በግብርና ዘርፍ የሚታየውን የተበታተነ አሠራር የሚያስተባብርና የሚከታተል ፎረም መመሥረቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ላይ በርካታ የውጭና አገር በቀል ተቋማት የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፎችን የሚያደርጉ ቢሆንም፣ በተገቢው መንገድ ክትትል ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኤክስቴንሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ ገርማሜ ጋሩማ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ሁሉም ድጋፎች ዕውቅና አግኝተው በአንድ ማዕከል በኩል እንዲያልፉና ክትትል እንዲደረግባቸው ለማስቻል ፎረሙ መመሥረቱን ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ቦታዎች በወረዳ ደረጃም ሆነ እስከ ክልል የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ከፎረሙ ዕውቅና አግኝተው መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በፎረሙ ውስጥ 26 አባላት የተካተቱ መሆናቸውንና ቁጥራቸውን እስከ 100 ለማድረስ ፍላጎት መኖሩን የገለጹት አቶ ገርማሜ፣ ይህም በዘርፉ የሚሳተፉና የሚመለከታቸውን አካላት የሚያካትት ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል።
በግብርና ሚኒስቴር በሚመራው ፎረም ውስጥ በአባልነት ከተካተቱት መካከል የግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩትና የጀርመን የተራድኦ ድርጅት (GIZ) ተጠቃሶሾች ናቸው።
ሁሉም አባላት የሚሳተፉበት የስትራቴጂ ዝግጅት በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ገርማሜ፣ በተለይ በግብርና ዘርፍ ውስጥ የሚገኘውን ሀብት አጠቃቀም በተመለከተ የተሻለ መንገድ ይቀየስበታል ብለዋል።
ፎረሙ በ2015 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገባና የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋትና አዳዲስ አሠራሮችን በማስተዋወቅ፣ የተቀናጀ አሠራር እንዲፈጠር አጋዥ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ለአርሶና በአርብቶ አደሮች የሚደርስ መረጃን በሚመለከት እስካሁን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት የመረጃ አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸው፣ ይህንን በተሻለ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ በአንድ ማዕከል የሚመራ ፎረም መቋቋሙ ጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።