Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሰላም ማስከበር ሥራችን ውጤታማ ባይሆን ኖሮ ቁጭ ብለን መነጋገር ይከብደን ነበር›› ሙላቱ ወርዶፋ (ረዳት ኮሚሽነር)፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር

ሙላቱ ወርዶፋ (ረዳት ኮሚሽነር) የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ለሚዲያ ቅርብ መሆኑንና መረጃም ከልክሎ አያውቅም ይላሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን በማጋነንና ለፖለቲካ ፍላጎት አጣሞ በማቅረብ የተጠመዱ ሚዲያዎች ብዙ ናቸው ሲሉም ይናገራሉ፡፡ የኦሮሚያ ፖሊስ ወንጀለኞችን የማፅዳት ጥረት ሳይሆን፣ የወንጀለኞች ጥቃት ተጋኖ እንደሚዘገብም ይከራከራሉ፡፡ በኦሮሚያ ክልል ስላለው የሕግ ማስከበርና የፀጥታ ሥራ፣ በክልሉ በየጊዜው የሚሰማው የንፁኃን ዜጎች መቀጠፍ ምክንያት ምን እንደሆነ፣ የክልሉ የፀጥታ ኃይል በተለይ እሳቸው በኃላፊነት እየሠሩበት ያሉት የኦሮሚያ ፖሊስ የዜጎችን ሕይወት ከሕልፈት ለመታደግ አቅሙ አለው ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ጭምር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በክልሉ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው እንዴት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ ስድስት ኪሎ በሚገኘው የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መምርያ በአካል ከተገኘው ዮናስ አማረ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦሮሚያ ክልልን የፀጥታ ችግር በተመለከተ የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ቢያብራሩልን፡፡ በክልሉ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ጎልቶ ይታያል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች ሰዎች ይገደላሉ፣ ከዚህ አንፃር ኮሚሽናችሁ ምን እየሠራ ነው?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- በኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ሕግን ለማስከበርና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ የፖሊስ ዋና ተልዕኮ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ በመሆኑ፣ ለዚህ የሚረዱ ሥራዎች ላይ አተኩረን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ሕዝቡ የራሱን አካባቢ ሰላም ለማረጋገጥ እንዲችል ስለሕግ፣ እንዲሁም ስለወቅታዊ ሁኔታዎች ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እንሠራለን፡፡ ከዚህ ባለፈ ሕዝቡ ወንጀለኞችን እንዲያጋልጥና ማስረጃዎችን በመስጠት እንዲተባበር፣ ግንዛቤዎችን የመስጠት ሥራዎችም ስንሠራ ነው የቆየነው፡፡

ይህን መነሻ በማድረግም በየአካባቢው ኅብረተሰቡን በማደራጀት ከፖሊስ ጋር ተቀናጅቶ የራሱን ሰላም እንዲጠብቅ የማድረግ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ ለዚህ የሚረዱ ሥልጠናዎችም ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡ በእያንዳንዱ ቀበሌ አደረጃጀት በመፍጠር ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ የአካባቢውን ሰላም እንዲያስከብር የሚያስችሉ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ሥራም እየተሠራ ይገኛል፡፡ ይህን መሰል ኅብረተሰቡን ያደራጀ የፖሊስ አገልግሎት በከተሞች አካባቢ ሙሉ ሽፋን ተሰጥቶታል፡፡ በገጠር አካባቢም ይህንኑ አደረጃጀት ለመፍጠር በየቀበሌው እየተሠራ ነው፡፡

በ2013 ዓ.ም. የሥርዓቱ ጋሻ ተብሎ በኅብረተሰቡ ውስጥ ወንጀለኞች መሸሸግ እንዳይችሉ ለማድረግና ሕዝቡ የራሱን ሰላም እንዲጠብቅ የሚያስችሉ ፖሊሳዊ ሥልጠናዎች ሰጥተናል፡፡ በአጠቃላይ በገጠሩም፣ በከተማውም ሰላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል፣ አደረጃጀቶችም ተፈጥረዋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢ ፀጥታ ጥበቃን በፕሮግራም፣ በተደራጀና ሥርዓት ባለው መንገድ ለማካሄድ የሚያስችል ሥራም ተሠርቷል፡፡ በየአካባቢው ተደራጅቶ የቅኝት/ፓትሮል የማድረግ ሥራ ከሕዝቡ ጋር እየተከናወነ ነው፡፡ ወንጀልን የመከላከል ሥራ የሚያከናውን የተደራጀ ኃይል መፍጠር ተችሏል፡፡

ከወንጀለኞችና ከፀረ ሰላም ኃይሎች ፍላጎት አንፃር የተሠራው ሥራ ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህን መሰል ሥርዓት በመዘርጋታችንና የፀጥታ አደረጃጀት በመፍጠራችን በመሀል ኦሮሚያ፣ በደቡብ ምሥራቅ፣ በደቡብ ምዕራብ ኦሮሚያዎች አካባቢ ጥሩ የሰላም ሁኔታ መታየት ችሏል፡፡ በጅማ፣ በኢሉአባቦር በመሀል አገር፣ በሌሎችም ውጤታማ የፀጥታ አደረጃጀት መፍጠር በተቻለባቸው ቦታዎች የሰላም ሁኔታው የተሻለ ሆኗል፡፡

ከእነዚህ ውጪ ባሉ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ኦሮሚያ፣ ምዕራብ ሸዋና ሰሜን ሸዋ፣ እንዲሁም በደቡብ ኦሮሚያ በሁለቱ የጉጂ ዞኖች አካባቢ የፀጥታ ችግሮች እያጋጠሙ ነው፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ በኩል ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት በአማራና በአፋር አካባቢዎች የፈጸመው ወረራን መመከት ቢቻልም ጦርነቱ ግን አልተጠናቀቀም፡፡ ከሕወሓት ጋር በጥምረት የሚሠራው ደግሞ በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰው የሕወሓት መጋለቢያ ፈረስ የሆነው የኦነግ ሸኔ ቡድን ነው፡፡ ሕወሓት በአማራና በአፋር አካባቢዎች የሚፈጽማቸውን ዓይነት ወንጀሎች ኦነግ ሸኔም በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች እየፈጸመ ነው፡፡

ኦነግ ሸኔዎች ዝርፊያ በስፋት ያካሂዳሉ፣ አስገድደው ይደፍራሉ፣ ሰዎችን ይገድላሉ፣ መሠረተ ልማቶችን ማውደምና የመሳሰሉ ወንጀሎች እየፈጸሙ ነው፡፡ እነዚህን ወንጀሎች ለማስቆም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በሕወሓት ላይ እንደተወሰደው ሁሉ፣ በኦሮሚያም በኦነግ ሸኔ ላይ ዕርምጃ የመውሰድ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡ ኦነግ ሸኔም ሆነ ሕወሓት ማንንም የማይመርጡና ሁሉንም የሚገድሉ አጥፊ ቡድኖች ናቸው፡፡ ስለዚህ በእነዚህ ላይ መንግሥት በተለይ የፌዴራልና የክልል ፀጥታ አካላት በጋራ ተጣምረው ዕርምጃ እየወሰዱ ነው፡፡

በኦሮሚያ ክልል የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየሠራን ያለነውን ሥራ ብዙዎች አይዘግቡም፡፡ በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋና በምዕራብ ሸዋም ዕርምጃ እየወሰድን ነው፡፡ በወንጀለኞች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡ ይህን ሕግ የማስከበር ሥራ ከመዘገብ ይልቅ ግን ጠላት የሚያደርሳቸውን ጉዳቶች አጋኖ የማጮህ ዝንባሌ ነው ብዙ ጊዜ የሚታየው፡፡ ብሔርን ከብሔር ለማጋጨትና ጥላቻ ለመዝራት የሚሠሩ ኃይሎች አሉ፡፡ በተለይ የኦሮሞ ሕዝብን ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ለማጋጨት የሚጥሩ አሉ፡፡ በመሀል አለመተማመንና ጥላቻ ለመፍጠር ነጥሎ አንድ ወገን ብቻ እንደሞተና የጥቃት ዒላማ እንደሆነ ለማስመሰል የሚጥሩ ወገኖች አሉ፡፡

መታወቅ ያለበት ግን ኦነግ ሸኔም ሆነ ሕወሓት የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጠላቶች ናቸው፡፡ ሁለቱም የአገር ጠላት ናቸው፡፡ ኦነግ ሸኔ በኦሮሞ ላይም ዝርፊያ፣ ግድያና ሌላም ብዙ ችግር አድርሷል፡፡ ከላይ እንዳነሳሁት ይህን ችግር ለማድረቅ አሁን ኅብረተሰቡን ያሳተፈና ያደራጀ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው የሚገኘው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህን ሥራ ሚዲያው የማይዘግበው ለምን ይመስልዎታል? በእናንተ በኩል ለሚዲያው ቅርብ ነን ብላችሁ ታምናላችሁ?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- አዎ፣ ለሚዲያ ቅርብ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ከእናንተም ሆነ ከሌሎች በርካታ የመንግሥት ተቋማት በኩል ፈጣን መረጃ ለማግኘት ብዙ ሚዲያዎች መቸገራቸውን መስማት የተለመደ ነው፡፡ በኦንላይን ሚዲያዎች በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ያልተጨበጡ መረጃዎች ሲሠራጩ ከእናንተና ከሚመለከታቸው አካላት በኩል ተጨባጭ መረጃ ፈልጎ ለማቅረብና እውነተኛ መረጃዎችን ለሕዝብ ለማድረስ መደበኛው ሚዲያ መቸገሩ የተለመደ ነው፡፡

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- እኛ መረጃ ከልክለን አናውቅም፡፡ እናንተም ቢሆን ስትመጡ ያስተናገድነው በተገቢው መንገድ ነው፡፡ መረጃዎች ሲኖሩን በኦቢኤን፣ በፋናም በኢቲቪም በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ ነው ያለው፡፡ በኮሚሽነራችንም ሆነ በኮሙዩኒኬሽናችን በኩል መረጃ እየተሰጠ ነው ያለው፡፡ ከዚህ ውጪ ለመረጃ በራችን ዝግ እንደሆነና መረጃ እንደከለከልን ተደርጎ የሚቀርበው ነገር ከጀርባው ሌላ ዓላማ ያነገበ ነው፡፡ የሕዝብን ፍላጎትና የሕዝብን ሰላም አስቀድመው ሳይሆን፣ ከራሳቸው ፍላጎት ተነስተው የሚዘግቡ አሉ፡፡ የተለያዩ አመለካከቶችን በማቀራረብ፣ አገራዊ መግባባትንና አገራዊ አንድነትን ለመፍጠር አስበው ሳይሆን ተቆርቋሪ መስለው ሕዝቦችን ለማጋጨት የሚሠሩ ኃይሎች አሉ፡፡

እናንተ መገንዘብ ያለባችሁ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ምንድነው የሚለውን ነው እንጂ፣ ሆን ተብሎ መረጃ የሚከለከልበት አሠራር የለም፡፡ ሕዝብ በተጨባጭ ያለውን እውነታ እንዲገነዘብ መረጃ መድረስ አለበት፣ እኛም የምንፈልገው ነው፡፡ ነገሮችን ወደ ራሳችን ፍላጎት የምንስብ ከሆነ ግን ለሕዝቡ ትክክለኛ መረጃ አላደረስንም ማለት ነው፡፡ እውነተኛ መረጃ ለሕዝቡ እንዲደርስ 24 ሰዓት በራችን ክፍት ነው፡፡

አሁን በእነዚህ ወንጀለኞች ላይ ተገቢ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው ያለው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ለምሳሌ በቀን እስከ 300 ሰዎች እጃቸውን እየሰጡ ነው፡፡ በምዕራብና በደቡብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ብዙ ቦታዎች ከወንጀለኞቹ እየፀዱ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ዕርምጃ እየተወሰደባቸው ሲሆን፣ ከጥፋት ለመመለስ ዝግጁ የሆኑትን በአባ ገዳዎች፣ በአገር ሽማግሌዎች፣ በቤተሰቦቻቸውና በአካባቢው ኅብረተሰብ ዕርዳታ ትጥቅ ፈተው በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ በምሥራቅ ወለጋ አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለዚህ እንደ ምሳሌ ማየት ይቻላል፡፡ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን ከጥፋት እንዲመልሱ፣ አባ ገዳዎችና ሽማግሌዎች አጥፊዎችን እንዲመልሱ በተሰጣቸው ዕድል መሠረት፣ ለጥፋት መገልገያ የሆኑ ወጣቶች ከድርጊታቸው እንዲቆሙ ማድረግ ተችሏል፡፡

ይህ ሁሉ እየተሠራ ባለበት ግን በመሀል በአንዳንድ ቦታዎች ተስፋ የቆረጡ ኃይሎች አሰቃቂ ወንጀሎችን ሲፈጽሙ ይታያል፡፡ ይህንን ከእነ አካቴው ለማድረቅ ደግሞ በሁሉም የኦሮሚያ አካባቢዎች የተቀናጀ ኦፕሬሽን በማድረግ ክልሉን ከእነዚህ ኃይሎች የማፅዳት ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ለምሳሌ ቄለም ወለጋ ጊዳሚ አካባቢ ብዙ ቦታዎችን ማፅዳት ችለናል፡፡ ነገር ግን አሁንም የቀረ በመኖሩ ይህ ተስፋ የቆረጠ ኃይል ደግሞ ድንገተኛ ዕርምጃዎች ሊወስድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ወንጀለኞችን ተከታትሎ የማዳንና ዕርምጃ የመውሰድ ሥራ በምዕራብ ወለጋ፣ በምዕራብ ሸዋ፣ በሰሜን ሸዋም ሆነ በሆሮ ጉዱሩና በሁሉም አካባቢዎች መሠራት አለበት ብለን ነው የምናምነው፡፡ መፍትሔው ከሕዝባችን ጋር በአንድ አመለካከት ተግባብተንና ተናበን በመሥራት ወንጀለኞችን መዋጋት ነው፡፡ የትኛውም ሚዲያ ለዚህ ዕገዛ ማድረግ አለበት፡፡ አንዳንዶች በቂ መረጃ ሳይኖራቸው የውሸት ፕሮፖጋንዳ ያስተላልፋሉ፣ ይህ መቆም አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በከረዩ አባ ገዳዎች ግድያ የኦሮሚያ የፀጥታ አካላት መሳተፋቸውን የሚጠቁም ሪፖርት አቅርቧል፡፡ የኦሮሚያ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን በሰጠው መግለጫ በክልሉ ለፀጥታ መደፍረስ እጃቸው ያለበት የፀጥታ አካላትና አመራሮች እንዳሉ አስታውቋል፡፡ ይኼን እንዴት ትገመግሙታላችሁ? በመዋቅሩ ውስጥ ፀረ ሰላም ኃይሎች ካሉ የማፅዳት ሥራ እየሠራችሁ ነው ወይ?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- ጠላት ፍላጎቱን ለማሳካት በተለያዩ መንገዶች ወደ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ችግር ያለበትን አካል በግምገማ ዕርምጃ የመውሰድ ሥራ ሠርተናል፡፡ ውስጣችንን እያጠራንና አሠራራችንን በየጊዜው እያረምን ነው የምንሄደው፡፡ ከዚህ ውጪ የከረዩ አባ ገዳዎችን በሚመለከት ጉዳዩ እየተጣራ ነው ያለው፡፡ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የራሱን መግለጫ ሊያወጣ ይችለል፡፡ በእኛ በኩል ግን የምርመራ ቡድን ተደራጅቶ ጉዳዩን እየመረመረ ሲሆን፣ የተጣራ መረጃ ይዘን መግለጫ የምንሰጥበት ይሆናል፡፡ ባላለቀና በምርመራ ሒደት ላይ ባለ ነገር ብዙ ማለት አንችልም፡፡ እናንተም ቢሆን እንደ ሚዲያ ጉዳዩ ተጣርቶ ሲያልቅ መረጃውን ብትጠይቁ ነው የሚሻለው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለከረዩ አባ ገዳዎች የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ላወጣው ሪፖርት ምን መልስ አላችሁ? ከዚህ ቀደም በደንቢዶሎ አማኑኤል የተባለ ወጣት በፀጥታ ሰዎች ተገድሏል መባሉ በፀጥታ ተቋማት ላይ የሚቀርበውን ክስ አያጠናክርም ወይ?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- የከረዩ አባ ገዳዎች ጉዳይ ተጣርቶ ምርመራው ሲጠናቀቅ መረጃ እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡ ከዚህ ውጪ ጉዳዩ ውስጥ ገብቼ የምናገረው ነገር አይኖርም፡፡ ወንጀለኞች ይኖራሉ፣ ወንጀለኞችን ተከታትሎ ዕርምጃ የመውሰዱ ሒደት እንዴት እንደነበር የሚገለጽበት አግባብም አለ፡፡ በየጊዜው በወንጀሎች ላይ ስለተወሰዱ ዕርምጃዎች ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ደጋግመን መግለጫ ወደ ሰጠንባቸው ያለፉ ጉዳዮች በመመለስ ነገሮችን ማንሳት አዲስ ምላሽ አያመጣም፡፡ ሁለት ዓመታት ያስቆጠረና በወቅቱ መልስ የተሰጠውን ጉዳይ ማንሳቱ የተለየ መልስ አያስገኝም፡፡

ሪፖርተር፡- አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ ችግር ደጋግሞ ሲከሰት አያሳስብም ወይ ከሚል ነው ጉዳዩን ያነሳነው?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- ተደጋጋሚ አይደለም፡፡ ጠላት በየጊዜው ወንጀል የሚፈጽመው የራሱን ፍላጎት ለማሳካት ነው፡፡ ጠላት ነው ይህን እየፈጸመ ያለው፡፡ በየከተማው ‹‹አባቶርቤ›› የሚባል ቡድን እያስገባ ስንት ሰው ነው እየፈጀ ያለው፡፡ ይህን የጠላት ወንጀል አውጥቶ የሚናገር ጋዜጠኛም እኮ የለም፡፡ ከእነዚህ አባቶርቤዎች ብዙዎቹን በቁጥጥር ሥር አውለን ለሕግ በማቅረብ ውሳኔ እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ እሱም ከአባቶርቤዎቹ አንዱ ነው፣ ባለፈው ጊዜም ይህንኑ ተናግረናል፡፡ ነገር ግን ነገሩን ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎ የማቅረብ ነገር ይታያል፡፡ ጥያቄዎቹም ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ሳይሆን ከዚያ ዓይነቱ አካሄድ የሚነሱ ይመስላል፡፡

ሪፖርተር፡- የመንገድ መዘጋትን በተመለከተ በቅርቡ አማራና ኦሮሚያን የሚያገናኘው ዋናው የባህር ዳር መንገድ በፀጥታ ችግር መዘጋቱ ይታወቃልና አሁን ያለበት ሁኔታን ቢያስረዱን?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- የሆነ ሽፍታ ተኩሶ አንድ ሾፌር ተጎድቷል፡፡ ነገር ግን ወዲያው የፀጥታ ኃይል በአካባቢው ደርሶ መንገዱ ተከፍቷል፡፡ ለአምስት ደቂቃም አልተዘጋም፡፡ እንዲህ ዓይነት ድንገተኛ አደጋዎች በየአካባቢው አልፎ አልፎ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ የሕወሓትና የኦነግ ሸኔ ሴራ ደግሞ የተወሳሰበ ነው፡፡ እኛ ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር ማድረግ የሚገባንን ሁሉ እያደረግን መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በኦሮሚያ በአንዳንድ አካባቢዎች የፀጥታ ችግር መኖሩን ኮሚሽናችሁም የሚቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ የኦሮሚያ የፀጥታ ተቋማትን መገምገም እንደሚቻለው በቂ ሥልጠና የወሰደ፣ ጠንካራ የሰው ኃይልና የሎጂስቲክስ አደረጃጀት ያለው ተቋም ክልሉ ለመገንባት ጥረት እያደረገ መሆኑም ይታመናል፡፡ ነገር ግን በክልሉ በየቦታው የሰው ሕይወት ይጠፋል፣ የፀጥታ ችግርም ደጋግሞ ይፈጠራል፡፡ ይህ ለምን ይሆናል? የክልሉን ፀጥታ ለመቆጣጠር አቅቷችኋል? ከአቅማችሁ በላይ ሆኗል ወይ?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- አንደኛው በሕወሓት የታወጀብን ጦርነት ነው፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ የሕወሓትን ተልዕኮ ወስደው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች አሉ፡፡ ይህን ለመግታት የእኛ ኃይል ራሱን አደራጅቶና ሥልጠና ወስዶ ተገቢውን ኦፕሬሽን እያደረገ ነው ያለው፡፡ የክልላችን ፖሊስ ከሌሎች የክልሉና የፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር ተባብሮ በተቀናጀ መንገድ ባደረገው የፀረ ሰላም ኃይሎችን ማፅዳት ዕርምጃ በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ እየመጣ ነው ያለው፡፡ እነዚህ ተስፋ የቆረጡ የሽብር ኃይሎች ግን በዚህ መሀል በአንዳንድ አካባቢዎች የሚወስዱት ሰውን የመግደል፣ ንብረት የመዝረፍና ሌላም ድርጊት ይከሰታል፡፡

ይህን ተገንዝበን ፈጣን ዕርምጃዎችን እየወሰድን እንገኛለን፡፡ ለምሳሌ በምሥራቅ ወለጋ የተዘረፉ መኪኖችና ነዳጅ ጭምር አስመልሰናል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች የጠላት እንቅስቃሴ ቢኖርም፣ የማፅዳት ሥራችን ግን በተገቢው ሁኔታ እየተካሄደ መሆኑን ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ በቄለም ወለጋ ከጠላት የፀዱ ቦታዎች አሉ፡፡ ነገር ግን ከአካባቢው እነዚህ ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ ካልጠፉ በስተቀር ሰላም እንደማይመጣ አውቀን ዕርምጃ መውሰዳችንን ቀጥለናል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖም አልፎ አልፎ በየቦታው የሚያጋጥሙ ጥቃቶች ለጊዜው ችግር እየፈጠሩብን ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያ የአገሪቱ ዕምብርት ነው፡፡ ኦሮሚያ ሰላም ካልሆነ አገር ሰላም ሊሆን አይችልም ተብሎ ስለሚታመን፣ በዚህ መሠረት ክልሉን ሰላማዊ ለማድረግ ምን እየሠራችሁ ነው? ከፌዴራልም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር ተባብሮ በመሥራት በኩልስ ምን እየተሠራ ነው?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- አንተ እንዳስቀመጥከው የኦሮሚያ ክልል ሰላም የአገር ሰላም ነው የሚለው አረዳድ በሁሉም ወገን ዘንድ ግንዛቤው መፈጠር አለበት፡፡ እያንዳንዱ ጋዜጠኛ፣ ሚዲያ፣ ፖለቲከኛም ሆነ አክቲቪስት የኦሮሚያ ክልልን ችግር በመረዳት ከራሱ የፖለቲካ ፍላጎት ጋር አዛምዶ በተዛባ መንገድ ከማቅረብ ይልቅ፣ ችግሩ የአገርና የጋራ ጉዳይ ነው ብሎ ሲያምን ችግሩን ለመፍታት ቀላል ይሆናል፡፡ በዩቲዩብ ላይ ጉዳዩን ለጥጦና አዛብቶ ከማቅረብ ይልቅ በጋራ ብንሠራ ውጤታማ ልንሆን እንችላለን፡፡ በተጨባጭ እንደሚታየውም በእኛ በኩል ይህ እየተደረገ ነው፡፡ የሰላም ማስከበር ሥራችን ውጤታማ ባይሆን ኖሮ እኔና አንተም እዚህ ቁጭ ብለን መነጋገር ይከብደን ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ፣ በመሀል ኦሮሚያ፣ በምሥራቅ በኦሮሚያ፣ በባሌ፣ በአርሲ፣ በጅማና በኢሉአባቦር አካባቢ ጥሩ ሰላም አለ፡፡ ይህ የተሳካው ደግሞ ቅድም ያልኳቸውን ሥራዎች በመሥራታችን ነው፡፡ በአንዳንድ የፀጥታ ችግር አለባቸው ተብለው በተለዩ ቦታዎችም ይህን አጠናክረን መሥራት ከቻልን ሰላምን ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ኃይላችን የሕዝቡን ፍላጎት ተከትሎ ለሰላም ከሠራ ስኬቱ ይመጣል፡፡ ከፌዴራል ኃይል ጋርም በቅንጅት መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ፣ የፀጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የጋራ ኦፕሬሽኖች እያካሄድን ነው፡፡ በዚህ መንገድ የኦሮሚያ ክልልን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ መመለስ ይቻላል ብለን እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሮሚያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነ ክልል ነው ማለት ይቻላል፡፡ ኅብረተሰቡ ወጥቶ ለመግባት የሰላም ዋስትና ይፈልጋልና በተለይ ብሔርን ወይም ቋንቋና ሃይማኖትን መሠረት ያደረጉ ግጭቶች እንዳይፈጠሩና የሕዝቡን አብሮ የመኖር እሴት ለመጠበቅ ምን እየሠራችሁ ነው?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- ዜጎች በሰላም አብረው እንዲኖሩ ግንዛቤ እንሰጣለን፡፡ በተለይ የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲጠበቁ፣ እንዲሁም በሰላም አጠባበቅ ዙሪያ የሕግ ግንዛቤዎችን እንሰጣለን፡፡ ይህን የማኅበረሰቡን አብሮ የመኖር እሴት ለመጠበቅ በማኅበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትና በተለያዩ ሕዝብ አደረጃጀቶች ወደ ታች እስከ ቀበሌና ቀጣና ወርደን ብዙ ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡ ሕዝቡ የሥርዓቱ ጋሻ ነው ተብሎ ሥልጠና ወስዶና ተደራጅቶ አካባቢውን እየጠበቀ ነው ያለው፡፡ ይህ ሁሉ ሥራ ባይሠራ እኮ አንፃራዊ ሰላምም አይገኝም ነበር፡፡ የፓትሮል/ቅኝት ሥራ የሚያከናውኑ አደረጃጀቶች በየሠፈሩ መሥርተናል፡፡

ሕዝቡ እርስ በርስ ይተዋወቃል፡፡ መተማመን፣ መደጋገፍና መረዳዳት ሕዝቡ ውስጥ እንዲሰርፁ የሚያስችሉ ሥራዎችን እንሠራለን፡፡ አንዳንዴ የሚፈጠሩ ችግሮች ጥቂት ጽንፈኛ ኃይሎች እንጂ፣ ሕዝቡ እርስ በርሱ ጥላቻ እንደሌለው በደንብ ይታወቃል፡፡ ሕወሓት ጦርነት ሲከፍትብን ሕዝቡ እንዴት ነበር ምላሽ የሰጠው፡፡ የኦሮሚያ ወጣቶች በጦርነቱ ለመሠለፍ እንዴት ነበር አለን ብለው በነቂስ የወጡት፡፡ ሕዝቡ ሀብቱን ሳይሰስት ያለውን ለዘመቻው የሰጠውስ እንዴት ነበር፡፡ እነዚህ ሕዝቡን በጋራ እንዲቆም የሚያስችሉ ሥራዎች በመሠራታቸው ነበር አገሪቱ በሕዝቦቿ ተሳትፎ ከመፍረስ የተረፈችው፡፡ ኦነግ ሸኔና ሕወሓት አገር ለማፍረስ ነበር ሲንቀሳቀሱ የነበሩት፡፡ ዳሩ ግን ሕዝባችንን አደራጅተን የፀጥታ ሥራዎች ስለሠራን ዓላማቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የኦነግ ሸኔና የሕወሓት ፍላጎት ምንድነው? ሁለቱን ኃይሎች በጋራ ግንባር ያሠለፋቸው ምክንያት ምንድነው?

ሙላቱ (ረዳት ኮሚሽነር)፡- እኔ እንድናገረው ካልተፈለገ በስተቀር ፍላጎታቸው ደጋግሞ የተባለ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ አገር ማፍረስ ነው ግባቸው፡፡ ኦነግ ሸኔ ለዚህ ዓላማ ከሕወሓት በቀጥታ ትዕዛዝ የተቀበለ ኃይል ነው፡፡ ሁለቱም ተናበው አገር ለማፍረስ የሚጥሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ናቸው፡፡ ኦነግ ሸኔ መደበኛ ውጊያ ሳይሆን የሽምቅ ጥቃት ነው የሚከፍተው፡፡ አልፎ አልፎ አለሁ ለማለት ብቅ ይልና ባልታሰበ ሰዓትና ቦታ አደጋዎችን ይጥላል፡፡ ለምሳሌ የናይጄሪያው ቦኮ ሀራም ሲያፍን፣ ሲገድልና አደጋ ሲያደርስ የሚታየው በሽምቅ ነው፡፡ እነዚህም ልክ እንደዚያ ዓይነት ባህሪ ያላቸው ናቸው፡፡ አደጋ ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ከእናንተም ሆነ ከሕዝቡ ጋር ተባብረን በቅንጅት የማፅዳት ሥራ እንሠራለን እንጂ፣ የሆነ ነገር በተፈጠረ ቁጥር ለእነሱ የሚረዳ አፀፋ መስጠት መፍትሔ አይሆንም፡፡

ለምሳሌ ያህል በቄለም ወለጋ የፀጥታ ኃይልና የቀበሌ አመራሮች ለፀጥታ ሥራ ሲንቀሳቀሱ ጠላት አፈናቸው፡፡ ይህ ሲዘገብ ግን በውሸት ሌላ ብሔር ታፈነ ተብሎ ተስተጋባ፡፡ ይህን መሰል የሐሰት መረጃ ሥርጭትን ባንቀበል መልካም ነው፡፡ ባልሆነ መንገድ በሕዝቦች መካከል ቁርሾ ለመፍጠር የሚጥሩ ወገኖች አሉ፡፡ ይህ ሕዝብ ይህን አገር በጋራ ነው ጠብቆ ያቆየው፡፡ ይህች አገር የሁላችንም የጋራ አገር ናት፡፡ ለአንድ ቡድን የተሰጠ አይደለም፡፡ እኔ ከሌለሁ አገሩ ሊኖር አይችልም፣ እኔ ካልመራሁ ወይም ለእኔ ብቻ ካልተሰጠኝ ብሎ መነሳት አይበጅም፡፡ ሕወሓት እኔ የማልገዛት አገር መኖር የለባትም፣ ለማፍረስ ሲዖልም ቢሆን እገባለሁ ብሎ ነው የተነሳው፡፡ እነ ኦነግ ሸኔም ይህን የሕወሓትን መንገድ የሚከተሉ ቡድኖች ናቸው፡፡

እነዚህ ኃይሎች የሕዝብና የአገር ጠላት በመሆናቸው ሚዲያውም፣ ኅብረተሰቡም ሆነ እኛ በጋራ ተሠልፈን ነው መከላከል ያለብን፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ አሁን የማልገልጸው ቢሆንም፣ መረጃ እያሰባሰብን ነው፡፡ ዕርምጃም የምንወስድ ይሆናል፡፡ በሚዲያም፣ በዩቲዩብም የውሸት ወሬ በማሠራጨት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ላይ ተከታትለን ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የዋጋ ንረቱን ለማርገብ የተተገበረው የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማ ነው ለማለት ያስቸግራል›› አቶ አሰግድ ገብረመድህን፣ የፋይናንስ ባለሙያና አማካሪ

የዓለም ኢኮኖሚ በተለያዩ ተግዳሮቶች እየተፈተነ ነው፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት መጠኑ ይለያይ እንጂ፣ የእያንዳንዱን አገር በር አንኳኩቷል፡፡ መንግሥታት ይህንን ችግር ለማርገብ የተለያዩ የፖሊሲ ዕርምጃዎችን እየወሰዱ...

‹‹በአመራሮቻችን የተነሳ የፓርቲያችን ህልውና ጥያቄ ውስጥ ገብቷል›› አቶ አበባው ደሳለው፣ የአብን አባልና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በአማራ ከተመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአመዛኙ የተሻለ ሕዝባዊ ድጋፍ ያገኘ፣ ከሦስት ዓመታት በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ተወዳዳሪ...

‹‹የግሉን ዘርፍ በመዋቅር መለያየት የነበሩ ችግሮችን ከማባባስ ውጪ መፍትሔ አያመጣም›› አቶ ሺበሺ ቤተማርያም፣ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ

አቶ ሺበሺ ቤተማርያም በኢኮኖሚክስ፣ በኢኮኖሚ ፖሊሲና ዕቅድ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በማግኘት ለ36 ዓመታት የዘለቀ የሥራ ልምድ እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በዕቅድና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር፣ በዓለም አቀፍ...