Monday, November 28, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊሸገር ዳቦ ዋጋውን በእጥፍ አሳድጎ ወደ ሥራ ተመለሰ

  ሸገር ዳቦ ዋጋውን በእጥፍ አሳድጎ ወደ ሥራ ተመለሰ

  ቀን:

  ባጋጠመው የግብዓት ዋጋ መወደድ ምክንያት ከአንድ ወር በላይ ለሚሆን ጊዜ አቅርቦቱን አቋርጦ የቆየው ሸገር ዳቦ፣ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ወደ ሥራ መመለሱ ተገለጸ፡፡ በ900 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ሥራ የጀመረው ሸገር ዳቦ፣ በአንድ ብር ከ20 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረውን ዳቦ በሁለት ብር ከአሥር ሳንቲም እንዲሸጥ መወሰኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታውቋል፡፡

  በ2012 ዓ.ም. ፋብሪካው ሲመረቅ በሰዓት 80 ሺሕ ዳቦ በማምረት በሦስት ፈረቃ እስከ ሁለት ሚሊዮን ዳቦ እንደሚያቀርብ ተነግሮ የነበረ ቢሆንም፣ ፋብሪካው በቀን ከ700 እስከ 800 ሺሕ ዳቦ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ካለፈው ዓመት መጋቢት ወር አንስቶም በቀን የሚያመርተው የዳቦ መጠን ወደ 1.5 ሚሊዮን ማደጉ መገለጹ ይታወቃል፡፡

  ይሁንና ለዳቦ ማከፋፈያነት በተሰጡት 400 ያህል አገልግሎታቸውን የጨረሱ አንበሳ አውቶብሶች አማካይነት በሚቀርበው ዳቦና በነዋሪዎች መካከል ባለው የፍላጎት መጠን መካከል ከፍተኛ ልዩነት አለ፡፡ ፋብሪካው ሥራ በጀመረ በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለ70 ሚሊዮን ብር ኪሳራ መዳረጉን አስታውቆ ነበር፡፡

  ፋብሪካው ከአንድ ወር በፊት ሥራ ሲያቆም የግብዓት እጥረትና የዋጋ መወደድ እንዳጋጠመው ያስታወቀ ሲሆን፣ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግም ለከተማ አስተዳደሩ ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡

  የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳዳር ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በሸገር ዳቦ መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ መደረጉን ተናግረው የከተማ አስተዳደሩ የሚያደርገው ድጎማም ማደጉን አስታውቀዋል፡፡ እንደ አቶ መስፍን ገለጻ የከተማ አስተዳደሩ ሁለት ብር ከአሥር ሳንቲም ለሚሸጠው ዳቦ አንድ ብር ከ14 ሳንቲም ድጎማ ያደርጋል፡፡ ለዚህም አስተዳደሩ በዓመቱ ከ613 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡

  ለሸገር ዳቦ በየወሩ 100 ሺሕ ኩንታል ስንዴ የሚያቀርበው የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 309.3 ሚሊዮን ብር ድጎማ አድርጓል፡፡ ይሁንና የስንዴ ዋጋ መጨመር ችግር መፍጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የካቲት መጀመሪያ ላይ በተካሄዳው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን አንደኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ ተናግረው ነበር፡፡

  የከተማ አስተዳደሩ ከሸገር ዳቦ በተጨማሪ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ተገንብቶ በጥቅምት ወር የተመረቀውን ብርሃን ዳቦ ፋብሪካ ሥራ ለማስጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑን ከንቲባዋ አስታውቀዋል፡፡ ለከተማ አስተዳደሩ የተሰጠው ፋብሪካው በቀን አንድ ሚሊዮን ዳቦና 72 ቶን ዱቄት እንደሚያመርት በምረቃው ወቅት ተነግሯል፡፡

  ኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ ፍላጎቷን የምታሟላው ከአገር ውስጥ ምርት ቢሆንም፣ በየዓመቱ 1.7 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ከውጭ ታስገባለች፡፡ መንግሥት በጥቅምትና በኅዳር ወራት የአራት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ግዥ የተከናወነ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ኩንታል ስንዴ ወደ አገር ውስጥ መግባቱ ተገልጾ ነበር፡፡

  ጦርነት ውስጥ የገቡት ሩሲያና ዩክሬን የዓለምን 30 በመቶ የስንዴ ሽያጭ ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ አገሮቹ ወደ ጦርነት ከገቡ በኋላ እ.ኤ.አ. ከ2008 ወዲህ ከፍተኛ የሆነው የስንዴ ዋጋ ጭማሪ ተመዝግቧል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...