Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በቦረና ዞን የወጣው የከርሰ ምድር ውኃ ተመረቀ

በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ በቦረና ዞን የወጣው የከርሰ ምድር ውኃ ተመረቀ

ቀን:

ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ አስከፊ የሚባል ድርቅ ባጋጠመው የኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን፣ በአምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ቶፕ ቤቨሬጅ ኤንድ ትሬዲንግ ኢንዱስትሪ የተባለ ኩባንያ የወጣው የከርሰ ምድር ውኃ ተመረቀ፡፡

በ600 ሺሕ ሰዎች ላይ የውኃ ዕጥረት ባጋጠመበት የቦረና ዞን፣ የተቆፈረው ጉድጓድ ድርቁን አስመልክቶ እየተደረጉ ካሉ የሳርና የመኖ ጊዜያዊ ድጋፎች ይልቅ ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጣ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የከርሰ ምድር ውኃ ቁፋሮው የተከናወናው፣ ከቦረና ዞን ዋና ከተማ ያቤሎ በ185 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በዳስ ወረዳ ሥር በምትገኘው ቦርቦር ቀበሌ ነው፡፡ ቀበሌዋ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ውኃ ለማጠጣት ከአጎራባች ወረዳና ቀበሌዎች ተነስተው የሚመጡባት በመሆኗ ቁፋሮው በቦርቦር ቀበሌ መከናወኑ ታውቋል፡፡

- Advertisement -

የካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. የተመረቀውን የከርሰ ምድር ውኃ ጉድጓድ ቁፋሮ ለማጠናቀቅ ሁለት ወር እንደወሰደ የተናገሩት የቶፕ ቤቨሬጅ ኤንድ ትሬዲንግ ኢንዱስትሪ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ አጀማ፣ በሰከንድ ከአሥር ሊትር በላይ የሆነ ውኃ ከጉድጓዱ እየወጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይኼ የውኃ መጠን በአካባቢው ካሉና በሰከንድ ከሁለት ሊትር በላይ ውኃ ከማይወጣባቸው ሌሎች ጉድጓዶች አንፃር ከፍተኛ መሆኑንና ቁፋሮው ሲጀመር ይኼንን ያህል ውኃ ይኖራል ተብሎ እንዳልታሰበ አቶ ሽመልስ ተናግረዋል፡፡

144 ሜትር ጥልቀት ያለው የከርሰ ምድር ውኃው፣ አሁን እየሰጠ ባለው የውኃ መጠን በቀን ለስምንት ሰዓት አገልግሎት ቢሰጥ 1,800 ሰዎች በየቀኑ ሁለት መቶ ሊትር ውኃ ማግኘት እንደሚችሉ ታውቋል፡፡ እየወጣ ያለው ውኃ በሰከንድ ወደ 15 ሊትር እያደገ በመሆኑም በአንድ ቀን ውስጥ ተደራሽ የሚያደርጋቸው ሰዎች ብዛት ወደ 2,300 ማደግ እንደሚችል ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ካሉት 1.4 ሚሊዮን ነዋሪዎች ውስጥ 600 ሺሕ ያህሉ ላይ የውኃ ዕጥረት ያጋጠመበት የቦረና ዞን፣ ባለፉት ተከታታይ የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ባለማግኘቱ አስከፊ ድርቅ እያስተናገደ ነው፡፡ በዚህ ድርቅ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ከብቶች የሞቱ ሲሆን ድርቁ ያስከተለው ዋነኛው ችግር የውኃ ዕጥረት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዞኑ አስተዳደር ኩባንያው ያስቆፈረውን የከርሰ ምድር ውኃ ላይ ማስተላለፊያ መስመሮችን በመግጠም እስከ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሉ ቀበሌዎች እንደሚያሠራጨውና ይህም ከብቶቻቸውን ውኃ ለማጠጣት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን እየተጓዙ ያሉትን የቦረና አርብቶ አደሮች ችግር በጥቂቱም ቢሆን መፍታት እንደሚያስችል የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጃርሶ ቦሩ ተናግረዋል፡፡

ዋና አስተዳዳሪው የዞን አስተዳደሩ 32 የውኃ ቦቴዎችን ተከራይቶ ውኃ ማቅረብ እንደጀመረ ተናግረው፣ ግብረ ሠናይ ድርጅቶችም ውኃ ማቅረቡ ላይ መሰማራታቸውን አስታውቀዋል፡፡ አስተዳደሩ እያቀረበ ያለው የቦቴ ውኃ የአስቸኳይ ጊዜ ሥራ እንጂ ዘላቂ መፍትሔ እንዳልሆነ ያስታወሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር እየወጣባቸው ያሉ 14 አነስተኛ ግድቦች በግንባታ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጃርሶ አሁን የተከሰተውን ድርቅ አስመልክቶም በየሁለት ሳምንቱ ግምገማ የሚያደርግ ግብረ ኃይል በዞንና በወረዳዎች ተዋቅሮ በእንቅስቃሴ ላይ መሆኑን ተናግረው፣ አባላቱ ከተለያዩ አካላት ሀብት ማሰባስብ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ነገር ግን ድርቁ ያስከተለው ችግር እየተባባሰ በመሆኑ የተገኘውን ዕርዳታ ለሁሉም ማድረስ እንዳልተቻለ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ