Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዘይት ያለውና የሌለው!

ጉዞ ከጦር ኃይሎች ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። ‹‹እኔ ምለው ዘይት የሌለው ሽሮ ብቻ እየበሉ ስቴኪኒ የሚይዙ ሰዎች የበዙት ለምድነው?›› ትጠይቃለች ቢጫ ካኔቲራ የለበሰች ተሳፋሪ። ችፍፍ ያለ ላቧን በመዳፏ እየጠረገች ጥራጊው ውስጥ ልዩ ሐተታ እንደምታነብ ሁሉ፣ አተኩራ መዳፏን ስታጠና መጠይቋን የረሳች ትመስላለች። ‹‹አንዳንዴ ሁኔታችን ህያዋን በድኖች ስለመሆናችን በግልጽ ያስታውሰናል። ያልበሰለ ነገር እንዳትቀምሱ እየተባለ ስለሚወራ ምናልባት የጥሬ ሥጋ ናፍቆታችንን በስንጥር የምናጣጣ መስሎን ይሆናላ…›› ሲላት በላብ የወዛ መዳፏን በተቀመጠችበት ኪሷ ከታ፣ ‹‹ምን አልክ?›› አለችው መልስ የሰጣትን ጎልማሳ በሰያፍ እያየች፡፡ ‹‹ዘይት የሌለው ሽሮ እየበላ በስንጥር ጥርሱን የሚጎረጉረው በዛብኝ ስትይ የሰማሁሽ መሰለኝ?›› ጎልማሳው ሳትደርሽብኝ አልደረስኩብሽም ዓይነትያት፡፡ ‹‹እኔ እኮ ዘይት አልባ ሽሮ ለቀልድ ነው ያልኩት አከረርከው እንዴ?›› ብላ ፈገግ አለች፡፡ ጥርሶቿ ሃጫ በረዶ መስለው ልብን ወከክ ያደርጋሉ፡፡ በስንቱ ወከክ ብለን እንችለዋለን!

ይኼን እንደ እኔ የታዘበ አጠገቤ የተቀመጠ ተሳፋሪ ‹‹ኧረረ…›› ብሎ ጉቺ መነጽሩን ከመቅጽበት አወለቀ፡፡ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች አለባበሷና ሥነ ሥርዓቷ ሁሉ እንደ ሚኒስትር ልዩ ጸሐፊ የሚያደርጋት ወይዘሮ በበኩሏ፣ ‹‹አገራችን የብልፅግና ጎዳና ለመጀመር ስትነሳ ወደ ድህነት የሚመልሱ ወሬዎች ላይ ባናተኩር መልካም ነው…›› እያለች የነገር ጧፍ መለኮስ ጀመረች፡፡ የእረኛ በሚመስል ዘመናዊ ቆብ ላይ ኢርፎን ጆሮው ሰክቶ አጠገቧ የተቀመጠ ወጣት፣ ከእሱ አልፎ ሾፌሩ ድረስ በሚሰማ ሬጌ ሙዚቃ ሲወዛወዝ ሌላም ነገር ብላው ቢሆን አልሰማትም፡፡ ላንሰማማ ስንጠያየቅ፣ ላንግባባ ስንለፋለፍ ቀኑ በወሬና በአግቦ ድንቁርና ያለ ፍሬ ያልፋል፡፡ ይኼም ጊዜ የሰላም፣ የብልፅግናና የዕድገት ይባላል፡፡ ለመባል ግን ከእኛ በኩል በጣም ብዙ ይቀራል፡፡ በጣም ብዙ!

ጉዟችን ከተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች ጠፍተዋል። ሾፌሩ በልዩ ትዕግሥትና ችሎታ ተሳስተው የሚያሳስቱትን ቀለብላባ አሽከርካሪዎች ቅድሚያ እየሰጠና እያባበለ አልፎ ቦታ እየለቀቀ፣ ‹‹ወይ ጉድ ተመልከቱት እስኪ?›› ብሎ በአግቦ ሂስ ችሎት እንደ ዓቃቤ ሕግ ክስ እየመሠረተ ያሽከረክራል፡፡ ወያላው መንገዱን፣ ገንዘቡንና ሥራውን ረስቶ አዲስ አበባ ከመጣባት ከዛሬ ስድስት ዓመት እስከ ዛሬ ድረስ፣ አገሩ ምን ያህል እደተለወጠ አገር ቤት ካለው ዘመዱ ጋር በስልክ ይጫወታል፡፡ ‹‹ኧረ ሒሳቡን ተቀበለን ካርድህ ሳያልቅ?›› ይላል መጨረሻ ወንበር የተሰየመ ራሰ በራ ወጣት፡፡ ‹‹ቢያልቅ ይሞላላ፣ አንተ አለህ አይደል ፀጉርህ ያለ ዕድሜህ ሲያልቅ ዝም ብለህ ያየህ፡፡ ቆይ ለምንድነው ያኔ ከጀርመን ያመጣሁትን ቅባት አልቀባም ያልከው?›› ያሳጣዋል በጎንዮሽ የተቀመጠ ወዳጁ፡፡ ወይ ጉድ!

‹‹እስኪ አሁን ጀርመን ደርሶ መምጣቱን ሙያ ብሎት ዕወቁልኝ ነው? ብቻቸውን ሲሆኑ እኮ ይኼኔ እንኳን እንዲህ ሊያስብለት፣ ቀድሞት ባረጀ ወዳጁ ላይ እሰይ ሲል ነው የሚውለው…›› ይለኛል አጠገቤ የተቀመጠው፡፡ ‹‹አይ የእኛ ሰው፣ ይኼው የስቴኪኒው ነገር መጣ እኮ ሰውዬው፡፡ ዘይት የሌለው ሽሮ እየበላን በስቴኪኒ የመጎርጎር አመላችን ሥር ሰዶ ገንዘብ ሳይኖረን ባለ መስመር ስልክ፣ ፀጉር ሳይኖረን ማበጠሪያ አድናቂዎች፣ ቤት ሳይኖረን ሞዴል መኪና አዳኞች፣ ለኪራይ ቤት የምንከፍለው ሳይኖረን የሱፐር ማርኬት ተገበያዮች…›› እያለች ስትቀጥል፣ ‹‹ምነው ደግ ደጉን ብቻ አነነሳሽው እህት? የመንግሥት ደመወዝተኛ ሆነው ባለ ሕንፃና ፋብሪካ፣ ታክሲ ሹፍርና ላይ ተሰማርተው የጫኑትን ሕዝብ ሳያራግፉ መሀል መንገድ ላይ ወርደው ባለ አምስት ኮከብ ሆቴል ባለቤት የሆኑትንና ሌሎችን ወዴት ረሳሻቸው? ይኼም እኮ በቅቤ ያበደ አሮስቶ በልቶ ስቴኪኒ የመጠቀም አባዜ ታላቁ ደረጃው ነው…›› ብሎ ጎልማሳው የሽሙጥ ካካታውን ለቀቀው። ወይ ነዶ!

ወያላው በስንት ግብግብ ስልኩን ለሾፌሩ አስረክቦ ሒሳብ መሰብሰብ ጀምሯል፡፡  ‹‹አንተ ይኼን ያህል ምን ተማምነህ ነው በስልክ ይኼን ሁሉ የቤተሰብ ሚስጥር የምታወራው?›› ጠየቀ ዝምተኛው ሾፌራችን፡፡ ‹‹ታዲያ በደብዳቤ ላወራ ኖሯል? ኧረ ጋሼ ሞኝ ነዎት ልበል አንዳንዴ? ጊዜው እኮ ሠልጥኗል፡፡ በእኛ የቀበሌ ገበሬ ማኅበር ባለ ሞባይል ያልሆነ ማን አለ? እኔ ከተማ ተቀምጬ አዲስ አበባ ገባ ተብዬ እየተወራልኝ ገና ለገና መንግሥት የማወራውን ያዳምጣል ብዬ ፈርቼ ደብዳቤ ብጽፍ ሰው ያደርጉኛል? እኔ ተንቄ ቤቴሰቤን ከማስንቅ ደግሞ የስልክ ጭውውቴ ሲቀዳ ቢኖር እመርጣለሁ…›› ብሎ ወያላችን ዘራፍ አለ፡፡ ‹‹ይገርማል እኮ እናንተ ውርደት ክብር የሆነባት አገር…›› ሲል ደግሞ ጎልማሳው ወሬ ጀመረ፡፡ ‹‹ምን ተገኘ ደግሞ?›› አለች ቢጫ ለባሿ ያንን በረዶ ጥርሷን በመፋቂያ አሳሩን ማብላት እየጀመረች፡፡ ‹‹በሠለጠኑት አገሮች መንግሥታት ኢሜይል፣ ስልክና ፖስታ እየከፈቱ፣ ኮድ እየሰበሩ፣ መስመር እየጠለፉ ያነባሉ፣ ያዳምጣሉ የሚል መረጃ ከወጣ ቀን ጀምሮ ሕዝብና መንግሥት ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡ እዚህ በብሔራዊ ዜና ማሠራጫ ጣቢያ የተጠለፈ ስልክ በዜና እንድንሰማው ይደረግ እንደነበር ተረሳ እንዴ? እያንዳንድሽ የምትተነፍሽው ሳይቀር  ይታወቃል፣ ገቢቶ…›› ሲል አዳነቀ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምኑን ከምኑ ነው የሚገጣጥሙት? ወይ የዘመኑ ሰው!

ጋቢና ከተሰየሙ ሁለት ወጣቶች አንደኛው፣ ‹‹አይ አንተ ምን ይገርማል ይኼ? በመላው ዓለም እንኳን ስልክ መጥለፍ ቀርቶ የዕለት ተዕለት የሕዝቡ እንቅስቃሴ፣ አገባብና አወጣጥ በቪዲዮ በተደገፈ ማስረጃ በድሮን ይሰለላል ብልህ አታምንም ታምናለህ?›› ሲል፣ ‹‹አመንን አላመንን ዕድሜ ለሆሊውድ እንዳይሞቀን እንዳይበርደን አድርጎ ጉድ ሠርቶናል…›› አለች ከመጨረሻ ወንበር። ‹‹ዕውን ኢትዮጵያ የአየር ድብደባ እንጂ የመጥለፊያ ድሮን አላት?›› ሲል ሌላው ወይዘሮዋ ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ጀስት ኢማጂንያልጠረጠረ ተመነጠረ እንዳይሆን ጀስት ኢማጂን…›› ብላ ጠቀሰችው፡፡ መቼ ነበርገንፎ ውስጥ ስንጥር አይጠፋምየተባለው? ደመና ውስጥ ሰላይ ድሮን ይኖር እንዴ? ትከሻችሁን ከከበዳችሁ ጀስት አሲዩምእሺ… እንግዲህ ከፖለቲካው ራቅ ብላችሁ መደበኛው ሕይወት ውስጥ ስትገቡ ወሬው ሁሉ እንዲህ ነው የሚመስለው!

ወደ መዳረሻችን መከረኛ ፖለቲካ ለጉዞአችን ማሳረጊያ ይመስል ተጀመረ፡፡ ‹‹ጎበዝ ምንድነው እንዲህ በጥቅል የውክልና አስተሳሰብ የሚያምሰን የበዛው?›› ብሎ ፀጉሩ ወደ ኋላ የሸሸው ምሬት አቀረበ። ‹‹እንዴት?›› አለው ወዳጁ፡፡ ‹‹ጉድ እኮ  ነው  አንዱ  ነገረኛ  ተነስቶ ከእንግዲህ  የእንትን ሕዝብ  አቋም  ይኼ  ነው  ሲል  ቁርጡን  ይነግርሃል፡፡  አንዱ  ግብዝ  ይነሳና  በቃ  እንትን ከእንግዲህ  ወዲህ  መንገዱ  ይኼ  ብቻ  ነው  ሲል  እቅጩን  ይነግርሃል፡፡  አንዱ  ወፈፌ  ተነስቶ  የእንትን  ብቸኛ  አማራጭ  ይኼ  ብቻ  ነው  ሲል  ከዚያ  በመለስ  እንደማይደራደር  ይነግርሃል፡፡  እንዴት  ነው ግን  አንድን  ሰፊ  ማኅበረሰብ  ወክሎ  እንዲህ  መናገር  የሚቻለው?  ለዚያውም  በሚሊዮኖች  የሚቆጠር  ሕዝብ፣  ትክክለኛ  ፍላጎትና  አቋሙን  ማወቅ  የሚቻለው  በዴሞክራሲያዊ  ሥርዓት  በሚሰጥ  ድምፅ  ብቻ  ነው፡፡ ከዚያ  ውጪ አንድን ሕዝብ  ያለ ዕምነቱ፣ ያለ ፍላጎቱና ያለ ምርጫው  በአንድ  ኮረጆ  ለማስገባት  መሞከር  በትንሹ  ግብዝነት፣  በትልቁ  በዘረኝነት  የታጀበ  የአምባገነንነት  ክፉ  ልክፍት  ነው…›አለ፡፡ ሌላው ጎልማሳ ደግሞ፣ ‹‹የሚያደክም  ነገር  ነውበቡድን  ማሰብ  እንዴት  እንደሚቻል  አልገባ  አለኝ  እኮ? እኔ  ከራሴ  ጋር  ተስማምቼ  ማሰብ  አቅቶኛል  የአገሬ  ሰው  ሚሊዮን  ሆኖ  እንደ  አንድ  ያስባል  ይሉኛል፡፡ እስቲ  እንደ ሰው ለራሳችን እንድናስብ  ተውን…›› ብሎ ሲያበቃ፣ ‹‹ወራጅ!›› ብሎ ጮኸ፡፡ ደርሰን ነበርና ታክሲያችን ጥጓን ያዘች፡፡ ወያላውመጨረሻብሎ በሩን ከፈተው፡፡ ጎልማሳው መንገዱን እየያዘ፣ ‹‹በቡድን አስተሳሰብ ከመዋጥ በራስ አስቦ መወሰን ቢቀድምስ? ሁላችንም ዘይት የሌለው ሽሮ ብንበላም አንድ ቅርጫት ውስጥ ግን አንጠቅጠቅ… ዘይት ያለውና የሌለው እያልን ብንቀልድ ይሻለናል…›› እያለ ተለየን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት