Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ለመሆን የፋይናንስ ተቋማትን ከወዲሁ ማጠናከር ይገባል!

ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ትሆናለች ተብሎ መነገር ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ መንግሥትም ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል ለመሆን የሚያስችላትን ሁኔታዎች እያመቻች ነው፡፡

በተመሳሳይ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነትን ኢትዮጵያ ፈርማለች፡፡ ይህ አፍሪካውያንን ድንበር ሳይገድባቸው ይገበያዩበታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው፡፡ ስምምነቱም በቅርቡ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ሌሎች እንዲህ ያሉ ስምምነቶችም እንደሚኖሩ ይታመናል፡፡ በመሆኑም ከፊት ለፊታችን ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች እንደሚጠብቁን ያሳያል፡፡ አገራዊ ኩባንያዎችም ከተለመደው አሠራር ወጣ ብለው አጠቃላይ የንግድና የኢንቨስትመንት ጉዟቸው ዓለም አቀፋዊ ቅኝት እንዲኖረው ያስገድዳል፡፡

ኢትዮጵያ ለውጭ ኩባንያዎች ዘግታ የቆየችውን የፋይናንስ ዘርፍ ለመክፈት እየተዘጋጀች ነው መባሉም በሁሉም ረገድ ተወዳዳሪነታችን በድንበር የተከለለ እንደማይሆን ያመላክታል፡፡

መንግሥት የፖሊሲ ውሳኔውን ሲያሳልፍ ከውጭ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ሳይወዳደር የቆየው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ውድድሩ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ድንበር ዘለል ይሆናል፡፡

የውጭ የፋይናንስ ተቋማት መግባት አይቀሬ በመሆኑም መንግሥት የውጭ ኩባንያዎቹ የሚገቡበትን መንገድ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች በማይጎዱበት እንዲሆን ሁኔታዎችን ያመቻቻል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ውጪ አንድና ሁለት ዓመትም ተጨማሪ ጊዜ ሊሰጥ የሚችበት ዕድል ሊኖር ካልቻለ የአገር ውስጥ ፋይናንስ ተቋማት ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ዝግጅት ገና ነውና፡፡

 የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት አሁን እየሠሩበት ያለው በውድድሩ አሸናፊ አያደርጋቸውም የሚል አመለካከት ቢኖርም፣ እኩሉ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ዕድል ግን አለ፡፡

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በውጭ የፋይናንስ ኩባንያዎች ሊፈተኑ ይችሉባቸዋል ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል የካፒታል አቅማቸው አነስተኛ መሆኑ ነው፡፡ አመሠራረታቸውና የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናቸው ለተወዳዳሪነት ሊያበቃቸው አይችልም የሚል እምነት ያላቸውም አሉ፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን የብዙዎቹ ፋይናንስ ተቋማት በተለይ የባንኮች አመሠራረትና አደረጃጀት ሲታይ ‹‹ብሔርን መሠረት ያደረገ ነው›› የሚለው ደግሞ ሌላው የሥጋት ምንጭ ነው፡፡

ስለዚህ እነዚህ ተቋማት ውድድር ስለሚጠብቃቸው ብቻ ሳይሆን፣ ቀድሞም በአመዛኙ አካባቢን መሠረት ያደረገ አመሠራረታቸው ተገቢ ነው ተብሎ አይታሰብም፡፡ እንዲህ ያለውን አደረጃጀታቸውን ከወዲሁ ሊያስተካክሉ የሚችሉበትን መንገድ መፈለግ አለባቸው፡፡

ገንዘብ ዘርና ብሔር የሌለው ቢሆንም፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት እንዲህ ያለው አወቃቀራቸው የት ድረስ ሊያደርሳቸው እንደሚችል በማሰብ ይህንን አካሄዳቸውን ለማረም አሁን ጥሩ አጋጣሚ የመጣላቸው በመሆኑ ይህንን ዕድል ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡

የውጭ ኩባንያዎች በምን ሁኔታ ይግቡ የሚለውን ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጠንከር ያሉ አገራዊ የፋይናንስ ተቋማት እንዲኖሩን የግድ ነውና ይህንን ወሳኝ ጉዳይ ለመተግበር ሰብሰብ ማለት እጅግ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

ስለዚህ የውጭ ኩባንያዎች እስኪገቡ ድረስ እነዚህ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ተቋማት እርስ በርስ በመዋሀድ ካፒታላቸውን አጠንክረውና የሰው ኃይላቸውን አሰባስበው የተሻለ ተወዳዳሪ የሚሆን ኢትዮጵያዊ የፋይናንስ ተቋም ለመፍጠር ከቻሉ የአገር ባለውለታ ይሆናሉ፡፡ ባለአክሲዮኖቻቸውንም ይጠቅማሉ፡፡

ለአንድ ኩባንያ ግማሽ ቢሊዮን ብር በአንዴ ለማበደር አቅም የሌላቸውን ባንኮች ይዞ፣ በሀብት የደረጁ የውጭ ኩባንያዎችን ለመወዳደር መሞከር ሊከብድ የሚችል በመሆኑ፣ ውድድሩን በአሸናፊነት ለመወጣት በመዋሀድ ጠንከር ብሎ መጠበቅ ያዋጣል፡፡

ይህንን ዘርፍ የበለጠ ለማደራጀትና ጠንካራ አገራዊ ባንክ እንዲኖረን ከተፈለገ፣ ሳይታሰብ ከመክሰማቸው በፊት ሰብሰብ ብለው ጠንካራ ባንክ እንዲፈጥሩ መትጋት የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡ በተለይ ከመንግሥትና ከባለ አክሲዮኖች ብዙ ይጠበቃል፡፡

ጠንካራ ባንክ ለመፍጠር አቅም የሚጠይቅ በመሆኑ የተወሰነ ጊዜ ትርፍን ከመከፋፈል ባንኮቻችሁን በማጠናከር ላይ ማዋል ግድ የሚል በመሆኑ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ መዋሀዱ ለእኛም፣ ለአገርም ይጠቅማል የሚለውን አመለካከት ማዳበርም ያስፈልጋቸዋል፡፡

የዓለምን ገበያ የምንቀላቀልበት ዕድልና ማዕበል ከፊት ለፊታችን እየመጣ ስለሆነ፣ ይህንን ለመወጣት ምን ማድረግ አለብን ብሎ በየዘርፉ መምከርና ለተወዳዳሪነት መዘጋጀት የግድ ነው፡፡

የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ስንሆንና የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ሲጀመር ከመሯሯጥ ይልቅ ከወዲሁ ራስን ማጠንከር ለነገ የሚባል ጉዳይ አይደለም፡፡ ተወዳዳሪ የሚሆነው ደግሞ መንግሥት አይደለም፣ የግል ዘርፉ ነውና፡፡ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚጠብቃቸው በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ያሉ የንግዱ ማኅበረሰብ፣ ለእነዚህ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ከወዲሁ እንዲነቃቁ መደረግ አለበት፡፡ እስካሁን በእነዚህ ጉዳዮች የግሉ ዘርፍ ላይ ይህ ነው የሚባል ሥራ እየተሠራ ያለመሆኑ ያሳስባል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ይጠብቃቸዋል የሚባለው ውድድርም በተመሳሳይ የሚታይ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት በውጭ ኩባንያዎች እንዳይዋጡ አማራጩ ምንድነው? የተሻለውስ ነገር የቱ ነው? በማለት ማሰብ፣ ለዚህም መምከርና የተሻለውን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡

ከየትኛውም አማራጭ ግን የፋይናንስ ተቋሞቻችን አሁን ከተሸበቡበት አመለካከት ወጥተው ባለአክሲዮኖቻቸውን ይዘው በመዋሀድ ጠንካራ አገራዊ ባንክ ፈጥረው ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን መዘጋጀትን ቅድሚያ ቢሰጡት መልካም ነው፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት