Wednesday, February 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በወቅታዊ ጉዳዮች ምክንያት የተዘጋው ሳፋየር አዲስ ሆቴል ተከፈተ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በቦሌ ክፍለ ከተማ ከቦሌ መድሃኒዓለም ወደ አትላስ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው ሳፋር አዲስ ሆቴል በወቅታዊ ጉዳዮች በሚል ምክንያት ለሦስት ወራት ተዘግቶ ከቆየ በኋላ “ምንም ችግር የለበትም” በመባሉ ከማክሰኞ የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተከፍቷል፡፡

ባለ አራት ኮከቦ ሳፋየር አዲስ ኅዳር 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በክፍለ ከተማው ወረዳ ሦስት ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት ከመታሸጉ በፊት ከሦስት ላላነሱ ጊዜያት በፀጥታ ኃይሎች ተፈትሾ ነበር፡፡ የመጨረሻው ፍተሻ ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ከተደረገበት በኋላም በሁለተኛው ቀን ሆቴሉ ታሽጓል፡፡

ሳፋየር አዲስ ሲዘጋም ሆነ ሲከፈት ምንም ዓይነት ገለጻ ለሆቴሉ አስተዳደር እንዳልተደረገ ለሪፖርተር የተናገሩት የሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ወርቁ፣ ሆቴሉ በተዘጋባቸው ሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ክስም እንዳልተመሠረተ አስታውቀዋል፡፡ በሆቴሉ ውስጥ በተደረጉት ሁሉም ፍተሻዎች ምንም ነገር አለመገኘቱንና ይኼንን የሚገልጽ ፊርማ ፍተሻውን ያካሄዱ አካላትና የሆቴሉ አስተደዳር መፈራረማቸውን ያስታወሱት አቶ ዮናስ በዚህም ምክንያት “በቶሎ ይከፈታል” በሚል ጉዳዩን ሲከታተሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኙ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ከወራት በፊት በተለያዩ ምክንያቶች እንዲዘጉ መደረጋቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ሳፋየር አዲስ ሆቴል በሚገኝበት ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሦስት ከተዘጉት ሆቴሎች መካከል ካሌብና ሀርመኒ ሆቴሎች ይገኙበታል፡፡ ወረዳው እስከ ኅዳር 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ 100 ገደማ የሚሆኑ እንደ ሆቴል፣ ባርና ሬስቶራንት ያሉ ቤቶች ላይ የማሸግ ዕርምጃ ወስዶ የነበረ ሲሆን ሳፋየር አዲስ በተዘጋበት ሰሞን 12 የንግድ ቤቶች እንዲዘጉ ተደርጎ ነበር፡፡ የማሸግ ዕርምጃ ከተወሰደባቸው ቤቶች ውስጥ የተወሰኑት የተዘጉት ከፀጥታ አካላት በመጣ ትዕዛዝ መሆኑ ታውቋል፡፡

ሳፋየር አዲስ በምን ምክንያት እንደተዘጋ ባይገለጽም፣ ‹‹በወቅታዊ ሁኔታ›› ዕርምጃ የተወሰደባቸው አብዛኞቹ ሆቴሎች ‹‹በአሸባሪነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው፣ እንዲሁም ድጋፍ ያደርጋሉ›› ተብሎ በመጠርጠራቸው መሆኑን  የወረዳው ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ጀባሞ ከዚህ ቀደም ለሪፖርተር ተናግረው ነበር፡፡

የወረዳው ንግድና ኢንደስትሪ ልማት ጽሕፈት ቤት ሆቴሉን የከፈተው የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ በክፍለ ከተማው በኩል በደብዳቤ ስለደረሰው መሆኑን የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጆቴ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ደቻሳ ከወቅታዊ አገራዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችል የኢኮኖሚ አሻጥርን ቀድሞ ለመከላከል በተቋቋመው ግብረ ኃይል ጥያቄ ሆቴሉ እንደታሸገ አስታውሰው ግብረ ኃይሉ ጥርጣሬ እንደነበረው አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና ግብረ ኃይሉ ለወራት ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ ለሥጋት የሚያጋልጥ ችግር እንደሌለበት እንዲሁም በንግድ ሕጉ መሠረትም አስፈላጊውን ያሟላ መሆኑን በደብዳቤ በመግለጽ ሆቴሉ እንዲከፈት ሰኞ የካቲት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የተጻፈ ደብዳቤ መላኩን አስታውቀዋል፡፡ ይኼንንም ተከትሎ በማግሥቱ ሆቴሉ እንዲከፈት መደረጉን አክለዋል፡፡

ይሁንና ሳፋየር አዲስ በምንም ምክንያት እንደተጠረጠረ የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡ በ1,300 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተገነባበው ሆቴሉ 130 የመኝታ ክፍሎች፣ ሁለት ሬስቶራንቶች ሦስት ባሮች፣ ጂምናዚየም፣ ስፓና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን ያያዘ ነው፡፡ ሆቴሉ ከመዘጋቱ አስቀድሞ በአማካይ 60 በመቶ የሚሆኑት የሆቴሉ ክፍሎች በእንግዳ ይያዙ እንደነበር የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ አቶ ዮናስ ሆቴሉ በድጋሚ ከተከፈተ በኋላ ባሉት ቀናት ወደ ሆቴሉ የሚመጡ የደንበኞች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች