- የዛሬው ስብሰባ የተጠራው በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ እንደመሆኑ መጠን፣ አንገብጋቢና አሳሳቢ በምትሏቸው ጉዳዮች ላይ መወያየታችንን መጀመር እንችላለን።
- እዚያ ጋ… አዎ አንተ መቀጠል ትችላለህ…
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር ኢንፎርማል በሆነ መንገድ እየተደራጁ ያሉ ታጣቂዎች ጉዳይ…
- ክቡር ሚኒስትር ከተነሳው ጉዳይ የሚበልጥ ሌላ አንገብጋቢው የዘይት ጉዳይ እያለ…
- አቁም… እንድትናገር ዕድል አልሰጠሁህም…
- ክቡር ሚኒስትር…?
- አቁም አልኩኝ እኮ! ማነህ የጀመርከውን ቀጥል!
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የጦር መሣሪያ የታጠቁ ኢንፎርማል አደረጃጀቶች ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሔ ካላገኘን የአገሪቱን የፀጥታና የፖለቲካ መረጋጋትን የማወክ አቅሙ ትልቅ ነው።
- ትክክል ነው፣ ይህንን ችግር የመፍታት ኃላፊነትም ሆነ ባለቤቶቹ የሚመለከታቸው ክልሎች ናቸው፣ የማዕከላዊ መንግሥት ኃላፊነት ድጋፍ መስጠት ነው፣ በተለይም የመረጃ ድጋፍ በማድረግ የምንከታተለው ጉዳይ በመሆኑ እንደተባለው ጊዜ ወስደን ልንነጋገርበት የሚገባ አጀንዳ አልመሰለኝም።
- ክቡር ሚኒስትር ቀደም ብዬ ያነሳሁት የዘይት ጉዳይ አንገብጋቢና ፖለቲካዊ ሴራ ያለበት መሆኑን ደግሜ ማሳወቅ እፈልጋለሁ።
- ፖለቲካዊ ምን አለበት ነው ያልከው?
- ከጀርባው ጥልፍልፍ ፖለቲካዊ ሴራ የያዘ ጉዳይ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እሺ፣ በል ከጀርባ ስላለው ፖለቲካዊ ሴራ ትኩረት ሰጥተህ እንድትናገር ዕድል ሰጥቼሃለሁ።
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ መቼም የአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ ሰሞኑን አንድ ሺሕ ብር እንደገባና ማኅበረሰቡን እንዳስደነገጠ ሰምታችኋል ብዬ አስባለሁ።
- አዎ፣ እኛም መጀመርያ ስንሰማ ደንግጠን ነበር…
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎም ደንግጠው ነበር?
- ማነህ ወንድሜ…. ለምን ወደ ሴራው አትገባም!
- ምን አሉኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ከጀርባ አለ ስላልከው የፖለቲካ ሴራ ለምን አትሻገርም?
- ድንጋጤው ይዞኝ ነው እንጂ እየተሻገርኩ ነበር ክቡር ሚኒስትር።
- ኦ… ኦ… እንዴት ያለ ነገር ነው?
- እኔንም አስገርሞኛል ክቡር ሚኒስትር፣ ከዘይት ጀርባ የፖለቲካ ሴራ ይኖራል ብዬ ገምቼ አላውቅም ነበር።
- ይኼ ሰውዬ ለምን ስለሴራው አያወራም?
- ወደ እዚያው ነኝ ክቡር ሚኒስትር… አመራሩ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት በየተቋሙ ጓሮ ያለማው አትክልት ለምግብነት በደረሰበት ወቅት፣ እንዴት የዘይት ዋጋ በድንገት አንድ ሺሕ ብር ሊገባ ቻለ?
- ይኼ ነው የፖለቲካ ሴራው?
- ክቡር ሚኒስትር አመራሩ የጓሮ አትክልቱን እየጎበኘ ባለበት ወቅት የዘይት ዋጋ በድንገት የተወደደው ያለምክንያት አይደለምኧ የለፋንበትን የጓሮ አትክልት ለማኅበረሰቡ እንዳናቀምስና ልፋታችንን መና ለማስቀረት ነው።
- አልሰሜን ግባ በለው አሉ።
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- እያለማነው ያለው የጓሮ አትክልት ዘይት አይፈልግም፣ በዳቦ ብቻ መበላት ወይም በውኃ ብቻ ተቀቅሎ መበላት የሚችል ነው።
- ክቡር ሚኒስትር እርስዎ እንደዚያ ቢሉም…
- ተው… ዕድል አልሰጠሁህም… እሺ ጥግ ላይ ያለኸው… አንተ… አዎ…
- አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር የዘይት ጉዳይ እንደተባለው
- አንተም ዘይት ላይ ነህ?
- እኔ እንኳ የተሳሳተ መረጃ ለማጥራት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ጥሩ፣ ቀጥል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር የዘይት ዋጋ መናር በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ አይደለም፣ ነገሩ በዩክሬን ከተከሰተው ጦርነት ጋር የሚገናኝ በበርካታ የዓለም አገሮችም የተከሰተ እንጂ ከአገር ውስጥ ፖለቲካ ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም።
- ክቡር ሚኒስትር የተሳሳተ ነው…
- ዕድል ሳልሰጥህ አትናገር አላልኩም እንዴ? የስብሰባ ሥነ ሥርዓት ይከበር እንጂ፡፡
- ይቅርታ ክቡር ሚኒስትር ትክክል ባልሆነ መረጃ ተሰብሳቢው እንዳይሳሳት ብዬ እንጂ፣ ሥነ ሥርዓቱን ለመጣስ አልነበረም።
- እሺ፣ የተሳሳተው መረጃ ምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር በዩክሬን የተቀሰቀሰው ጦርነት መከሰት ያልነበረበት አሳዛኝ አጋጣሚ ቢሆንም…
- ይኼ ሰው እንዴት ሆኖ ነው አማካሪ ኮሚቴው ውስጥ የገባው?
- ምን አሉ ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን በቀጥታ ወደ ጉዳዩ አትገባም? የተሳሳተ መረጃ ያልከው ምንድነው?
- ወደ እሱ እየገባሁ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ቀጥል እሺ…
- አንዳንዶች የዘይት ዋጋ የተወደደው በዩክሬን በተቀሰቀሰው ጦርነት ይበሉ እንጂ፣ የሚሉት ነገር በፍፁም የተሳሳተ ነው።
- አሱንማ ነገርከን እኮ…? ትክክለኛው መረጃ ምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር ከዩክሬን ጦርነት ጋር ተያይዞ ዋጋው በዓለም አቀፍ ደረጃ የጨመረው የምግብ ዘይት አይደለም፣ በፍፁም።
- ምንድነው ታዲያ?
- የነዳጅ ዘይት ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጠዋት ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የእጅ ስልካቸው መጥራት ጀመረ። ትይዩ ሚኒስትር ተብለው የተመደቡ አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናቸው የደወሉት]
- ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? አስታወሱኝ?
- ኦ… ሞክሼ፡፡
- ሃሃሃ… ሞክሼ አሉኝ?
- ባለፈው ስንተዋወቅ እኔም ክቡር ሚኒስትር ብዬ ስጠራህ ፌዝ ስለመሰለህ መቀየሬ ነው።
- ችግር የለውም… ካስታወሱኝ በቂ ነው።
- እሺ ዛሬ ምን አገኘህ? ማለቴ ምን አገኘህብን?
- ክቡር ሚኒስትር በተለይ በከተሞች እየተከሰተ ያለውን ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ብዙ ያሳሰባችሁ አልመሰለኝም፣ መሠረታዊ የዕለት ሸቀጦች በሙሉ ዋጋቸው በከፍተኛ ደረጃ ቢንርም መንግሥት በተለይም የሚመለከተው የእርስዎ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከችግሩ ግዝፈት አኳያ እየተንቀሳቀሰ አለመሆኑ አሳስቦናል።
- እኔም የዘይት ዋጋ በድንገት በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ስሰማ ጠርጥሬ ነበር።
- ምን ጠረጠሩ?
- ትይዩ ካቢኔው ሥራውን በእኔ መሥሪያ ቤት ላይ እንደሚጀምር ነዋ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር እኛ ለመጀመር ወይም ለዝና ብለን አይደለም ይህንን አሠራር ያስተዋወቅነው፣ ዋና ዓላማችን መንግሥትንም ሕዝባችንንም ለማገዝና መፍትሔ ለመጠቆም ነው።
- እውነተኛ ዓላማው እንደምትለው ቀና ከሆነ መልካም ነው፣ እና ታዲያ ምን ልርዳህ?
- ክቡር ሚኒስትር መሠረታዊ የፍጆታ ሸቀጦች በተለይም ምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ በእጅጉ እየናረ ቢሆንም፣ መንግሥት በችግሩ ልክ እየሠራ አለመሆኑ በእውነት አሳስቦናል፣ ሌላው ይቅር የከተማው ደሃ ዳቦ እንኳን ገዝቶ መብላት አልቻለም እኮ?
- በእርግጥ ችግሩ አለ፣ ነገር ግን አንተ እንደምትለው የተጋነነ አይደለም፣ በዚያ ላይ መንግሥት ችግሩን ዝም ብሎ እየተመለከተ አይደለም።
- መንግሥት ምን አደረገ? ምንም ዓይነት መፍትሔ የሚያመጣ ውሳኔ ሲሰጥ ወይም ተግባር ሲከውን እያየን አይደለንም?
- ተሳስተሃል፣ መንግሥት የዋጋ ንረቱ አዝማሚያና የሚያስከትለውን የኑሮ ውድነት በጥልቀት ገምግሞ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፎ ወደ ተግባር የገባው ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ነው።
- እኮ ምን? እንደዚያስ ከሆነ ምን መፍትሔ ተገኘ?
- የምታስታውስ ከሆነ ከውጭ በሚገቡ መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ይከፈሉ የነበሩ ቫት፣ ኤክሳይስ ታክስና መሰል ቀረጦች ለጊዜው ቀሪ እንዲሆኑ የወሰነው ባለፈው ነሐሴ ወር ነው፣ የዳቦ ዱቄት፣ ዘይት፣ ፓስታ፣ ስኳርና መሰል የፍጆታ ዕቃዎች ከታክስ ነፃ እንዲገቡ የተወሰነው ችግሩን ቀድመን መመልከት ስለቻልን ነው።
- ይህንን ውሳኔ አስታውሳለሁ፣ ነገር ግን የተባለውን ውጤት አላመጣም።
- እንዴት አላመጣም ትለኛለህ? በዚህ ውሳኔ ምክንያት መንግሥት ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ምን ያህል የታክስ ገቢ ሊያገኝ እየቻለ የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ቀሪ እንዳደረገ ታውቃለህ? በስድስት ወራት ብቻ 18 ቢሊዮን ብር የታክስ ገቢ በመተው የሕዝቡን ጫና እየተጋራ ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ምን ያህል የታክስ ገቢ ቀሪ እንደተደረገ ሚዲያዎች ዘግበውት ተመልክቻለሁ፣ ለመደወል ምክንያት ከሆኑኝ ጉዳዮች መካከልም አንዱ ይህ ስህተት ነው።
- ስህተት? እንዴት?
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት ኑሮን ለማረጋጋት ብሎ ከውጭ በሚገቡ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ ታክስ እንዳይከፈል ማድረጉ ድንቅ ውሳኔ ነበር፣ ነገር ግን ማኅበረሰቡ ያገኘው ጥቅም የለም።
- እንዴት?
- ምክንያቱም ቢያንስ ቀሪ እንዲሆን በተደረገው ታክስ ልክ የሸቀጦች ዋጋ መውረድ ነበረበት፣ ነገር ግን ከዚህ ውሳኔ የተጠቀሙት አስመጪዎች ናቸው።
- በእርግጥ አሁን ያነሳኸውን ችግር እኛም በቅርቡ ባደረግነው ግምገማ ተመልክተነው አስመጪዎችን ለመቆጣጠር መመርያ እያዘጋጀን ስለሆነ በቅርቡ ይስተካከላል።
- አይስተካከልም።
- እንዴት?
- በፍፁም ነጋዴው አይሰተካከልም።
- ለምን?
- ምክንያቱም ነጋዴው ብቻውን ሆኖ ያደረገው ነገር እንዳልሆነ ይታወቃል።
- ማለት?
- ምክንያቱም መንግሥት በስድስት ወራት ብቻ 18 ቢሊዮን ብር ታክስና ቀረጥ ቀሪ ያደረገበት ግብይት ዓላማውን ስቶ የሸቀጦች ዋጋ መናሩ ቀጥሏል ማለት፣ መንግሥት ያጣው 18 ቢሊዮን ብር አስመጪዎች እጅ ገብቷል ማለት ነው፣ ይህ ደግሞ መንግሥት ውስጥ ያሉ ሰዎች ተቋዳሽ ነበሩ ማለት ነው፣ በአስመጪነት የሚሠሩ በገዢው ፓርቲ የተቋቋሙ ድርጅቶችም እንዳሉበት ይወራል።
- ጥርጣሬህ ውኃ ቢያነሳም፣ እኛ ባደረግነው ግምገማ እንደዚያ ዓይነት ምልክት አላየንም፡፡
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት መፍትሔው ውሳኔውን መከለስ ነው፣ በስድት ወራት የታጣው 18 ቢሊዮን ብር በዓመት 36 ቢሊዮን ብር ወይም የትልልቆቹ ክልሎች ዓመታዊ በጀት ነው።
- እና ምን መደረግ አለበት ነው የምትለው? በእናንተ በኩል የሚቀርብ መፍትሔ ካለ ለመስማት ዝግጁ ነን።
- መልካም፣ መንግሥት ከውጭ በሚገቡ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ እንዲነሳ ያደረገውን ቀረጥና ታክስ ወደ ቦታው በመመለስ በስድስት ወራት ውስጥ ያጣውን 18 ቢሊዮን ብር ወይም ለአንድ ዓመት ቢቀጥል የሚያጣውን መጠን ለደመወዝ ጭማሪ ይመድብ።
- ምን መፍትሔ ያስገኛል?
- ያስገኛል፣ ይህ ከተደረገ ማኅበረሰቡ የዋጋ ንረቱን መቋቋም ይችላል፣ የመንግሥት ወሳኔም ዓላማውን ይመታል፣ ነጋዴውም የማይገባውን ሳይሆን ተገቢውን ትርፍ ያገኛል።