Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበአዲስ አበባ አምስት መንገዶች ላይ አዲስ የትራንስፖርት ሥርዓት ሊዘረጋ ነው

በአዲስ አበባ አምስት መንገዶች ላይ አዲስ የትራንስፖርት ሥርዓት ሊዘረጋ ነው

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ መጨናነቅ በሚታይባቸው አምስት ኮሪደሮች ላይ፣ የትራፊክ ፍሰቱን የሚቆጣጠር ኢንተለጀንት ትራንስፖርት ሲስተም (ITS) ለመዘርጋት የዲዛይን ጥናት እየተከናወነ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ጀርመን ሬል ኢንጂነሪንግ በተባለ ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት እየተሠራ ካለው የአምስት ኮሪደሮች የዲዛይን ጥናት ውስጥ፣ የመጀመርያው ኮሪደር ጥናት በመጠናቀቁ በግንባታ ጨረታ ሒደት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ብድር እየተከናወነ ያለው የኢንተለጀንት ትራንስፖርት ሥርዓት ዲዛይን ጥናት ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አፍሪካ ጎዳና፣ ከአራት ኪሎ በደጎል አደባባይ አቡነ ጴጥሮስ፣ ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ወደ ድል በር፣ ከአራት ኪሎ ወደ ቦሌ ብራስና ከኡመር ሰመተር ትምህርት ቤት ወደ ታላቁ ቤተ መንግሥት የሚወስዱ መንገዶችን የሚመለከት ነው፡፡

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የመንገድ ዲዛይን ዳይሬክተር ሜቲ ውድነህ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የዲዛይን ጥናቱ እየተደረገ ያለው በእነዚህ ዋነኛ መተላለፊያ መንገዶች ላይ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በዘመናዊ መንገድ ለመፍታትና ፍሰቱን ለማስተካከል ነው፡፡ እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ መንገዶቹ  ግንባታቸው ሲጠናቀቅ በሚገጠምላቸው ሲሲ ካሜራና ሴንሰር ባላቸው የትራፊክ መብራቶች የሚሰበሰበው መረጃ፣ መገናኛ አካባቢ እየተገነባ ወዳለው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል ይሄዳል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በ835 ሚሊዮን ብር በጀት በ2012 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው የትራፊክ መቆጣጠሪያ ማዕከል መንገዶቹ ላይ ከሚገጠሙ ካሜራዎች የሚገኙ መረጃዎችን በመሰብሰብ ተንትኖ ለትራፊክ ፖሊሶች፣ ለሾፌሮችና ለሌሎች የመረጃው ተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡ ማዕከሉ አሽከርካሪዎች የመንገዶችን የትራፊክ ሁኔታ ቀድመው እንዲያውቁና አማራጭ መንገዶችን እንዲፈልጉ መረጃ የመስጠትና የትራፊክ ሕጎችን የሚተላለፉ አሽከርካሪዎችን የመለየት ሥራ ያከናውናል፡፡ እንዲሁም የትራፊክ ፍሰት፣ የአደጋና የደኅንነት መረጃዎችን ወደሚመለከታቸው ተቋማት ያስተላልፋል፡፡

በቻይና ኮሙዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ኩባንያ (CCCC) እየተገነባ ያለው ማዕከል ሲጠናቀቅ፣ ውስጡ በሚገጠሙ ግዙፍ የቴሌቪዥን ስክሪኖች አማካይነት የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ በማየት የቁጥጥር ሥራ ያከናውናል፡፡

በአሁኑ ወቅት የዲዛይን ጥናት እየተደረገላቸው ያሉት መንገዶችም ከተገነቡ በኋላ የትራፊክ ፍሰታቸው ቁጥጥር የሚደረግበትና የሚመራው፣ በትራፊክ ፖሊሶች ሳይሆን በማዕከሉ ነው፡፡ በመንገዶቹ ላይ የሚገጠመው ካሜራ የተፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ ቀርፆ ወደ ማዕከሉ ሲልክ ሴንሰር የተገጠመላቸው መብራቶች እንደ ትራፊክ ፍሰቱ በመለዋወጥ፣ ተሸከርካሪና እግረኞችን እንደሚያስተናግዱ ሜቲ (ኢንጂነር) አስረድተዋል፡፡

ዳይሬክተሯ እንደተናገሩት ከአምስቱ ኮሪደሮች ውስጥ ከእንግሊዝ ኤምባሲ ወደ አፍሪካ ጎዳና የሚወስደው 4.5 ኪሎ ሜትር መንገድ የዲዛይን ጥናቱ ተጠናቆለት ግንባታ ለመጀመር የጨረታ ሒደት ላይ ነው፡፡ ከእንግሊዝ ኤምባሲ በጎላጉልና በደንበል አድርጎ ወደ ቦሌ መንገድ የሚወጣው ይህ የመንገድ ግንባታ ወጪው በዓለም ባንክ ብድር የሚሸፈን ነው፡፡

በ2011 ዓ.ም. የተጀመረውና 7.7 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀው ዲዛይን ጥናት ከሰባት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀሪዎቹ አራት ኮሪደሮች ግንባታቸው ከየት በሚገኝ ፈንድ እንደሚከናወንና ለየትኛው ቅድሚያ ኮሪደር ግንባታ ቅድሚያ እንደሚሰጥ አለመወሰኑን ሜቲ (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡

የአምስቱ መንገዶች ግንባታ የሚከናወነው ከዚህ ቀደም ሲደረግ እንደነበረው የተሽከርካሪ መተላለፊያነትን ብቻ ታሳቢ በማድረግ አይደለም፡፡ ይልቁንም እንደ ቸርችል ጎዳና ማስፋፊያ ሁሉ የመንገዶቹ ግንባታ እግረኞችን ማዕከል ያደረገና ሰፊ የእግረኞች መንገድ፣ የብስክሌት መስመር፣ የአትክልት ቦታ፣ እንዲሁም ማረፊያ መቀመጫዎችን እንደሚያካትት ሜቲ (ኢንጂነር) አብራርተዋል፡፡

የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሥርዓትን ለማዘመን የሚረዳና ለሰባት ዓመታት የሚቆይ ፕሮጀክት ያስጀመረው በ2008 ዓ.ም. ነበር፡፡ ባንኩ ሊጠናቀቅ ከሁለት ዓመት ያነሰ ጊዜ ለቀረው ፕሮጀክት 300 ሚሊዮን ብር ብድር ማቅረቡ ታውቋል፡፡ የብድሩ ተጠቃሚ ከሆኑ ተቋማት ውስጥ አንዱ የሆነው አንበሳ አውቶቡስ ድርጅትም፣ በፕሮጀክቱ አማካይነት 644 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ የኢንተለጀንት ትራንስፖርት ሲስተም እየዘረጋ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...