሰጣጥ መንገድ ለሕዝባችን አገልግሎት እንስጥ የሚል አቅጣጫ አስቀምጠናል፡፡ በዚህም መሠረት የነበረውን አመራር ሹም ሽር ከማድረግ ጀምሮ፣ አጠቃላይ አደረጃጀቱን አስተካክለን ወደ ተግባር ገብተናል፡፡ ወደ ተግባር ከተገባ በኋላ ያለንን አቅም በመገምገም እንዲሁም አቅሙን እንዴት መጠቀም እንችላለን በሚል በከፍተኛ አመራር ደረጃ ቁጭ ብለን ውይይት አደረግን፡፡ በዚህም 234 ሺሕ ሔክታር መሬት፣ ለማልማት ከአስፈጻሚም፣ ከአስተባባሪም ከአርሶ አደር እንዲሁም ከግል ባለሀብት ጋራ ስምምነት ላይ ከደረሰን በኋላ፣ 6,800 ሔክታሩን በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት ጀመርን፡፡

ሪፖርተር፡- የክልሉን አርሶ አደር ከመደበኛው የዝናብ ወቅት በዘለለ፣ በበጋ መስኖ ግብርና ልማት ላይ መሰማራቱ የተለየ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይቻላል?

አቶ ዑስማን፡- የመጀመርያው ማሳ የሌላቸውን አርሶ አደሮች ተቀናጅተውና ተባብረው እንዲሠሩ ከማድረግ በዘለለ፣ በአርሶ አደሮች መካከል መነቃቃትን ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ሌላው የአካባቢያችን አርሶ አደሮች የሥራ ባህል ላይ ለውጥ እንዲያመጡ አስችሏችዋል፡፡ በተለይ በክልሉ ታኅሣሥና ኅዳር ወር አብዛኛውን ምርት የሰበሰበ አርሶ አደር ጫት የሚቅመው በመቃም፣ የሚጠጣው በመጠጣት ጊዜውን ከማቃጠል ተቆጥቦ፣ አሁን ጊዜውን ማሳ ውስጥ እንዲያሳልፍ አስችሎታል፡፡ በዚህም ምክንያት ከዚህ ቀደም ያላግባብ ሲያወጣ የነበረውን ገንዘብ እንዲቆጥብ ከማስቻሉም በላይ፣ ቤተሰቡን ሳይቀር በማሳ ውስጥ እያዋለ ጠንክሮ እንዲሠራ አድርጎታል፡፡

ሪፖርተር፡- በክልሉ ሲነሱ የነበሩ የክልልነት ጥያቄዎች ጎን ለጎን በአዲስ የግብርና ዘይቤ አምርት ብሎ የማሳመን ሒደት እንዴት ይታያል?

አቶ ዑስማን፡- በክልሉ በጋራ ባደረግነው ግምገማ መሠረት ወደ ሥራው ከመግባታችን በፊት፣ በጉዳዩ ጋር መግባባት ላይ መድረስ አለብን ብለን ነበር የተነሳነው፡፡ በዚህም መሠረት ከአመራር፣ ከሙያተኛ እንዲሁም ከአርሶ አደሩ ጋር መተማመን ፈጠርን፡፡ ከዚያም የበጋ ስንዴ መስኖ ልማትን ጀመርን፡፡ ይኼንንም ለማሳካትና ብርሃን ለማየት በቁርጠኝነት እንዲሁም በፅናት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተማምነን ነበር፡፡ ስለዚህ የበጋ መስኖ ስንጀምር አይደለም የክልልነትና አስተዳደራዊ ጥያቄ ይቅርና አገራችን የህልውና ጥያቄ ውስጥ ስለነበረች፣ ልማቱን ለመጀመር አልተቸገርንም፡፡ የዚህ ውጤት ዋናው ጉዳይ የነበረው በውስጣችን እምነትና ይቻላል የሚለው ነበር፡፡

ስለዚህ ምርቱ አሁን ከታየው ውጤት ባሻገር ምርቱ ወደ አርሶ አደሩ ጎተራ ሲገባ፣ እንዲሁም ምርቱን ለገበያ አቅርቦ ገንዘብ ኪሱ ሲገባ ነው የበለጠ የእኛ ጥረትና ውጤት የሚታየው፡፡ ምርቱ ወደ አርሶ አደሩ እስኪገባ ክትትላችንና ድጋፋችን ይቀጥላል፡፡ ክትትልና ድጋፍ ደግሞ በሪፖርት ብቻ ተሸፋፍኖ የሚታለፍ ሳይሆን፣ በአካል አርሶ አደሩ ጋ ወርዶ ችግርን በመፍታት ሒደት የታገዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክልሉ የአርሶ አደሩን የበጋ መስኖ የማስፋፋት ፍላጎት ለመደገፍ እንዲሁም ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ ምን ታስቧል?

አቶ ዑስማን፡- በርካታ አርሶ አደሮች ቀድሞ የተገነቡ ቦዮችና የግድብ ጉድጓዶችን መንግሥት ያፅዳልን የሚል ጥያቄን ያነሱ ነበር፡፡ ቀድሞ አንድና ሁለት ሔክታር መሬት ላይ አትክልት ያለሙ የነበሩ አርሶ አደሮች አሁን 100 ሔክታር መሬት ማልማት ሲጀመሩ ውኃ እየሸሸ መሄድ ሲጀምር፣ እነሱም የተለያዩ ዘዴዎችን ፈጥረው፣ ተጨማሪ ጉድጓዶችንም ፈጥረው ውኃን በአግባቡ ሲጠቀሙ ታዝበናል፡፡ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ ብድር ተመቻችቶ፣ አርሶ አደሮቹ ፓምፕ ገዝተው እየተጠቀሙ ነው፡፡ ስለዚህ ያሉንን የውኃ አቅም እንዴት እንጠቀም? ምንድነው የሚያስፈልገን? የሚለውንና የአርሶ አደሩን ፍላጎት የሚያሟላ የድጋፍ አቅርቦት ላይ እየተማከርን እንሠራለን፡፡

ስለዚህ መንግሥት ብድር እያዘጋጀ፣ በርካታ የውኃ ጉድጓዶችን እየቆፈረና የተገነቡ የውኃ ጉድጓዶችን በሙሉ አቅማቸው በሚፈቀደው መንገድ ለማመቻቸት ከወዲሁ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ከዚያም ባሻገር የውኃ ብክነትን ለመቀነስ የውኃ አስተዳደር ሥርዓት ማበጀት እንደሚያስፈልግ እየተወያየንበትና መስመር እያስያዝን እንገኛለን፡፡ ሌላው የኤሌክትሪክ ችግሮችን ለመፍታት በአካባቢ ያለውን ሶላር በመጠቀም ቀን ውኃን በፓምፕ ለማውጣት እንዲሁም ማታ ለመብራት እንዲጠቀሙ ይደረጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አርሶ አደሩ ውኃን ለመጠቀም የጄኔሬተር ነዳጅ ዋጋ ፈተና እንደሆነበትና በቂ ውኃ ለማግኘት ጥረት በመጠባበቅ ሒደት ውስጥ ልማቱን እንዳስተጓጎለበት ያስረዳል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ምን ታቅዷል?

አቶ ዑስማን፡- አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች ላይ ሥራውና የውኃ ፍላጎቱ የማይመጣጠኑበት አጋጣሚዎችን ተመልክተናል፡፡ ሁሉም አርሶ አደር በተመሳሳይ ሰዓት አልምቶ ‹‹ውኃ ለእኔ ይገባኛል›› በሚል ሊያጋጥም የሚችለውን የውኃ አስተዳደር ችግር እኛም ተረድተናል፡፡ በአንፃሩ ‹‹ውኃ ለእኔ ይገባኛል›› የሚለው ጥያቄ እንደ ጥሩ ማሳያ ነው የምወስደው፡፡ ምክንያቱም ሥራው በአርሶ አደሩ ዘንድ የፈጠረውን የሥራ መነቃቃት ምን ያህል እንደሆነ ነው የምመለከተው፡፡ ከውኃ አጠቃቀም (Water use Efficiency) ጋር ተያይዞ ውጤታቸው እየታየ መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች እየተፈቱ ይሄዳሉ፡፡ ከነዳጅ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የክልሉ መንግሥት በመስኖ ልማት ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ቅድሚያ እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡ በዚህም ወጣቶች ተደራጅተው ለአርሶ አደሩ ነዳጅ በቀዳሚነት እንዲያቀርቡ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በአጠቃላይ በክልሉ ከበጋ ስንዴ መስኖ ልማት ባሻገር በሌሎች የመስኖ ልማቶች ላይ ያለው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

አቶ ዑስማን፡- በዚህ ዓመት በክልላችን የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ጨምሮ አጠቃላይ 234 ሺሒ ሔክታር መሬት ለማልማት አቅድን ነበር፡፡ እስካሁን ባለው 209 ሺሕ ሔክታር መሬት የታረሰ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አብዛኛው መሬት በሰብል ተሸፍኗል፡፡ በዚህም 960 ሺሕ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 6,000 ሔክታር መሬት ብቻ ለበጋ መስኖ ስንዴ ላይ ያዋልን ሲሆን፣ ቀሪው በሌሎች የመስኖ ልማቶች የተሸፈኑ ናቸው፡፡ ከስንዴው ባሻገር በአትክልት፣ በፍራፍሬና በሥራ ሥር ያሉ ሰብሎች እየለሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በአማካይ ከአንድ ሔክታር ከ125 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ ክልሉ ከመደበኛው የበቆሎ፣ የስንዴና የጤፍ ሰብሎች ባሻገር ዋናውና ትኩረት አድርጎ የሚሠራው በፍራፍሬ ነው፡፡ ይኼም እንደ አካባቢው የአየር ንብረትና የአፈር ተስማሚነት ታሳቢ በማድረግ ለምግብ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለአገር ውስጥ እንዲሁም ለውጭ ገበያ የሚውሉ ምርቶችን በስፋት ለማልማት ዕቅድ ነድፏል፡፡ በዚህም በርካታ የፍራፍሬ መንደሮችን በክላስተርና ተፋሰስ ይለማሉ፡፡ በፍራፍሬ ልማቱ የእምነት፣ የጤና እና የትምህርት ተቋማት ይሰማራሉ፡፡ ይኼንን የፍራፍሬ ልማት ዘንድሮ ጀምረናል፡፡ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ሐባብና ሌሎች የፍራፍሬ ምርቶች እንደ አካባቢው የአየር ሁኔታ በሰፊው ይለማሉ፡፡ በአሥር ዓመታት ውስጥ ውጤታቸውን ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በአሁኑ ወቅት ከ21 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋል›› አቶ አበራ ሉሌሳ፣ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ጸሐፊ

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ላለፉት 89 ዓመታት በመላ አገሪቱ የሰብዓዊነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ በድርቅ፣ በበሽታና በግጭት ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች የምግብ፣ የመጠለያ፣ የመድኃኒትና የ24 ሰዓት...

ከቢሻን ጋሪ እስከ ዶባ ቢሻን እንክብል

ዶባ ኢንዱስትሪያል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም. ከሦስት ዓመታት በላይ ጥናትና ምርምር ያደረገበትንና ለገበያ ያበቃውን ዶባ-ቢሻን እንክብል የውኃ ማከሚያ...

ለሴቶች ድምፅ ለመሆን የተዘጋጀው ንቅናቄ

ፓሽኔት ፎር ኤቨር ኢትዮጵያ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በፆታ እኩልነት፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤና እንዲሁም የሴቶችን ማኅበራዊ ችግር በማቃለል ዙሪያ በተለያዩ ክልሎች ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ...