Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአገር ውስጥ ምርቶች እንዲሸፈን የሚፈለገው የመድኃኒት አቅርቦት

በአገር ውስጥ ምርቶች እንዲሸፈን የሚፈለገው የመድኃኒት አቅርቦት

ቀን:

ከ100 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት ኢትዮጵያ የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የተለያዩ ፖሊሲዎች ተቀርፀውና መመርያዎች ተዘጋጅተው እየተተገበሩ ቢሆንም፣ የጤናው ዘርፍ አሁንም ተግዳሮት አለበት፡፡

የጤናው ዘርፍ ስፔሻላይዝድ ባደረጉ የጤና ባለሙያዎች እጥረት ብቻ ሳይሆን በጤና ተቋማትና በግብዓት ማነስ፣ በመድኃኒትና የሕክምና መሣሪያዎች እጥረት የሚፈተንም ነው፡፡

ባለፉት ዓመታት የጤናውን ዘርፍ ለማሻሻል የተሠሩ ሥራዎች፣ የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ ቢያስችሉም፣ ከዚህ ቀደም ተደራሽ ያልነበሩ ሥፍራዎችን እየደረሱ ቢሆንም፣ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የተመጣጠነ አገልግሎትና አቅርቦት እየተሰጠ አይደለም፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የሕክምና ባለሙያዎች ምጣኔም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ አንድ የጤና ባለሙያ በቀን ከ30 በላይ ሕሙማንን በሚያይበት ኢትዮጵያ፣ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ አቅርቦትም ከሚታዩ ችግሮች በቀዳሚነት ይመደባል፡፡

ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የጤና ሽፋን ለማሳካት የጤና ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ከአንድ እስከ አራት፣ የጤና ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራምና የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዘርግታ እየሠራች ትገኛለች፡፡

በኢትዮጵያ ከፍተኛ በጀት ከሚመደብላቸው ዘርፎች አንዱም የጤናው ዘርፍ ነው፡፡ የጤናው ዘርፍ ከሚመደብለት በጀት ውስጥ ከፍተኛ የሚባለው የሚውለውም ለመድኃኒት ግዥ ነው፡፡

በህንድና ባንግላዴሽ ተሳትፎ ለሦስት ቀናት የተዘጋጀው የጤና ዓውደ ርዕይ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲከፈት እንደተገለጸው፣ በጤና ዘርፍ የመንግሥት ወጪ በ2012 ዓ.ም. ከነበረው 12 በመቶ፣ በ2013 ዓ.ም. ወደ 13.2 በመቶ አድጓል፡፡ የመድኃኒት ግዥ ደግሞ በ2009 ዓ.ም. ከነበረበት 4.8 ቢሊዮን ብር፣ በ2013 ዓ.ም. ወደ 17.2 ቢሊዮን ብር ተሻግሯል፡፡

መንግሥት ለመድኃኒት ግዥ ከፍተኛ ወጪ በሚያወጣባት ኢትዮጵያ ግን በመድኃኒት ማምረት ዘርፉ የተሰማሩ ድርቶች 13 ብቻ እንደሆኑ የኢትዮጵያ የመድኃኒትና የሕክምና መገልገያ አምራቾች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ዋቅቶላ ይገልጻሉ፡፡

ይህ በኢትዮጵያ ከሚያስፈልጋት የመድኃኒት አቅርቦት አሥር በመቶውን ብቻ የሚሸፍን ሲሆን፣ 90 በመቶ ከውጭ አገር የሚገባ ነው፡፡

በኢትዮጵያ አሁን ላይ እየተመረቱ ያሉ የመድኃኒት ዓይነቶችም በኢትዮጵያ ደረጃ መሠረታዊ የሚባሉት እንጂ የካንሰርና የሌሎች ከባባድ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን አይጨምርም፡፡ ይህም የኢትዮጵያን የውጭ ምንዛሪ እየተፈታተነ ብቻ ሳይሆን የተገልጋይንም ሥቃይ አብዝቶታል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች መድኃኒቶችን በቀላሉ ማግኘት፣ ሲገኙም በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት ፈታኝ እየሆነ መጥቷል፡፡ በተለይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በበርካታ ፋርማሲዎች ውስጥ መድኃኒቶችን በተፈለገው ጊዜና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት አዳግቷል፡፡

ይህንንና መንግሥት ለመድኃኒት ግዥ የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ ለመቀነስ የውጭ መድኃኒት አምራቾች በኢትዮጵያ ገብተው እንዲሠሩ የቂሊንጦው የኢንዱስትሪ ፓርክ መመቻቸቱን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ የውጭ ባለሀብቶች በፓርኩ በመግባት፣ ከአገር ውስጥ አምራቾች ጋር በመጣመር ወይም ለብቻቸው ሌላ ቦታ ላይ መድኃኒት በማምረት ዘርፍ እንዲሰማሩ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣይ ዓመታት የመድኃኒት አምራቾችና ላኪዎች ማዕከል እንድትሆን እየተሠራ ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፣ በመድኃኒት ዘርፉ የተዘጋጁ ፖሊሲዎችን ወደ መሬት ለማውረድና የዘርፉን ክፍተት ለመሙላት በመንግሥት በኩል ፍላጎቱ እንዳለ ተናግረዋል፡፡  

በሕክምና መገልገያዎችና በመድኃኒት ዘርፍ በተካሄደው ዓውደ ርዕይ በባንግላዴሽ፣ በህንድ፣ በዮርዳኖስ፣ በሱዳን፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በታይላንድ፣ በቱርክ፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና በአሜሪካ ዋና መቀመጫቸውን ያደረጉ የመድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ አምራቾች እንዲሳተፉ ጥሪ የተደረገ ሲሆን፣ ከእነዚህ ከየአገራቸው ከ30 በላይ ኩባንያዎቻቸውን ይዘው የመጡት ባንግላዴሽና ህንድ ናቸው፡፡

ከህንድ የመጡ የተለያዩ የዘርፉ ተዋናዮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በርካቶቹ ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን፣ ፍላጎታቸውም ከአገር ውስጥ አጋር አግኝተው አብረው ለመሥራት ነው፡፡

ለዚህም የተመቻቸ ሁኔታ መኖሩን የገለጹት የጤና ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሩት ንጋቱ (ዶ/ር)፣ ሚኒስቴራቸው በዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶችን እንደሚደግፍ በመክፈቻ ንግግራቸው አስታውቀዋል፡፡

በጤና ትራንስፎርሜሽን ፕላኑ ውስጥ የግሉን ዘርፍና የመድኃኒት አቅርቦትን ማጠናከር አንዱ ቅድሚያ የተሰጠው ተግባር መሆኑን ያወሱት ሩት (ዶ/ር)፣ ጤና ሚኒስቴር መድኃኒቶችንና የሕክምና መሣሪያዎችን በኢትዮጵያ የሚያመርቱ ባለሀብቶችን ያበረታታል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ዘጠኝ የሕክምና ሙያ ማኅበራት በተሳተፉበት ስድስተኛው የጤና ጉባዔና ዓውደ ርዕይ ላይ ለመሳተፍ ከ40 ያላነሱ መድኃኒት አምራቾችን ይዞ ከተሳተፈው ባንግላዴሽ፣ በካንሰር ሕክምና መድኃኒት አቅርቦት የተሰማራው ቢኮን ሜዲካል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አንዱ ነው፡፡

የኩባንያው የኬንያ ቅርንጫፍ ዳይሬክተር ሚስተር መሐመድ ነቢል እንዳሉት፣ ፋብሪካውን ባንግላዴሽ ያደረገው የቢኮን ኩባንያ ለካንሰር ሕክምና የሚያገለግሉ 120 ዓይነት መድኃኒቶችን ያመርታል፡፡

በባንግላዴሽ የካንሰር መድኃኒቶችን በማምረት ወደ 25 አገሮች እንደሚልክና በዓለም የባለቤትነት ጊዜያቸውን የጨረሱ (ጀነሪክ) የካንሰር መድኃኒቶችን በማምረት ከቀዳሚዎቹ አገሮች ተርታ እንደሆነም አክለዋል፡፡

በአፍሪካ በኬንያ፣ በታንዛኒያ፣ በዑጋንዳና በሩዋንዳ የካንሰር ሕክምና መድኃኒቶችን እንደሚያቀርቡና በኢትዮጵያም በዘርፉ ለመግባት እንደሚፈልጉ ሚስተር ነቢል ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ትልቅ ገበያ እንዳለና ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እንደሚፈልጉ የጠቀሱት መሐመድ ነቢል፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ አዲስ በካንሰር በሚያዙ ሕሙማን ቁጥር በሁለተኛ ደረጃ ስለምትገኝ ችግሩን ከኢትዮጵያ መንግሥትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር ተባብረን ልንቀርፈው እንችላለን ብለዋል፡፡

የካንሰር ሕክምና ለመንግሥት ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ነገር ግን በሽታውን መቆጣጠር እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በኢትዮጵያ መድኃኒቶችን ለማምረት ዕቅድ እንደሌላቸው፣ ነገር ግን የኩባንያው መድኃኒቶች ከተለመዱ በኋላ ፋብሪካውን እዚህም ለመትከል እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ለካንሰር ሕሙማንን ጥራታቸውን የጠበቁና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸውን መድኃኒቶች በማቅረብ መርዳት እንፈልጋለን፤›› ያሉት ነቢል፣ ኢትዮጵያ የሕክምና መድኃኒት አምራቾች ኢንቨስት እንዲያደርጉ መደገፍና መሳብ አለባት ብለዋል፡፡

ጉባዔው በአምስት ርዕሰ ጉዳዮች ማለትም የሕክምና አገልግሎት ልህቀት፣ የታካሚ ደኅንነት የጨረርና ላቦራቶሪ ምርመራዎች፣ የመጀመርያ ደረጃ የጤና እንክብካቤና መድኃኒት ላይ ልምድ ልውውጥ የሚደረግበትና ለሕግ አውጪዎች ግብዓት የሚገኝበት እንደሆነ ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...