Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአዳማ ዩኒቨርሲቲ የሊጉን ሁለተኛ ዙር ለማስተናገድ የስታዲየም ዕድሳቱን እያጠናቀቀ ነው

አዳማ ዩኒቨርሲቲ የሊጉን ሁለተኛ ዙር ለማስተናገድ የስታዲየም ዕድሳቱን እያጠናቀቀ ነው

ቀን:

  • ክለቦች የሆቴል ዋጋ በዕጥፍ እየጨመረብን ነው ብለዋል      

የቤቲኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ዙር የሚያስተናግደው አዳማ ዩኒቨርሲቲ የስታዲየም ዕድሳቱን እያጠናቀቀ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ከሐዋሳ ከተማ ቀጥሎ የሊጉን አንደኛ ዙር ጨዋታዎች የማሰናዳት ዕድል ተሰጥቶ የስታዲየም መሠረተ ልማቶች አለመሟላታቸውን ተከትሎ ዕድሉን ለድሬዳዋ አሳልፎ የሰጠው ከተማው፣ ሁለተኛ ዙር ጨዋታን ለማሰናዳት ከሊግ ካምፓኒው አዎንታን አግኝቷል፡፡

አጣሪ ቡድን ልኮ የስታዲየም መሠረተ ልማቱን ሲገመግም የከረመው አክሲዮን ማኅበሩ፣ የስታዲየም ዕድሳቱ እየተጠናቀቀ መሆኑን መመልከቱንና ውድድሩ እስከሚጀምርበት መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ቀሪዎች ሥራዎች እንደሚጠናቀቁ ገልጿል፡፡

በመጋቢት መገባደጃ የሚጀምረው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ላይ ለመካፈል ክለቦች ማሪፊያቸውን አዳማ እንዳደረጉ ታውቋል፡፡ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም የመብራት፣ የሜዳ፣ የመልበሻ ክፍልና የልምምድ ሥፍራዎች ዕድሳት የተደረገላቸው ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ውድድሩ እስከሚጀምርበት ቀን ድረስ ይጠናቀቃሉ ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል አክሲዮን ማኅበሩ የሊጉን ሁለተኛ ዙር ጨዋታ መርሐ ግብር አውጥቶ ለክለቦች መላኩም ተሰምቷል፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት በክልል ከተሞች እየተዘዋወረ እያከናወነ የሚገኘው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ክለቦችን ለከፍተኛ ወጪ እየዳረገ እንደሆነ የሚያነሱ አሉ፡፡ ምንም እንኳን ክለቦች ከከተማ ከተማ እየተዘዋወሩ ጨዋታ በሚያደርጉበት ወቅት ለከተሞቹ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ የጎላ እንደሆነ ቢጠቀስም፣ በአንፃሩ ክለቦች ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ እየከተታቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በአንድ ከተማ ውድድር ለማድረግ ቢያንስ ከ30 እስከ 35 ቀናት ቆይታ የሚያደርጉት ክለቦቹ፣ ለሆቴል ከ900 እስከ 1,500 ብር በቀን ወጪ እንደሚያደርጉ ያስረዳሉ፡፡ በዚህም መሠረት አንድ ክለብ ከ30 እስከ 35 የክለቡን አባላቱን በሆቴል የሚያሳርፍ ሲሆን፣ ምግብን ጨምሮ በቀን ለአንድ ሰው እስከ 1,500 ብር ድረስ ወጪ ያደርጋል፡፡

በዚህም ሥሌት አንድ ክለብ በአማካይ ለ32 የቡድኑ አባላት የቀን ምግብን ጨምሮ 1,200 ብር ቢያወጣ በቀን 38,400 ብር፣ እንዲሁም በወር 1,152,000 ብር ወጪ ያደርጋል፡፡ በአራት ከተሞች ቆይታ የሚያደርገው አንድ ክለብ ለሆቴል ብቻ እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ሊያደርግ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ ይኼም በከተሞቹ ላይ ሆቴሎች ጭማሪ ካላደረጉ ነው፡፡

ሆኖም ክለቦቹ ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ ሲያመሩ የሆቴሎች ዋጋ በእጥፍ እየጨመረ መምጣቱ የወልቂጤ እግር ኳስ ክለብ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባው ሰለሞን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አስተያየት ከሆነ፣ ምንም እንኳን የከተሞቹን የንግድ እንቅስቃሴ ለማሳደግ የጎላ ድርሻ ቢኖረውም፣ በአንፃሩ ክለቦች የፋይናንስ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል በማለት ያስረዳሉ፡፡

አብዛኞቹ ክለቦች የመንግሥት ካዝና ላይ የተንጠለጠሉ መሆናቸውን ተከትሎ፣ የራሳቸውን የገንዘብ ምንጭ ለመፍጠር እንደሚገባቸው ይታመናል፡፡ በዚህም ክለቦች በተለያዩ ከተሞች የሚያደርጉትን ጨዋታ በራሳቸው ሜዳ የሚያደርጉበትን የቀድሞ መንገድ ቢከተሉ የተሻለ ነው ሲሉ አቶ አበባው ተናግረዋል፡፡

በአቶ አበባው አስተያየት፣ ክለቦች የፋይናንስ አቅማቸውን ለማሻሻልና ከመንግሥት የገንዘብ ጥገኝነት ለመላቀቅ ውድድሮቹን በራሳቸው መቀመጫ ከተሞች ማድረግ እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ፡፡ ይኼም ክለቦቹ የስታዲየሞቻቸውን መሠረተ ልማት እንዲያሳድጉና የገቢ ምንጫቸው እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል ሲሉ አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡

አብዛኛዎቹ በሊጉ እየተካፈሉ የሚገኙት ክለቦች የገንዘብ ምንጫቸው የከተማ አስተዳደሮች መሆኑንና ታዳጊ ቡድን የሌላቸው ናቸው፡፡ ምክንያቱም የሚለቀቀው በጀት እንኳን ታዳጊ ለማቋቋም ይቅርና ለዋናውም ቡድን በቂ ባለመሆኑ ክለቦች በገንዘብ ዕጦት ምክንያት ለተጫዋቾቻቸው ደመወዝ መክፈል ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡

የአንደኛው ዙር ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሐዋሳና ድሬዳዋ የተከናወነ ሲሆን፣ ሁለተኛው ዙር መጋቢት 21 በአዳማ ጀምሮ መጠናቀቂያውን ባህር ዳር ያደርጋል፡፡

የመጀመርያው ዙርን በ31 ነጥብና በመሪነት ያጠናቀቀው ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን፣ በሦስት ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ የሆነው ወላይታ ድቻ፣ በአራት ነጥብ ልዩነት ሦስተኛ ላይ የተቀመጠው ሐዋሳ ከተማ ነው፡፡ የዓምናው ሻምፒዮን ፋሲል ከነማ በ26 ነጥብ አራተኛ ላይ ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...