ኢትዮጵያዊነት የአገራዊ ምክክሩ ቀዳሚ አጀንዳ እንዲሆን ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት ጠየቀ።
ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት ከመስከረም 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በዜጎች መብቶችና በሕዝባዊ አንድነት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ የሲቪክ ማኅበር ሲሆን፣ ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚያካሂደውን የመተዋወቂያ ፕሮግራም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ላይ የተገኙት የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሞገስ በቀለ በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚለው አጀንዳ በአገራዊ ምክክሩ ውስጥ በቀዳሚነት ሊነሳ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ይህንንም የሚጠይቅ ደብዳቤ በመጪው ሳምንት ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እንደሚያስገቡ ተናግረዋል።
አገራዊ ምክክሩ በተለይ በኢትዮጵያዊነት ላይ ተመሳሳይ አመለካከት ከተያዘና ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ፣ ወደ ሌሎች ጉዳዮች መሄድ አለበት ብለዋል። ኢትዮጵያዊነት የሚለውን ሐሳብ የማይቀበል አካል ባለበት ሁኔታ፣ ሌሎች ጉዳዮች ላይ ምክክር ቢደረግ ውጤት አያመጣም ሲሉም አስረድተዋል።
ሕገ መንግሥትን በተመለከተ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ለተፈጠረው ግጭትና አለመግባባት ምክንያት የሆኑ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ተለይተው ግልጽ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል ብለዋል። መሻሻል ያለባቸው አንቀጾችም በቀጣይ የችግር ምንጭ እንዳይሆኑ በማድረግ ማሻሻል ያስፈልጋል ብለዋል።
ምክክሩ የሁሉም ኅብረተሰብ እንዲሆንና በተለይ በምሁራንና በፓርቲዎች ላይ ብቻ የተንጠለጠለ መሆን እንደሌለበት አሳስበው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ሁሉም አካላት ሊወከሉ ይገባል ብለዋል፡፡
‹‹ለምክክር ኮሚሽኑ ከተጠቆሙት የመጀመሪያ 632 ሰዎች ውስጥ ከ200 በላይ የሚሆኑት በእኛ ድርጅት አማካይነት የተጠቆሙ ናቸው፤›› ያሉት አቶ ሞገስ፣ ከጥቆማው ባለፈ ሁሉም ኅብረተሰብ በምክክሩ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን ማስተማር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንድነት ማጠናከርና የዜግነት ሥነ ልቦናን ማዳበር ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት በ1984 ዓ.ም. እነ ዶ/ር ሀዲስ ዓለማየሁ፣ ሌተና ጄኔራል ጃጋማ ኬሎና ሌሎችም በጋራ መሥርተውት የነበረውን ‹‹የኢትዮጵያዊነት ማኅበር›› ሐሳቦች መነሻ በማድረግ በ2013 ዓ.ም. የተመሠረተ ድርጅት እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።