Sunday, March 3, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን ማዕከል በ400 ሚሊዮን ብር ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ11ኛው የኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በ400 ሚሊዮን ብር ወጪ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን ማዕከል ሊገነባ ነው፡፡

በቦንጋ ከተማ የሚገነባው ይህ ማዕከል ባለአራት ወለል ሕንፃና ትልልቅ መጋዘኖች የሚገነቡበት ሲሆን፣ ግንባታው ከ14 ወራት በኋላ ሲጠናቀቅ  በዓመት 150 ሺሕ ኩንታል በላይ ዘር ማዘጋጀት የሚችል የዘር ማበጠሪያ ማሽን መትከያ ቦታ፣ 120 ሺሕ ኩንታል የመያዝ አቅም ያላቸው የግብርና ግብዓት ማከማቻ መጋዘኖች፣ እንዲሁም የላብራቶሪና የቢሮ አገልግሎት መስጫ ክፍሎች ይኖሩታል ተብሏል፡፡

 የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከል ግንባታ የግብርና ግብዓቶችን ማለትም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና ኬሚካል የመሳሰሉትን በክልሉ እንዲሁም በአጎራባች ክልሎች ተደራሽ ማድረግን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ ታውቋል፡፡

የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከሉ በዋናነት ለመገንባት ሲታሰብ ከግምት ውስጥ ከተቀመጡት ጉዳዮች አንዱ ከቦንጋ ከተማ በ62 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የታማሻሎ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በማዕከሉ የሚገነቡት መጋዘኖች ከታማሻሎ እርሻ ልማት የተሰበሰበውን የምርጥ ዘር ከማበጠርና ማከማቸት አገልግሎቶች ባሻገር የማዳበሪያና የኬሚካል ግብዓቶችን በአካባቢውና አቅራቢያ ለሚገኙ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ለማዳረስ ነው፡፡ ይህም  እንደ ጋምቤላና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ያሉ ክልሎችን ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

አቶ ጋሻው እንዳስረዱት የካቲት 26 ቀን 2014 ዓ.ም. በቦንጋ ከተማ የግንባታ ስምምነትና የሳይት ርክክብ መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡ ግንባታው ደሳለኝ አስራደ የሕንፃ ተቋራጭና ምዕራብ ኮንስትራክሽን በተባሉ ሁለት የግንባታ ተቋራጭ ድርጅቶች አማካይነት የሚከናወን ሲሆን፣ በሁለት ተቋራጮች እንዲገነባ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ፈጥነው ወደ ሥራ ገብተው በ14 ወራት ወይም በ420 ቀናት እንዲያጠናቅቁ በመፈለጉ እንደሆነ አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

የሚገነቡት መጋዘኖች በአጠቃላይ 120 ሺሕ ኩንታል ዘር የመሸከም አቅም ያላቸው እንደሚሆኑ፣ ከሚገነቡት አራት መጋዘኖች ውስጥ ሁለቱ እያንዳንዳቸው 20 ሺሕ ኩንታል፣ እንዲሁም ቀሪዎቹ መጋዘኖች እያንዳንዳቸው 40 ሺሕ ኩንታል ምርት የመያዝ አቅም ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ከሚገነቡት መጋዘኖች በአንደኛው ግዙፍ የእህል ማበጠሪያ ማሽን እንደሚተከል ታውቋል፡፡

ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ በታማሻሎ እርሻ ልማት ያመረታቸውን የምርጥ ዘር ሰብሎች ለማበጠር በርካታ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ነቀምት መሄድ ነበረበት ያሉት ኃላፊው፣ ሆኖም በ62 ኪሎ ሜትር ርቀት በቦንጋ ከተማ የሚገነባው ይህ ግዙፍ ማዕከል ይህንን ድካም የሚያስቀር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና ሜካናይዜሽን ማዕከል ወደ ሥራ ሲገባ የክልሉን የግብርና ግብዓት አቅርቦትና የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽነት ችግር እንደሚቀርፍ፣ ለበርካታ የከተማው ነዋሪዎችም የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የግንባታ ስምምነት በተደረገበት መርሐ ግብር ላይ ተገልጿል፡፡

በጋምቤላና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች መሰል የማዕከላት ግንባታ ለማከናወን ኮርፖሬሽኑ የመሬት ጥያቄ እንዳቀረበ የተናገሩት አቶ ጋሻው፣ ይህም የምርጥ ዘር ማባዣ፣ የእርሻ መሬትና የተባዛው ምርጥ ዘር ማበጠሪያና ማዘጋጃ ማዕከላት ግንባታን የሚያጠቃልል ነው ብለዋል፡፡

ሁለቱ ክልሎች መሬቱን ለማቅረብ ተስፋ እንደሰጡ የተገለጸ ሲሆን፣ ተፈላጊው መሬት  በየትኛው የክልሎቹ አካባቢ ሊሆን ይገባል የሚለው በዚህ ወቅት በጥናት ላይ ይገኛል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በተጨማሪም የምርጥ ዘር መባዣ ወደ ሌላቸው ክልሎች ገብቶ እንደሚሠራ የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይ ከላይ ከተጠቀሱት ክልሎች በተጨማሪ በአማራና በሶማሌ ክልሎች አግልግሎቱን የማስፋት ሥራ እንደሚከናወን ተመላክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች