Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ድብብቆሽ!

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከፈረንሣይ ሌጋሲዮን ወደ መርካቶ ነው። ሕይወት ዓመሏ ብዙ ነው። መልኳ እያደር ይለዋወጣል። የጠበቁት ይቀርና ያላሰቡት ይከሰታል። የሠጉበት ነገር ጭምድድ አድርጎ እያሰረ በጭንቀት ይንጣል። ይኼኔ ታዲያ ‹‹የፈሩት ይደርሳል የጠሉት ይወርሳል›› ብለው እንዲተርቱ ይገፋፋል። ይህች ነፍስ ተብዬ በሥጋ ከተማ ውስጥ የተሸሸገች ታላቅ ምስጢር ነች፡፡ የሁለመናን ሚዛን እየጠበቀች እስከ ፍፃሜ ትገሰግሳለች፡፡ ስለዚህም ሕይወት ምን ብትከብድ፣ ኑሮ ምን እያደር ፊቷ ቢጠቁር መኖር ይፈቀር ዘንድ ግድ ታስብላለች። ነፍስ ታሳሳለችና። በሕይወት ጎዳና ላይም ሆነ በልማታዊውም መንገድ ላይ ወዲያ ወዲህ ስንል ቀናችንና ዘመናችን ይጠናቀቃል። እንቅፋቱ ሲበዛብን በነፍስ በኩል ለፈጣሪ በሥጋ በኩል ለአስተዳዳሪዎቻችን ልንናገር ዘንድ እንማስናለን። ይህ ቢሆንም ቅሉ መኖር ይቀጥላል። ምን መከፋት ቢነግሥ፣ ምን መሰልቸት ቢበዛ መኖር በሕይወት ጎዳና፣ መኖር በጉዞ ውስጥ መቀጠሉን ሁላችንም ለመታዘብ ሁሌም በቦታው እንገኛለን። እንዳልነው ነፍስ ያሳሳልና፡፡ ታክሲ ውስጥ ገብቼ እንደተቀመጥኩ ዓይኔ አንዱ ጥቅስ ላይ ተተከለ። ‹‹ራስን ከመግዛት የበለጠ ትልቅ ሥልጣን የለም›› ይላል። አጠገቤ ደልደል ብሎ የተቀመጠ ተሳፋሪ እንደ እኔው ጥቅሱን በሙሉ አንብቦ ሲያበቃ፣ ‹‹ባይሆን በዚህ እንኳ እንፅናና እንጂ…›› ብሎ ፈገግ አለ። በተናገረው ቃል ውስጥ ያለው መልዕክት ቅድሚያ ለራሱ እንደተገለጠለት ሊጠቁመን የፈለገ ይመስላል። እንዲያ ነው!

‹‹በምኑ?›› በማለት ከኋላችን የተቀመጠ ጎልማሳ ጠየቀው። ‹‹‘ራስን ከመግዛት በላይ ሥልጣን የለም’ የሚለውን ጥቅስ አላየህም እንዴ? ባይሆን እንዲህ እያልን እንፅናና እንጂ! ሂሂ አሁን ይቺ ስላቅ አይደለችምና ነው?›› ብሎ አሽሟጠጠ። አንድ ወጣት ተሳፋሪ ፈጠን ብሎ፣ ‹‹እንዴ? እንዴ? ምነው ዴሞክራሲ እየገነባን? በድምፃችን ራሳችንን ማስተዳደር እየቻልን ማሽሟጠጡን ምን አመጣው ወንድሜ?›› ብሎ በቀናነት የመሰለውን አስተያየት ጨምሮ ጠየቀው። መልሱን ከመስማታችን በፊት፣ ‹‹ከታክሲ ውስጥ የመናገር ነፃነትና ከፓርላማችን የትኛው የሚበልጥ ይመስልሃል?›› ብሎ ከኋላ የተቀመጠ ሰው ወዳጁን ሲጠይቀው ሰማን። መልሱ ተድበስብሶ አልሰማን ሲል፣ ‹‹ደጇን ዓይተህ ቤቷ ግባ፣ እናቷን ዓይተህ ልጅቷን አግባ›› የሚሉት ምሳሌ በአዕምሮዬ ተመላለሰ። ተድበስብሶ ማድበስበስ የት ያደርሰን ይሆን? የዚህንም መልስ መስማት አማረን፡፡ ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ በሌለበት ሁኔታ ውስጥ ጥያቄዎችን እንደ ሸቀጥ ማምረት ምን ይፈይድልን ይሆን? እንጃ!

‹‹ምን ዋጋ አለው?›› አለ አሽሟጣጩ ተሳፋሪ ድንገት ጮክ ብሎ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ድምፃችን የሚፈለገው ለምርጫ ብቻ ነው መሰለኝ። ለአቤቱታና ለአስተያየት ጊዜ ሰሚ የለም…›› ሲለው ወጣቱ ዝም አለ። ሰው እየገባ ታክሲያችን እየሞላች ብትሆንም፣ ወያላው ትርፍ ካልጫነ በቀላሉ የሚንቀሳቀስ አልመሰለንም። ‹‹ኧረ እንሂድ? ምናለ ቢበቃህ?›› አለው አንድ ተሳፋሪ። መቸኮሉ ከመቁነጥነጡ ያስታውቃል። ‹‹ቀስ በላ፣ እንደ ፈለግኩት ጭኜ ነው የምሄደው…›› ብሎ በትዕቢት አነጋገር መለሰለት። ይኼ አልበቃው ብሎ ደግሞ፣ ‹‹ከፈለግክ መውረድ ትችላለህ…›› ብሎ ገላመጠው። ‹‹አይ ራስን መግዛት?› በማለት ቅድም ጥቅሷን እያየ ሲያሽሟጥጥ የነበረው ተሳፋሪ በሳቅ ፈነዳ። ‹‹ልጅ የአባቱን ይወርሳል ሆነና ለምንለጥፈው ጥቅስ፣ መርህና ዓላማ ታማኞች አልሆን አልን…›› ብሎ ሳቁን ካቋረጠበት ቀጠለው። ሌላው መለሰና እኔ የምፈራው ሥራው በሌለበት ግልጽነትና ተጠያቂነት እየተባለ የሚነገረው ነገር ተረት ተረት እንዳይሆን ነው…›› ብሎ አቀረቀረ። አንዳንዱ ሰው ክፉኛ ነገር ሲገባው አሳሳቅና አለቃቀስን አሳምሮ ይችላቸዋል። በአስመሳዮች ዘመን ሙዚቃው፣ ድራማው፣ ኮሜዲው፣ ለቅሶው፣ እንደ ማኅበራዊ ተሰናድተው ሲቀርቡ ትወናውም የዚያኑ ያህል ቀጥሏል፡፡ እውነት ነው!

አንድ ወጣት ተሳፋሪ ደግሞ፣ ‹‹ዋናው መገንዘብ የሚገባን ጉዳይ አገራችን አሁን ባለችበት ሩጫ ይህን መሰል ወሬ እኛን ሥራ ማስፈታት የለበትም። የህዳሴው ግድብ ኤሌክትሪክ ማመንጨት የቻለው እኮ በዚያ በበረሃ ቀንና ሌሊት ተሠርቶ ነው፡፡ እኛ የሚያስፈልገን ተቀምጦ ማውራት ሳይሆን እንዴት ለሥራ እንደምንነሳ መነጋገር ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ በሰሞኑ የሩሲያና የዩክሬን ጉዳይ የነዳጅ ዋጋ ወደ ላይ ሲተኮስ፣ እኛ የምናወራው ምን ያህል ሚሳይል እንደ ተተኮሰ እንጂ ከአስፈሪው የዋጋ ንረት ውስጥ እንዴት ሠርተን ማምለጥ እንደምንችል አይደለም…›› ሲል ከኋላ የተቀመጠው ተሳፋሪ በሐሳቡ ከተስማሙ ሰዎች ድጋፍ ተቸረው። አወይ ዕውቀት ዓይነቷ ብዙ፣ ፈላጊዋ ብዙ፣ ተማሪዋ ብዙ። ምን ያደርጋል? አደናቃፊዎቿም የዛን ያህል ናቸው፡፡ ልክ ነው ያሰኛል!

ወያላው እንዳሰኘው አፋፍጎን ሲያበቃ፣ ‹‹እንሂድ!›› ብሎ ሾፌሩን አዘዘው። ‹‹የበላዩ ታዛዥ የበታቹ አናዛዥ የሆነበት ዘመን። እግዚኦ! አሁን ይኼ አንድ ፍሬ ልጅ ከሕግ በላይ ሆኖ መብታችንን በጠራራ ፀሐይ ሲነፍገን ካልተባበርን መቼ ልንተባበር ነው?›› ብለው ከኋላ ተጨናንቀው የተቀመጡ አንድ አዛውንት ተናገሩ። ‹‹እውነት እኮ ነው! መቼ ይሆን እኛ እርስ በርሳችን ለመልካም ነገር፣ ለዕድገት፣ ለመብታችን መንግሥትን ሳንጠብቅ ተነሳስተን የምንተባበረው?›› ብሎ አጠገባቸው ያለ ጎልማሳ ተናገረ። ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹የትራፊክ ፖሊስ ሲኖር…›› ብሎ በስስ ፈገግታ ፊቱን አብርቶ እያንዳንዳችንን ተመለከተን። ‹‹ማለት?›› አለው አጠገቡ ያለው ወጣት። ‹‹በግልህ ሞክረህ የሚረዳህ ስታገኝ የራስህን ድርሻ ተወጣህ ማለት ነው፡፡ ኳሷን ለግተህ የሚቀበልህ ሲኖር ማለቴ ነው። እኛም የምናበሳጫችሁና የምንበሳጨው በዚህ ክፍተት መካከል ነው። ከእኔ ጋር ብለህ ብለህ ሲያቅትህ የሚመለከተው አካል በቅርብህ ከሌለ ምን ዋጋ አለው?›› ሲል ነገሩ ገባን። የወያላው ሁኔታ፣ ‹‹አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም›› መሆኑ አሳዘነን። ስንቱ አውቆ ተኝቶ ሰበብ እንደሚያፈላልግ ስናውቅ ሐዘናቸን ብሔራዊ የማይሆንልን ለምን ይሆን? አጠያያቂ ነው!

 ጉዞአችን ሊገባደድ ጥቂት መንገድ ሲቀረን ሾፌሩ የከፈተው ሬዲዮ በቴሌቪዥን ስለሚተላለፍ አንደ ፕሮግራም ተናገረ፡፡ አዛውንቱ እየተቆጡ፣ ‹‹ምን ዋጋ አለው እየቆራረጡ ነው የሚያቀርቡት? በዚያ ላይ ደግሞ እሑድ ያሉት ረቡዕ፣ ማክሰኞ ያሉት ዓርብ እየቀረበ ግራ ተጋባን እኮ?›› ሲሉ ድንግርግር ያልን በዛን፡፡ አጠገቤ ያለው ተሳፋሪ፣ ‹‹አንተም አልገባህም?›› አለኝ፡፡ እንዳልገባኝ አንገቴን በመወዝወዝ ገለጽኩለት፡፡ ‹‹ሰሞኑን በቲቪ ሲተላለፍ ስለነበረው ዶክመንተሪ ትረካ እኮ ነው…›› ቢለኝም አልገባኝም፡፡ ወያላው መድረሻችንን ለማብሰር ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን ተንጋግተን መውረድ ጀመርን፡፡ አጠገቤ የነበረው ተሳፋሪ፣ ‹‹ከሁሉ ነገር በላይ ምን እንዳስደሰተኝ ታውቃለህ?›› ሲለኝ፣ ‹‹ምን ይሆን?›› አልኩት፡፡ ‹‹የእኛ ሰው የሚያስደስተው መስማት የሚፈልገውን ስትነግረው መሆኑን ማወቄ ነው…›› ሲለኝ ሳይገባን ‹‹ገባኝ!›› አልኩት፡፡ ሳይገባን እንደገባን ሆነን እርስ በርስ እንደ አይጥና ድመት ድብብቆሽ እንጫወት እንጂ፣ የዘንድሮ ነገራችን ከድብብቆሽ አልፎ ሌላ ነገር ውስጥ ሳያስገባን አይቀርም፡፡ መልካም ጉዞ!

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት