የኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ውኃ ከሚያርፍበት 123,189 ሔክታር ሪዘርቬየር (ውኃ መያዣ) ቦታ ደን ምንጣሮ ጋር በተያያዘ ከ1.983 ቢሊዮን ብር በላይ የሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሸን (ሜቴክ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ሙሉ ወልደ ገብርኤል፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ አዜብ አስናቀ (ኢንጂነር) ከተከሰሱበት የሙስና ወንጀል መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ ሙስና ወንጀል ችሎት የካቲት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ብይን ሰጠ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአጠቃላይ 50 ተከሳሾች ላይ ክስ መሥርቶ ላለፉት ሦስት ዓመታት ሲከራከር የከረመ ሲሆን፣ ክርክሩን በአካል ተገኝተው የተከራከሩት ጥቂት ሲሆኑ ወ/ሮ አዜብ (ኢንጂነር)ን ጨምሮ በርካቶች ክሳቸው የቀጠለው በሌሉበት ነበር፡፡
ክስ ከተመሠረተባቸው ውስጥ 38ቱ የደን ምንጣሮውን ለመሥራት ከሜቴክ ጋር ውል ፈጽመው ይሠራሉ የተባሉ ማኅበራት ሲሆኑ፣ ሜቴክ ሥራውን ለማሠራት ኅዳር 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ተጨማሪ እሴት ታክስን ሳይጨምር ከ5.1 ቢሊዮን ብር በላይ ውል ተፈጽሞ የውሉን 50 በመቶ ከ2.579 ቢሊዮን ብር ብላይ ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉን ዓቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ ያስረዳል፡፡
ሥራው መጠናቀቅ ያለበት በሁለት ዓመት ውስጥ ማለትም ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ሥራው የተሠራው እስከ ግንቦት 7 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የክፍያውን 31.7 በመቶ ብቻ መሆኑን ወይም ከውሉ 50 በመቶ ውስጥ 23 በመቶ ብቻ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቷል፡፡ ኮርፖሬሸኑ ደን እንዲመነጥሩ ለተዋዋላቸው ማኅበራት ከተቀበለው 50 በመቶ ክፍያ ውስጥ 23 በመቶውን ወይም ከ595.3 ሚሊዮን ብር መሆኑንና ቀሪውን ከ1.983 ሚሊዮን ብር በላይ ምን ላይ እንዳዋለው እንደማይታወቅ ክሱ ያብራራል፡፡
ወ/ሮ አዜብ (ኢንጂነር) እና ሌሎች ሦስት ተከሳሾች ከፍተኛ የተቋሙ ኃላፊዎችም ደግሞ ከሜቴክ ጋር ለህዳሴ ግድቡ ውኃ መያዣ ቦታ ደን ምንጣሮ ውል መፈጸማቸውንና ከ5.15 ቢሊዮን ብር መከፈሉን እያወቁና የተሠራውንና ያልተሠራውን የምንጣሮ ሥራ በመለየት ዕርምጃ መውሰድ ሲገባቸው፣ እንዲሁም ሥራው በውሉ መሠረት አለመፈጸሙን እያወቁ ውሉን በማሻሻል የመጀመርያ ዙር ሥራ 50 በመቶ ሲፈጸም የክፍያ ውሉን 30 በመቶ መክፈል ሲገባቸው፣ ባሻሻሉት ውል መሠረት 20 በመቶ በመጨመር ተጨማሪ ከ1.031 ቢሊዮን ብር ያላግባብ እንዲከፈል ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አብራርቶ ሲከራከር ቆይቷል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በርካታ ምስክሮችን አቅርቦ ያሰማ ሲሆን፣ ኮሎኔል ሙሉና ወ/ሮ አዜብ (ኢንጂነር)ን ጨምሮ ከሰባት በላይ ተከሳሾች ላይ ያቀረባቸው ምስክሮች እንደ ክሱ ባለማስረዳታቸው፣ ተከሳሾቹ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤት ብይን ሰጥቷል፡፡
ኮሎኔል ለተብርሃን ደሞዝ የተባሉ በሜቴክ የኮርፖሬት ኒው ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊ ክስ ሲቋረጥ፣ የሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው (የደን ምንጠራ ላይ ተሰማርተው ከነበሩት ማኅበራት ውስጥ አንዱ የእሳቸው ነበር) ስላልተመሰከረባቸው በነፃ ተሰናብተዋል፡፡
ኮሎኔል ሙሉ በሌላ ክስ ስለሚፈለጉ በነፃ ቢሰናቱም ከእስር አልተፈቱም፡፡ ሌሎች ዓቃቤ ሕግ እንዲከሱ ያስመሰከረባቸው ተከሳሾች እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ወ/ሮ አዜብ (ኢንጂነር) ከክሱ ጋር በተያያዘ ከአገር ውስጥ ወጥተው በውጭ እንደሚኖሩ መገለጹ ይታወሳል፡፡ ሰሞኑን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት አስመልክቶ በጉባ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ አዜብ (ኢንጂነር)ን ከሥራቸው ጋር በተያያዘ ማመሥገናቸው ይታወሳል፡፡