Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምዩክሬንን የጦር ዓውድማ ያደረገው የምዕራባውያኑና የሩሲያ ፍላጎት

ዩክሬንን የጦር ዓውድማ ያደረገው የምዕራባውያኑና የሩሲያ ፍላጎት

ቀን:

በሩሲያና በዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ምክንያቱ የሚመዘዘው የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት እ.ኤ.አ. በ1990ዎቹ መጀመርያ ላይ ከፈራረሰች ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡

በ1922 የአሁኖቹን ሩሲያ፣ ዩክሬን፣ ጆርጂያ፣ ቤላሩስ፣ አዘርባጃንን ጨምሮ 15 አገሮችን ይዞ የተመሠረተው ሶቪየት ኅብረት፣ በ1991 ከፈራረሰ በኋላ ዩክሬን በአቶሚክ ጦር መሣሪያ ብዛት በዓለም ሦስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቷ ለሩሲያና ለአሜሪካ ሥጋት ነበር፡፡

በወቅቱም የዩክሬንን የኑክሌር መሣሪያ ለማስፈታት አሜሪካና ሩሲያ ተከታታይ የሆኑ ዲፕሎማሲያዊ ስምምነቶችን አድርገዋል፡፡ በዚህም ዩክሬን በመቶዎች የሚቆጠሩ የኑክሌር አረር ለሩሲያ ስታስረክብ ሩሲያ ደግሞ በምላሹ ለዩክሬን ሥጋት ላትሆን የደኅንነት ማረጋገጫ ሰጥታለች፡፡ ነገር ግን ይህ እ.ኤ.አ. በ2014 መልኩን ቀይሯል፡፡

ከስምንት ዓመት በፊት ሩሲያና ዩክሬን ወደ ጦርነት የገቡበትና ክራይሚያም ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችበት ወቅት ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የሩሲያ ደጋፊ የሆኑትን የምሥራቅ ዶንባስ ክልሎች ሩሲያ መደገፍ የጀመረችበት ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረው የተሻለ ግንኙነት የሻረከ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በፊት ከነበረው ጦርነት በባሰና ምዕራባውያንም ወታደሮቻቸውን ከመላክ በመለስ ባሳተፈ ጦርነቱ በዩክሬን ምድር እየተካሄደ ነው፡፡

ጦርነቱ ወደ ኑክሌር ይቀየራል የሚል እምነት እንደሌላቸው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቢያስታውቁም፣ የምዕራባውያኑ የሩሲያን ኢኮኖሚ ለማንኮታኮት ማዕቀብ እየጣሉ መገኘት፣ ለዩክሬን የጦር መሣሪያ መርዳትና በሚዲያዎቻቸው ተጠቅመው ሩሲያን ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የማግለል አካሄዳቸው ወደ ዓውዳሚ የኑክሌር ጦርነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ሥጋት ደቅኗል፡፡

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በሩሲያ፣ በምሥራቅ አውሮፓ፣ በምዕራባውያንና በአጠቃላይ በዓለም ላይ የተደገነውን አጠቃላይ ቀውስ ለመቀልበስ ‹‹ፍላጎታችን ይጠበቅ›› ማለት ከጀመሩ ከርመዋል፡፡

 ሩሲያ፣ የሩሲያንና የአካባቢውን ደኅንነት ለማስጠበቅ አሜሪካና አውሮፓውያኑ እንዲያውቁላትና ቀይ መስመሩን እንዳያልፉ ያስቀመጠቻቸው ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በተለይም ዩክሬንን የተመለከቱት ውሳኔ ሊያገኙ የሚገባቸው እንደሆነ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን በግልጽ ለአሜሪካና ለሌሎቹ ምዕራባውያንና ለሰሜን ጦር ቃልኪዳን ድርጅት  (ኔቶ) አባል አገሮች በታኅሣሥ 2021 ላይ ማስታወቃቸውንም ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡

 ኔቶ በምሥራቅ አውሮፓ የሚያደርገውን የአባላት ማሳሰብ እንዲያቆም የጠየቁት ፑቲን፣ የዩክሬንን የአባልነት ጥያቄም እንዳይቀበል አስገንዝበዋል፡፡

በአውሮፓ የነገሠው ውጥረት እንዲቆምና በዩክሬንና ሩሲያ መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ፣ ኔቶ ዩክሬንን ከአባልነት ጥያቄ እንዲያግድ ብቻ ሳይሆን፣ በምሥራቅ አውሮፓ ካሉ አገሮች ከ1997 በኋላ ኔቶን ከተቀላቀሉ አገሮች ውስጥ የወታደሮችና የመሣሪያዎች ልክ ላይ ገደብ እንዲጥልም አሳስበዋል፡፡

ኔቶ ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ከመስፋፋቱ በፊት ወደነበረበት ቦታ መሣሪያውንም ሆነ ወታደሮቹን እንዲመልስ፣ የሩሲያን ፍላጎት የማያሟላ ከሆነ ደግሞ በ1962 እንደተከሰተው ‹‹የኩባ የሚሳይል ቀውስ›› ተመሳሳይ ዓይነት ወታደራዊ ምላሽ እንደሚሰጥ ፑቲን አስታውቀው ነበር፡፡

ኔቶ ከ1997 ወዲህ አብዛኛውን ምሥራቅ አውሮፓ፣ ፖላንድ እንዲሁም የቀድሞ የሶቪየት ኅብረት አባል አገሮች ኢስቶኒያ፣ ሊቱኒያ፣ ላትሺያና የባልካን አገሮችን አባል ያደረገው ኔቶ፣ ሩሲያን በኔቶ ወታደሮችና መሣሪያዎች እንድትከበብ ማድረጉን ሩሲያ ‹‹የደኅንነት ሥጋቴ ነው›› ትለዋለች፡፡ ምዕራባውያንን ለሩሲያ ደኅንነት ‹‹ሕጋዊ ዋስትና››  መስጠት አለባቸው ስትልም አሳስባ ነበር፡፡

ለዚህ ምላሽ ያልሰጡት የኔቶ አባል አገሮች ‹‹ሩሲያ ዩክሬንን ልትወር ነው›› በሚል ለሳምንታት ያህል በሚዲያዎቻቸው ሲያስተጋቡ የከረሙ ሲሆን፣ ‹‹ዩክሬንን ለመውረር ፍላጎት የለኝም›› ስትል የከረመችው ሩሲያ ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ በዩክሬን ላይ የአየር ጥቃት መጀመሯን አስታውቃለች፡፡

የዩክሬን በርካታ መንደሮችና ግዛቶች በሩሲያ ቁጥጥር ውስጥ ገብተዋል፡፡ የዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት አገር እየተሰደዱ ሲሆን፣ ሩሲያም ኪዬቭን ለመቆጣጠር 40 ኪሎ ሜትር ያህል እንደቀራት የተለያዩ ሚድያዎች ዘግበዋል፡፡

ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ በፊት ለዲፕሎማሲያዊ ውይይቶች ከተደረጉ ጥረቶች ይልቅ፣ የምዕራባውያኑ ለዩክሬን ‹‹አለንልሽ›› የሚለው ድጋፍ ማየሉ አገሮቹ ከሰላማዊ መፍትሔ ይልቅ ወደ ጦርነት እንዲገቡ አድርጓል፡፡ የካቲት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም በስድስት ቀናት ውስጥ ከ520 ሺሕ በላይ ዜጎች ዩክሬንን ለቀው ተሰደዋል ሲል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አስታውቋል፡፡

በዩክሬንና በሩሲያ መካከል የተጀመረው ጦርነት የአሜሪካና የምዕራውያኑ ፍላጎት ያለበትና ቀድሞ በቃል ድጋፍ አሁን ላይ የጦር መሣሪያ በመላክ የተጠናከረ ቢሆንም፣ ሁለቱ አገሮች የመጀመርያ ውይይታቸውን የካቲት 21 ቀን በቤላሩስ አድርገዋል፡፡

በቅድሚያ ተኩስ አቁም ማድረግ ላይ ያተኩራል የተባለው ውይይት በቤላሩስ መደረጉን የዘገበው አርቲ፣ በምን ጉዳዮች ላይ እንደተወያዩ ዝርዝር መረጃ አለመገኘቱንና ቀጣይ ውይይት እንደሚደረግ አስፍሯል፡፡

ጦርነቱን አቁሞ ወደ ሰላም ለመምጣት ዩክሬንና ሩሲያ የመጀመርያውን ድርድር ካደረጉ በኋላ ደግሞ የኔቶ አባል አገሮች ለዩክሬን የጦር ጀት ጨምሮ የተለያዩ መሣሪያዎችን እንደሚልኩ ማስታወቅ ጀምረዋል፡፡ በሩሲያ ላይ የማዕቀብ ናዳ እያወረዱም ነው፡፡

ይህ ግን ዩክሬንን ትጥቅ እናስፈታለን፣ በዩክሬን የሚኖሩ የሩሲያ ዜጎችና ደጋፊዎች ላይ የሚሳዩትን በደልና ዘረኝነታቸውን እናስቆማለን ለሚሉት ፑቲን አሁን ላይ ለውጥ አላመጣም፡፡

ይልቁንም ጦርነቱ ቀድሞ በኮቪድ-19 የተጎዳውን የዓለም ኢኮኖሚ ሌላ አደጋ ውስጥ ከቶታል፡፡ የነዳጅ ዋጋ በበርሜል መጨመሩ የተሰማው ጦርነቱ በተጀመረ በደቂቃዎች ውስጥ ነው፡፡ ይህ ጫና በኢኮኖሚ ወደ ኋላ የቀሩትን የአፍሪካና የሌሎች አኅጉሮች ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የበለፀጉትን ምዕራባውያንንም ጭምር ነው፡፡

ምዕራባውያን በሩሲያ የፋይናንስ ተቋማትና የንግድ ልውውጥ ላይ የጣሉት ማዕቀብ፣ ራሳቸውንም ሆነ ሌሎች አገሮችን የሚጎዳ ስለመሆኑ የተለያዩ የኢኮኖሚ ተንታኞች እየተናገሩ  ነው፡፡

በዓለም ሕዝብ ላይ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት የሚያባብሰው ይህ ጦርነት፣ ለሩሲያና ለዩክሬን የሚወግኑ ወገኖችን በቀጥታና በተዘዋዋሪ የሚያሳትፍ መሆኑ ሌላው የችግሩ አባባሽ ምክንያት ነው፡፡ 

(ጥንቅር በምሕረት ሞገስ)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...