Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ገንዘብ ሚኒስቴር 40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ለመግዛት ስምምነት አለመፈጸሙን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ግን ስምምነት መፈጸሙን ተናግሯል

ካለፈው ሳምንት አንስቶ የተከሰተውን የምግብ ዘይት መጥፋትና የዋጋ መናር ችግሮችን ለመፍታት፣ የ40 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዥ ስምምነት አለመፈጸሙን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ጉዳዩ በጅምር ላይ ያለና ጥናት እየተካሄደበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአዲስ አበባና ከኦሮሚያ ንግድ ቢሮዎች ጋር በመሆን ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ በአገሪቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተው የምግብ ዘይት ዋጋ መናር ለመፍታት የሚያግዝ 40 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት በቅርቡ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

የሚኒስቴሩ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ወ/ሮ መስከረም ባህሩ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽንና የኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት እያንዳንዳቸው 20 ሚሊዮን ሊትር ዘይት በልዩ ሁኔታ እንዲያስገቡ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረው ነበር፡፡

ዳይሬክተሯ መበደበኛ የግዥ ሒደቶችን መከተል ወራትን ሊወስድ ስለሚችል በልዩ ሁኔታ የሳዑዲ ዓረቢያ አስመጪ ድርጅት መመረጡንና ሰኞ የካቲት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ስምምነት መፈጸሙን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዓለም ላይ ያለው የምግብ ዘይት ዋጋ የሚታወቅ በመሆኑም አስመጪ ድርጅት መመረጡ ችግር እንደማይፈጥርም አክለዋል፡፡

ወ/ሮ መስከረም በጉዳዩ ላይ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ከሆኑት አቶ ኤፍሬም ተሰማ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት እንደሚቻል ቢጠቁሙም፣ አማካሪው ከዚህ ተቃራኒ ነው የተናገሩት፡፡ እንደ አቶ ኤፍሬም ዘይት ለማቅረብ የተመረጠም ሆነ ከመንግሥት ጋር ስምምነት ያደረገ አቅራቢ የለም፡፡ መንግሥት ሊያስገባ ያሰበው የዘይት መጠንን በተመለከተም፣ ውሳኔ ላይ እንዳልተደረሰና ጉዳዩ በጥናት ላይ ያለ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ኮሚቴ ተዋቅሮ ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ምን ያህል ነው የሚለውን እያጠና ነው፡፡ ይህንን ጥናት ደግሞ በሚቀጥለው ሳምንት ነው የምንጨርሰው፤››  ያሉት አማካሪው፣ የሚገባው ዘይት መጠን የሚታወቀው ከጥናቱ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በገንዘብና በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴሮች እየተደረገ ያለው ጥናት የአገሪቱን ፍላጎት መጠን፣ እንዲሁም ያለውን የምግብ ዘይት አቅርቦትና የጉድለት መጠን እንደሚዳስስና ከጉምሩክ ኮሚሽን መረጃ እንደሚሰበስብ ታውቋል፡፡ ከምግብ ዘይት ፈላጊዎች ውስጥም ቢሆን እንደ የኑሮ ደረጃቸው ፈሳሽና ፓልም ዘይት ተጠቃሚዎችን መለየት እንዳለባቸው አቶ ኤፍሬም አብራርተዋል፡፡

ሰማኒያ በመቶ የሚሆነውን የምግብ ዘይት ፍጆታዋን ከውጭ በምታስገባው ኢትዮጵያ፣ ካለፈው ሳምንት ወዲህ በችርቻሮ በምግብ ዘይት መሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ ታይቷል፡፡ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቶ 800 እና 900 ብር ሲሸጥ የነበረው አምስት ሊትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ከገበያ ጠፍቶ ነበር፡፡

በምግብ ዘይት ላይ የታየው ዋጋ ጭማሪ በዓለም አቀፍ ገበያው ላይ ባለው ጭማሪ ምክንያት እንደሆነ የገለጸው ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ከቀረጥ ነፃ የሚያስገቡ አስመጪዎች የዋጋ ጭማሪና የምርት እጥረት እንዳጋጠማቸው አስታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ አገር ውስጥ የተከሰተው የምርት እጥረት የዋጋ ጭማሪን ማስከተሉን ገልጿል፡፡

በሰኞ ዕለት መግለጫ ላይ የተገኙት አዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ፣ የዋጋ ጭማሪው የተከሰተው መንግሥት በድጎማ ለኅብረተሰቡ በሚያሠራጨው የፓልም ዘይት ላይ ብቻ ሳይሆን በተለምዶ ፈሳሽ ዘይት በሚባለው ጭምር ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ የዋጋ ጭማሪ እንደሚታይ ያስረዱት አቶ መስፍን፣ ነገር ግን መንግሥት በሚያሠራጨውና በአገር ውስጥ አምራቾች ተመርቶ በሚቀርበው የዘይት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዳልተደረገ ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ ከፊቤላና ከሸሙ የግል ዘይት አምራቾች፣ እንዲሁም ከንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሚገኝ በአጠቃላይ ሰባት ሚሊዮን ሊትር ዘይት በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደምታገኝ አቶ መስፍን አስታውቀዋል፡፡

የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተሯ ወ/ሮ መስከረም በበኩላቸው፣ የምግብ ዘይትን ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የአገር ውስጥ ፍላጎትና የሚያስፈልገውን መጠን ከእነ መፍትሔው የሚያጠና ቡድን መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪው አቶ ኤፍሬም የዘይት ግዥን አስመልክቶ የሚደረገው ጥናት በሚቀጥለው ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በማስረዳት፣ ግዥውን ለመፈጸም ጨረታ ወይስ ሌላ አማራጭ ይወሰድ የሚለውን በተመለከተም ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ገልጸዋል፡፡ የሚገዛው የዘይት መጠን በጥናቱ ውጤት ላይ የሚመሠረት ቢሆንም፣ ከ40 ሚሊዮን ሊትር ሊበልጥ እንደሚችል አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች