በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእስር ላይ የነበሩ የጉሙዝ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) የተባለው ታጣቂ ቡድን ሦስት አመራሮችና በርካታ አባላት፣ በመንግሥት ውሳኔ መፈታታቸው ተገለጸ፡፡
ከእስር የተፈቱት የጉሕዴን አመራሮች ሊቀመንበሩ ግራኝ ጉደታ፣ ምክትሉ ደርጉ ፈረንጅና የድርጅቱ ጸሐፊ መሆናቸው ታውቋል፡፡ የታጣቂዎቹ አመራሮችና አባላት የተፈቱት የካቲት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ጫካ ከነበሩት ታጣቂዎች ጋር ዕርቅ ለመፈጸም ለቀናት የሚቆይ ባህላዊ ሥርዓት ማካሄዱን፣ የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ፃፊዎ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥት ታጣቂዎች በሚገኙበት የካማሺ ዞን አስተዳደር በኩል በአገር ሽግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች የሚመራ ንግግር ከታጣቂዎች ጋር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በካማሺ ዞን በኩል የተወከሉት ሽማግሌዎች ታጣቂዎቹ ወደሚገኙበት ያሶ ወረዳ በመሄድ ጥያቄዎቻቸውን ከተቀበሉ በኋላ ከዞኑ አመራሮች፣ እንዲሁም በዞኑ ከሚገኙና ከክልሉ የፀጥታ አካላት ጋር መወያየታቸው ታውቋል፡፡
ታጣቂዎቹ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ማስታወቃቸው የተገለጸ ሲሆን፣ እንዲመለሱላቸው የሚፈልጓቸውን የተለያዩ ጥያዌዎችንም አንስተው ነበር፡፡ በእስር ላይ የሚገኙ አባላቶቻቸው እንዲፈቱ፣ ከፌዴራልና ከሌሎች ክልሎች የተውጣጡ በክልሉ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ክልሉን ለቀው እንዲወጡ የሚለው ታጣቂዎቹ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ናቸው፡፡
የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ፣ ታጣቂዎቹ ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት በመግለጻቸውና ግጭት ባለባቸው የካማሺና መተከል ዞኖች ሰላም ለማምጣት ቃል በመግባታቸው እስረኞቹ እንደተፈቱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ታሳሪዎቹ ከመፈታታቸው በፊት የክልሉ መንግሥት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር መወያየቱን የገለጸት ኃላፊው፣ በውሳኔው ላይ የፌዴራል መንግሥቱም ተሳትፎ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የሚገኙ ታጣቂዎች የሚያደርሷቸውን ጥቃቶች ለመቆጣጠር የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የሲዳማና የደቡብ ክልሎች ልዩ ኃይሎች፣ እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ተሰማርተዋል፡፡ የካማሺ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብጅጋ ታጣቂዎቹ እነዚህ ኃይሎች እንዲወጡ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዳገኘና ታጣቂዎቹም እንደተስማሙበት ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ዋና አስተዳዳሪው ምላሹን በተመለከተ፣ ‹‹አሁን ማብራሪያ መስጠት ጥሩ አይሆንም፤›› በማለት ጥያቄው በምን ዓይነት መልኩ እንደተመለሰ ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
በካማሺ ዞን የሚገኘውን ኮማንድ ፖስት የሚመሩት ኮሎኔል ዓለሙ በሽር የታጣቂዎቹን ጥያቄ በተመለከተ፣ ‹‹የሌሎቹን አላውቅም፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊትን ግን ማስወጣት አይቻልም፡፡ ይኼ አይመለስላቸውም እርግጠኛ ነኝ፤›› በማለት ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡
በካማሺ ዞን ካማሺ ከተማ ላይ ከተፈጸመው የዕርቅ ሒደት በኋላ የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንደሚከናወን ያስረዱት አቶ ብጅጋ፣ ተፈናቃዮችን ወደ መኖሪያቸው መመለስና ቀጣይ የልማት ሥራዎች ማከናወን ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ በታጣቂዎቹና በክልሉ መንግሥት መካከል ስምምነት ማድረግም ወደ ፊት የሚፈጸም ስለመሆኑ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ከክልሉ መንግሥት ጋር ባደረጉት ስምምነት አማካይነት ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ተመልሰው የነበሩት በክልሉ የሚገኙት ታጣቂዎች፣ በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ ወራት ላይ ስምምነቱን በመጣስ ተመልሰው ወደ ጫካ ገብተው ቆይተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ከቅርብ ወራት በፊት የመጨረሻ ዕርምጃ ሊወስድ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገለጽና ከዕርምጃው በፊት ታጣቂዎች እጅ እንዲሰጡ ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ የክልሉን ነዋሪዎች ከታጣቂዎች ለመለየት በሚልም ታጣቂች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች የነበሩ ነዋሪዎች ወደ ከተሞች ሲሰበስብ እንደነበር ይታወሳል፡፡