ለላሊበላ ውቅር አብያተ ቤተ ክርስቲያናት ዕድሳት ተጨማሪ በጀት ያስፈልጋል ተባለ
በአማራና በአፋር ክልሎች ሕወሓት በከፈተው ጦርነት በክልሎች ላይ የደረሰውን ጉዳት ፈረንሣይ እንድታጠና፣ ከፌዴራልና ከክልል መንግሥታት ጥያቄ እንደቀረበላት ተነገረ፡፡
እ.ኤ.አ. ከመጋቢት ወር 2022 እስከ መጋቢት 2023 ድረስ ለአንድ ዓመት በተለያዩ ሁነቶች (ክንውኖች) የሚከበረውን የኢትዮጵያና የፈረንሣይን 125ኛ ዓመት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አስመልክቶ በተሰጠ መግለጫ ላይ እንደተነገረው፣ ካለፈው ዓመት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረውንና ቀጥሎ የሚገኘው ጦርነት ያደረሰውን ጉዳት መጠንና የወደሙ ንብረቶችና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ለማወቅ፣ ፈረንሣይ ጥናት እንድታካሂድ በፌደራልና የክልል መንግሥታት ጥያቄ መቅረቡ ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የፈረንሣይ አምባሳደር ሚስተር ረሚ ማርሾ እንደተናገሩት፣ በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት በተለይም የጤና ተቋማትትን ውድመት በሚመለከትና መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገውን ሁሉ ፈረንሣይ እንድታጠና ተጠይቃለች፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ግጭት ወይም ጦርነት ማስቀረት ወይም መፍታት የሚቻለው፣ ከፖለቲካ ውሳኔም በተሻለ በአገራዊ ምክክር መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ፣ ብሔራዊ ምክክሩን በአገር ደረጃ ለማድረግ እየተሠራ ያለው የሚበረታታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የፈረንሣይ እምነት ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት አገራዊ ውይይቱ ቢካሄድ እንደነበር ጠቁመው፣ አሁንም ሁሉንም ያካተተና ጥንቃቄ የተሞላበት ውይይት ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፖለቲካ ውይይት ሲደረግ ጥበብ እንደሚያስፈልግና የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ለማስቀጠልም ደግሞ የታክስ ሲስተም መዘርጋት፣ የገቢ ክፍፍልን በሚመለከት መሥራትና የፀጥታ ኃይሎች አደረጃጀት ላይ ቀድሞ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አገራዊ ውይይቱን በሚመለከት የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻውን እየሠራ እንደሆነ እንደሚያውቁ የተናገሩት አምባሳደሩ፣ የፈረንሣይ መንግሥት ውይይቱን በሚመለከት ዕገዛ እንዲያደርግ ከተፈለገ በማንኛውም ሁኔታ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያና የፈረንሣይ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከተጀመረ እ.ኤ.አ. ከ1897 ጀምሮ ላለፉት 125 ዓመታት መቀጠሉንና ከዚህ ወር ማርች ጀምሮ እስከ 2023 ማርች ድረስ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካ ትልቁና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት መሆኑን ገልጸው፣ በግለሰቦች ደረጃ የተጀመረው ግንኙነት ግን 160 ዓመታት ማስቆጠሩን አስታውሰዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1907 በዳግማዊ ምኒልክ በተሰጠ ሰፊ ቦታ ላይ በተገነባውና ‹‹ፈረንሣይ ለጋሲዮን›› የሚባል ስያሜ በተሰጠው የፈረንሳይ ኤምባሲ መግለጫ የሰጡት አምባሳደር ማርሾ በትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት፣ በባህል፣ በቅርስና በተለያዩ ግንኙነቶች የሁለትዮሹ ግንኙነት ሳይቋረጥ ቀጥሎ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን መንግሥት የመጀመርያው ፍራንክ (ገንዘብ) በፈረንሣይ አገር መታተሙን፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ኮድ (ፍትሐ ብሔር ሕግ) በሚስተር ፌኔ ዴቪድ መጻፉን፣ የመጀመርያው አውሮፕላን በጃንሜዳ ማረፉንና የጄኔራል ሻርል ደጐል ጉብኝትንና ሌሎች ክንውኖችን ያስታወሱት አምባሳደሩ፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በተለያዩ ኢንቨስትመንቶችና ድጋፎች መቀጠሉን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ 58 የፈረንሣይ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ እንደሚገኙና በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ መሰማራታቸውንም ተናግረዋል፡፡
በፈረንሣይ መንግሥት ዕርዳታ ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ጋር በመተባበር የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዕድሳት ተጀምሮ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት መቋረጡን ጠቁመው፣ ተጨማሪ በጀት ቢያስፈልገውም በቅርቡ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡ የኢዮ ቤልዩ ቤተ መንግሥትን ወደ ሙዚየምነት ለመቀየር የቱሪስት መስህብ እንዲሆን እየሠሩ መሆኑንና በዚህ ዓመት መጨረሻ አካባቢ ሥራው እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡ ወታደራዊ ግንኙነትን በሚመለከት የኢትዮጵያ ባህር ኃይል አባላትን የፈረንሣይኛ ቋንቋ ለማስተማርና ለማሠልጠን የተጀመረው ሒደት፣ በተፈጠረው አገራዊ ሁኔታ የተቋረጠ ቢሆንም በቅርቡ እንደሚጀመርም ተናግረዋል፡፡