ዓመታዊውን የዓለም ሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ፣ በሴት የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ የተመራ የቀዶ ሕክምናን የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ሰጥቷል፡፡
‹‹ማርች 8›› ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀውን የዓለም ሴቶች ቀን፣ በኮሌጁ በሥራ ገበታ ላይ በመሳተፍ ያከበሩት ሴት የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶችና የተለያየ የሕክምና ዘርፍ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
በዕለቱ ሴት ሐኪሞች ለ23 ታካሚዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት በመስጠት ያከናወኑት ተግባር ሴቶች ሊወጡት የማይችሉ ሥራ እንደሌለ በተግባር ያስመሰከረ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይህ ዓይነቱን እንቅስቃሴ የበለጠ አጠናክረው ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን በሥራው የተሳተፉ ስፔሻሊስት ሐኪሞች ነግረውናል፡፡
ካነጋገርናቸው የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስቶች መካከል በዕለቱ እስከ ረፋዱ አራት ሰዓት ድረስ ለአንድ ታካሚ የቀዶ ሕክምና አድርገው፣ ሌሎች ስድስት ታካሚዎችን በየተራ የቀዶ ሕክምና ለማድረግ በዝግጅት ላይ የነበሩ የቀዶ ሕክምና ረዳት ፕሮፌሰሮቹ መሠረት ሺበሺ (ዶ/ር) እና ማርታ ሰይድ (ዶ/ር) ይገኙባቸዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰሮቹ የዓለም የሴቶችን ቀን ምክንያት በማድረግ የቀዶ ሕክምና ክፍሉ ሙሉ ሒደት በሴቶች ብቻ ለማከናወን ታቅዶ የመጀመርያው ቀዶ ሕክምና በጥሩ ሁኔታ አከናውነው ቀጣዩን ለማከናወን በዝግጀት ላይ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በሰባት አልጋዎች ላይ ለቀዶ ሕክምና ዝግጁ የሆኑ 23 ታካሚዎች እንዳሉ ለመጀመርያው ታካሚ የሀሞት ከረጢት ጠጠር እንዳወጡለት ረዳት ፕሮፌሰሮቹ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
በተለይ መሠረት ሺበሺ (ዶ/ር) እንዳብራሩት ታካሚዎች ከዋርድ መጥተውና ቀዶ ሕክምና ክፍል ገብተው አስፈላጊው ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ወደየአልጋቸው እስከሚመለሱ ድረስ ያለው የሥራ ሒደት በሙሉ በሴቶች የተሸፈነ ነው፡፡
በዚህም መሠረት ሁሉም ሴቶች የሆኑ ሁለት የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ሁለት የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት ተማሪዎች፣ ሁለት የሰመመን ሰጪ ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ ሦስት ነርሶች፣ የፅዳትና ታካሚዎችን የሚያስገቡና የሚያስወጡ ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡
‹‹በሥራ ላይ ያጋጠማችሁ ችግሮች አሉ ወይ? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ መሠረት (ዶ/ር) ሲመልሱ፣ ‹‹የተለያዩ ችግሮች አሉ፡፡ ሴት ሆኖ ሲሠራ ደግሞ በተጨማሪ ሌሎች ችግሮች መኖራቸው አይቀርም፡፡ መፍትሔው ችግሮቹን ሁሉ ተቋቁሞ መሥራት ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡
ከችግሮቹ መካከል አንዱና ዋነኛው የቀዶ ሕክምና በወንዶች እንጂ በሴቶች እንደማይሠራ በአብዛኛው ኅብረተሰብ ዘንድ ሠርፆ የቆየው ችግር መሆኑን ገልጸው፣ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑንና የቀዶ ሕክምና አሁንም በቀጣይም በሴቶች የሚሠራ መሆኑን ለማሳየት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
ይህ ዓይነቱም እንቅስቃሴ በቀዶ ሕክምና ዘርፍ ለመሠማራት ለሚፈልጉ ሴቶች መልካም አጋጣሚና ማነቃቂያ፣ ሴቶች የተለያዩ ከባድ ሥራዎችን ማከናወንም እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ከማብራሪያቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሥራው የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ብቻ በመስጠት የሚቆም ሳይሆን ታካሚውን መከታተል፣ ጤንነቱ እስኪመለስ ድረስ አስፈላጊውን ክብካቤ መስጠትና ሌሎች ተጓዳኝ የሆኑ ሥራዎችን ማከናወንን እንደሚጨምር መሠረት (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ በቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ማርታ ሰይድ (ዶ/ር) በበኩላቸው ቀዶ አካሚዎቹ ሴት ሐኪሞች ቢሆኑም አገልግሎቱን በሚያገኙት ላይ ግን የፆታ ልዩነት እንደሌለው ነው የገለጹት፡፡
በተያያዘ ዜናም ይኸው የዓለም የሴቶች ቀን የካቲት 29 ቀን በቸርችል ጤና ጣቢያ መታሰቡን የጤና ሚኒስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ገልጿል፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የሚኒስቴሩ የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዳይሬክተር መሠረት ዘላለም (ዶ/ር)፣ ማኅበረሰቡ ወንድ ልጆቹ የሴቶችን እኩልነት ከማረጋገጥና ሴቶችና ልጃገረዶችን የሚያከብር፣ የሚወድና የሚደግፉ እንዲሆኑ አበክሮ መሥራት አለበት ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሯ አያይዘውም በየዓመቱ ከ11,000 የማያንሱ እናቶች፣ ሴቶችና ልጃገረዶች መከላከል በሚቻሉት የተለያዩ በሽታዎች እንደሚሞቱ የገለጹ ሲሆን፣ ይህንን ቁጥር ከመቀነስ ረገድ የባሎች፣ የወንድሞች እንዲሁም የአባቶች ሚና ከፍተኛ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
ይኸው የሴቶች ቀን በኢትዮጵያ ‹‹እኔ የእህቴ ጠባቂ ነኝ” በሚል በራሷ መሪ ቃል ስታከብር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከበረው ግን ‹‹የሥርዓተ ፆታ እኩልነት ለዘላቂ ልማት›› (Gender equality today for a sustainable tomorrow) በሚል ነው፡፡
የመጀመርያው ‹‹የሴቶች ቀን›› የተዘጋጀው በአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ አማካይነት ፌብረዋሪ 28 ቀን 1909 ሲሆን፣ ይህም ከዓመት በኋላ በ1910 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የሶሻሊስት ሴቶች ኮንፈረንስ፣ የጀርመን ተወካዮች ‹‹ልዩ የሴቶች ቀን›› በየዓመቱ እንዲዘጋጅ ሐሳብ እንዲያቀርቡ አነሳስቷቸዋል። በመሆኑም የመጀመርያው ዓለም አቀፋዊ የሴቶች ቀን የተከበረው ማርች 19 ቀን 1911 (መጋቢት 10 ቀን 1903 ዓ.ም.) ሲሆን ቆይቶ ግን ወደ ማርች 8 (የካቲት 29 ቀን) መቀየሩ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡
በኢትዮጵያ የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮትን ተከትሎ ከስድስት ወራት በኋላ ዘውዳዊው ሥርዓት ካከተመ በኋላ፣ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ከ1968 ዓ.ም. ጀምሮ የሴቶች ቀን እንዲከበር መወሰኑ ይታወሳል፡፡ በቀዳሚዎቹ ሁለት ዓመታት መሥሪያ ቤቶች ተዘግተው በብሔራዊ በዓልነት ይከበር እንደነበረም አይዘነጋም፡፡