የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት እንደ አዲስ መሰጠት ያለባቸውን መረጃዎች ያልሰጡ ባንኮች አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ መታገዱ ታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ባንኮች ደንበኞቻቸውን ማንነት እንዲያውቁ አዲስ ባወጣው መመርያ መሠረት ደንበኞቻቸውን መረጃ አሰባስበው መጨረስ አለባቸው የተባለው የካቲት 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በመጠናቀቁ እስከ እዚህ ቀነ ገደብ ድረስ መረጃዎቻቸውን ማሟላት ያልቻሉ የባንክ ደንበኞች ተለይተው አካውንቶቻቸው እንዳይንቀሳቀሱ አድርገዋል፡፡
አካውንታቸው እንዳይንቀሳቀስ የተደረጉ ደንበኞች ቁጥር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሲሆን፣ አንዳንዶች ቀነ ገደቡ ከተጠናቀቀ በኋላ ገንዘብ ለማንቀሳቀስ ወደ ባንኮች ቢሄዱም አካውንታቸውን ማንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
አንዳንድ የባንክ ደንበኞች የተጠቀሰውን መረጃ ለማሟላት በተለይ የቀበሌ መታወቂያና ሌሎች መረጃዎች እየተጠየቁ በመሆኑ የታደሰ መታወቂያ የሌላቸው አዲስ መታወቂያ ለማውጣት ወደሚኖሩበት ቀበሌ መሄድ ግድ እያላቸው ነው፡፡ የቀበሌ መታወቂያ ዕድሳት የተጀመረው በተጠናቀቀው ሳምንት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመታወቂያ ዕድሳት ጥያቄ ያቀረቡ ነዋሪዎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በፍጥነት ማስተናገድ እንዳልተቻለና ይህም የባንክ ደንበኞች መረጃዎቻቸውን አሟልተው አካውንታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ ምክንያት እንደሆነ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡
ከአንዳንድ ባንኮች ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በተጠቀሰው ጊዜ መረጃ ያልሰጡ ከየካቲት 2014 ዓ.ም. በኋላ አካውንታቸው የታገደባቸው ደንበኞች ተገቢውን መረጃ ለባንኮች ከሰጡ ወዲያው አካውንታቸው እንዲከፈትላቸው እየተደረገ ነው፡፡
ነገር ግን የሚፈለገውን መረጃ ማሟላት ካልቻሉ የባንክ አካውንታቸው ሳይንቀሳቀስ የሚቆይ ይሆናል፡፡
ደንበኞች መረጃዎቻቸውን እንዲሰጡ ከስድስት ወራቶች በላይ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች የተጠየቁ ቢሆንም ጥቂት የማይባሉት መረጃውን ሳያሟሉ በመቅረታቸው ባንኮች የእነዚህን ደንበኞች አካውንት እንቅስቃሴ በማገድ በተለየ ቋጥ እንዲቀመጥ ማድረጋቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የባንክ ደንበኞች በተሰጠው የጊዜ ገደብ አለመጠቀማቸው ለመጉላላት ያደረጋቸው ሲሆን፣ የተጠየቀውን መረጃ ካሟሉ ግን አካውንታቸው ወዲያውኑ የሚንቀሳቀስላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
አብዛኞቹ የባንክ ደንበኞች የሚጠበቅባቸውን መረጃ አሟልተው የሰጡ ቢሆንም በአንዳንድ አካውንቶች ላይ ግን ተጨማሪ የማጣራት ሥራ ሊኖር እንደሚችል ለማወቅ ተችሏል፡፡