Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ግብታዊ ዕርምጃ የኑሮ ውድነቱን አያረግብም!

በአሁኑ ጊዜ በምግብና ምግብ ነክ በሆኑ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚስተዋለው ከመጠን ያለፈ የዋጋ ጭማሪ፣ የሸማቾችን የመግዛት አቅም በማዳከም የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ነው፡፡ በምግብ ምርቶችና በሸቀጦች ላይ በየቀኑ የሚታየው መረን የለቀቀ የዋጋ ጭማሪ ከሸማቾች አቅም በላይ ሲሆን፣ መንግሥት በፍጥነት የማረጋጊያ ዕርምጃዎችን መውሰድ ካልቻለ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የሸማቾች ገቢ ሳይጨምር ሁሉም ዓይነት ምርቶች ዋጋቸው በየቀኑ ሲጨምር፣ ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይፈጠር የማረጋጊያ ዕርምጃዎችን የመውሰድ ኃላፊነት የመንግሥት ነው፡፡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችም ሆኑ ሌሎች ምርቶች በሚፈለገው መጠን መመረታቸውን ወይም መቅረባቸውን ብቻ ሳይሆን፣ በተገቢው መንገድ ለሸማቾች መሠራጨታቸውን ማረጋገጥ የመንግሥት ሥራ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱን ጤናማነት የሚያውኩ፣ የአቅርቦትና የፍላጎት መመጣጠንን የሚያሰናክሉና በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው ፈተና የሆኑ ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡ ብልሹ አሠራሮች የሚስተዋሉት በመንግሥት መዋቅር፣ በንግዱ ማኅበረሰብና በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሱ ተዋንያን ውስጥ ነው፡፡ ሁሉንም ችግሮች ነጋዴው ላይ መደፍደፍ አይገባም፡፡ ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ዕርምጃ በጥናት ላይ የተመሠረተ ይሁን፡፡

የምግብ ዘይት ከመጠን በላይ ዋጋው ማሻቀቡ ሰሞነኛው ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ እንዲያው ቀለል ተደርጎ መነጋገሪያ ቢባልም መንግሥት ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ ካደረገው በተጨማሪ፣ ግዙፍ የምግብ ዘይት ማምረቻዎች አሉ በሚባልባት ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ ጆሮ የሚያደነቁር ጩኸት ቢፈጥር አይገርምም፡፡ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትና ከቀረጥ ነፃ ዕድል አግኝተው ሥራ የጀመሩ ፋብሪካዎች ይህንን ችግር ካልቀረፉ፣ ከዚህ ቀደም በዘይት ማስመጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ መወገዳቸው ያሳዝናል፡፡ በብልሹ አሠራር ሸማቹ ሕዝብ መቀጣቱ ያስቆጫል፡፡ ሸማቹ ሕዝብ፣ ነጋዴውና መንግሥት መስተጋብር ከሚፈጥሩበት የግብይት ሥርዓት አንስቶ፣ አጠቃላይ የኢኮኖሚው ፈተና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ያስፈልገዋል፡፡ ሸማቹን ሕዝብ ሊታደጉ የሚችሉ ማኅበራትን ከመደገፍ ጀምሮ፣ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑበት ተቋማዊ ጥንካሬ ለምን አይኖራቸውም? ሕዝቡ በተደጋጋሚ የዋጋ ግሽበት እየተመታ ኑሮ ሲኦል ሲሆንበት ምን እስኪሆን ድረስ ነው የሚጠበቀው? ፓርላማው መረን የተለቀቀውን የግብይት ሥርዓት መቼ ነው ፈር የሚያስይዘው? ማንም እንደፈለገ የሚጨፍርበት የግብይት ሥርዓት አደብ እንዲገዛ ካልተደረገ፣ ከፍተኛ ማኅበራዊ ቀውስ ሊቀሰቀስ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ የኑሮ ውድነቱን እያባባሰ ያለው የግብይት ሥርዓት መዘዙ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡

በበርካታ አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ከሚደረጉ መለስተኛ ውይይቶችና ክርክሮች መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ችግሮች በመሠረታዊነት ከሚነሱ የመፍትሔ ሐሳቦች መካከል አንዱ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ በመንግሥት መዋቅር፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በትምህርት ተቋማት፣ በንግዱ ማኅበረሰብ፣ በአርሶ አደሩና በአርብቶ አደሩ፣ እንዲሁም በአጠቃላይ በሕዝቡ ውስጥ መኖር አለበት፡፡ የአስተሳሰብ ለውጥ ሳይኖር ማቀድም ሆነ ማሳካት አይቻልም፡፡ ለዚህም ሲባል የዜጎች በልቶ ማደርን የሚወስኑ ተቋማዊ አሠራሮች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው፡፡ የመጀመሪያው ለምግብነት የሚውሉ ምርቶች በብዛትና በጥራት እንዲመረቱ የሚያስችል ፖሊሲ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ፖሊሲ በባለሙያዎች በሚገባ ተመክሮበት የሚወጣ መሆን ሲኖርበት፣ የሰው ኃይልንና የተፈጥሮ ሀብቶችን ያማከለ መሆን አለበት፡፡ በዚህም መሠረት በግብርናውም ሆነ በተያያዥ ዘርፎች ብቁ የሆኑ አመራሮችና ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የምርቶችን አቅርቦትና ሥርጭት የሚያቀላጥፉ ዘመናዊ አሠራሮች መዘርጋት ተፈላጊ ነው፡፡ ከማሳ እስከ በላተኛው ድረስ ያለው ሰንሰለት በደላሎች እንዳይጠለፍ ከፍተኛ ቁጥጥር መደረግ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት፣ ሸማቹና ነጋዴውን የሚያገናኛቸው የግብይት ሥርዓት ጤናማና በውድድር ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡ በግብታዊ ዕርምጃ የትም አይደረስም፡፡

መንግሥት ከዚህ ቀደም የምግብ ዘይት በአገር ውስጥ እንዲመረት ለማስቻል በሚል ምክንያት፣ ብዙዎቹን አስመጪዎች ከንግድ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲወጡ ማድረጉ የችግሩ መነሻ ነው፡፡ በአገር ውስጥ የምግብ ዘይት የሚያመርቱ ኢንቨስተሮች በውጭ ምንዛሪ ድፍድፍ እንዲያስመጡ ሲወሰን፣ እነሱን ሊያስተናግድ የሚችል የውጭ ምንዛሪ አቅም መኖሩ አለመረጋገጡ ብቻ ሳይሆን ምክንያቱ አሳማኝ አልነበረም፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ዘይትን ጨምሮ የተለያዩ የፍጆታ ምርቶችን ለሚያስገቡ አስመጪዎች ከቀረጥ ነፃ ዕድል በመፍቀድ፣ መንግሥት ማግኘት የነበረበትን በርካታ ቢሊዮን ብሮች ከማጣቱም በላይ ምርቶቹ በአግባቡ ለሸማቾች መድረሳቸውም አጠራጣሪ ነው፡፡ መንግሥት ውሳኔውም ሆነ ቁጥጥሩ የዘፈቀደ በመሆኑ ችግሮች ተባብሰዋል፡፡ አሁን ያለውን ችግር በዘለቄታዊነት ከመቅረፍ ጎን ለጎን የአጭር፣ የመካከለኛና የረዥም ጊዜ ዕቅድ ያስፈልጋል፡፡ የምግብ ዘይትን ጨምሮ የሌሎች ሸቀጦችን የዋጋ ግሽበት ለማርገብ፣ መንግሥት በተወሰነ ደረጃ ድጎማ በማድረግ ሸማቾችን ማገዝ ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም የአቅርቦት ሰንሰለቱን ሙያዊ በሆነ መንገድ በማጥናት ችግሮቹን ነቅሶ መፍትሔ መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ እሳት የማጥፋት ዓይነት ግብታዊ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ከነጋዴዎች ጋር ከመተናነቅ በፊት፣ ሰው ሠራሽ ችግሮች ለመኖራቸው የሚያሳዩ ችግሮችን ፈትሾ ማረም ግዴታው ነው፡፡

በሌላ በኩል ሰሞኑን በሩሲያና በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ይዞት የሚመጣው ጦስ አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ ምዕራባውያን በተለያዩ ዘርፎች ሩሲያ ላይ እየጣሉዋቸው ያሉ ማዕቀቦች፣ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአቅርቦት ሰንሰለቶችን በመበጣጠስና የፋይናንስ ገበያዎችን በማናወፅ ላይ ናቸው፡፡ በሩሲያና በዩክሬን የሚመረቱ እንደ ስንዴና ነዳጅ የመሳሰሉ አቅርቦቶች በመስተጓጎላቸው፣ የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋዎች ከመጠን በላይ እያሻቀቡ ለመሆናቸው በርካታ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ የነዳጅ ዋጋ በእጥፍ በመጨመሩ የምግብ ምርቶች ዋጋም አልቀመስ እያለ ነው፡፡ ለዓለም 30 በመቶ የሚሆነውን ስንዴ የሚያቀርቡት ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ በመሆናቸው፣ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ተጎጂ እንደሚሆኑ እየተነገረ ነው፡፡ ኢትዮጵያም ዋነኛዋ ስንዴ ገዥ ስለሆነች ችግሩ እንደሚፀናባት ግልጽ ነው፡፡ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ከበጋ መስኖ ስንዴ ለማምረት ደፋ ቀናው የተጀመረ ቢሆንም፣ በስንዴ ራስን መቻል ባልተደረሰበት በዚህ ጊዜ የፀና ችግር እንደሚያጋጥም ይታወቃል፡፡ ለዚህም በምሳሌነት የሚጠቀሰው በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ዳቦዎች ማምረት የሚጠበቅበት ሸገር ዳቦ ሥራ ፈቶ ቁጭ ማለቱ ነው፡፡

በተደጋጋሚ ለማስገንዘብ እንደተሞከረው ኢትዮጵያ ምንም ሳይጎድልባት የድህነት መጫወቻ የተደረገች አገር ናት፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወጣት ኃይል፣ ሰፊ ለም መሬት፣ ትልቅ የውኃ ሀብት፣ በአፍሪካ አንደኛ የእንስሳት ሀብት፣ የበርካታ የከበሩ ማዕድናትና የመሳሰሉ ፀጋዎች ታቅፋ ብዙኃኑ ሕዝቧ የሚበላው ምግብ ማግኘት ከባድ ሲሆንበት ከማሳፈር የበለጠ ምን ሊባል ይችላል? የጠንካራ መንግሥት መገለጫው ችግሮች ሲያጋጥሙ ከመመከት በላይ፣ በዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች በመንደፍ አሳማኝ የዕድገት መሰላል ማበጀት ነው፡፡ ድንገተኛ ወረርሽኝ ወይም ድርቅ ቢያጋጥም፣ የዋጋ ግሽበት ቢከሰት ወይም የኑሮ ውድነትን የሚያባብስ ያልታሰበ ክስተት ቢፈጠር፣ በደህና ጊዜ የተዘጋጀ ፖሊሲና ስትራቴጂ በሚገባ ያገለግላል፡፡ ከዚያ ውጪ ብቃት በሌለው መንግሥታዊ መዋቅርና አመራር ሊገኝ የሚችለው ግብታዊ ዕርምጃ ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የዘመናት ችግርም ግብታዊነት ነው፡፡ በምግብ ዘይትም ሆነ በሌሎች ሸቀጦች ድንገተኛ የዋጋ ጭማሪ ሲደረግ፣ እሳት ለማጥፋት ዓይነት የሚደረጉ ርብርቦችና ሰበብ ድርደራዎች ፋይዳ ቢስ መሆናቸው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ መንግሥት የኑሮ ውድነቱን በዕውቀት ላይ በተመሠረተ መፍትሔ እንጂ፣ እንደለመደው በግብታዊ ዕርምጃ ለማስተካከል አይጣደፍ፡፡ ግብታዊ ዕርምጃ የኑሮ ውድነቱን አያረግብም! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...

በአዲስ አበባ ከ700 ሺሕ በላይ የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸው ተገለጸ

በአዲስ አበባ 716,624 የትራፊክ የደንብ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ የአዲስ አበባ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...