Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ አሳሳቢውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት ከወር ወር እያሻቀበ የመጣውን የምግብ ዋጋ ንረት ለመቀነስ፣ ከየትኛውም ጊዜ ይልቅ ከፖለቲካዊ ፍትጊያው ተላቆ ለኢኮኖሚው ፋይዳ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡

ሰፊ የበጀት ጉድለት፣ ውስብስብ የገበያ አሻጥርና ፈጣን የምንዛሪ ምጣኔ መዳከም እያስተናገደ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፣ በየወሩ የሚስተዋልበት የዋጋ ግሽበት እየተንከባለለ መጥቶ በወርኃ የካቲት በተለይም በምግብ ነክ ኢንዴክስ ከፍተኛ ጭማሪ ታይቷል፡፡

በአገሪቱ የተመረጡ 119 የገበያ ቦታዎችን መሠረት አድርጎ በቀረበው የየካቲት ወር 2014 ዓ.ም. የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነፃፀር በ41.9 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በተለይም በእህሎች ዋጋ ላይ በአብዛኛው ጭማሪ እንደታየ የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የዋጋ ንረቱን ለመቋቋም የሚያስችል ወርኃዊም ሆነ ዕለታዊ የገቢ ጭማሪ ላላገኘው ብዙኃኑ የኅብረተሰብ ክፍል በየወሩ እየተጋፈጠው ያለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት መንግሥት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለምላሹ ካልተጋበት፣ በቀጣይ የሚመጣው ቀውስ ከፍተኛ እንደሆነ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢኮኖሚና የፖሊሲ አማካሪ ባለሙያዎች አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በዚህ ወቅት አገሪቱን እያስተዳደረ የሚገኘው የብልፅግና ፓርቲ እያከናወነ በሚገኘው ጠቅላላ ጉባዔ፣ ከፖለቲካ ሽኩቻዎች ይልቅ ለአንገብጋቢው የኢኮኖሚ ቀውስ መፍትሔ እንዲሰጥ ባለሙያዎቹ ጠይቀዋል፡፡

የኢኮኖሚ ጉዳዮች ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ፣ ምንም እንኳን በሚመለከተው የመንግሥት ተቋም በየወሩ ይፋ የሚደረገው የዋጋ ግሽበት አኃዝ ሁሉንም የሚያስማማ ባይሆንም፣ የተለያዩ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጫናዎችን እያስተናገደ ያለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እስካሁንም የዋጋ ንረቱ በ30 እና 40 በመቶ መቆየቱ የሚያስገርም ነው ሲሉ ለሪፖርተር ተናግርዋል፡፡

ከሁሉም በፊት መታየት ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ የዋጋ ንረት እንዴት ነው እየተሰላ የሚገኘው የሚለው መሠረታዊ ነገር ነው ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ 300 እና ከዚያ በላይ ሸቀጦች አንድ ላይ ተወስደው ጤፍም ሆነ ድንብላል፣  ስንዴ ሆነ ዱባ በአንድ ምድብ ተጨፍልቀው ሲቀርቡ የሚቀርበው ቁጥር መሬት ላይ ካለው እውነተኛ የዋጋ ንረት ጋር የማይስተካል ዝቅተኛ ቁጥር ሊያስገኝ ይችላል ብለዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ስንዴ፣ ጤፍ፣ ገብስ፣ ዘይት፣ ስኳርና መሰል አስፈላጊ አሥር የሚደርሱ ግብዓቶች ተሰልተው የዋጋ ንረቱ ቢሠራ በአማካይ የሚገኘው ቁጥር 100 ፐርሰንት ሊገባ ይችላል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሌሎች አገሮች የዋጋ ንረትን ከቦታ ቦታ ለየብቻው እንደሚቀርብ የገለጹት፣ የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ አዲስ አበባና ምንጃር ላይ አንድ ነዋሪ ለቤት ኪራይ እኩል ወጪ እንደማያወጣ ቢታወቅም ወርኃዊ የስታትስቲክስ ሪፖርት ሲቀርብ ግን መረጃው በመላው ኢትዮጵያ ተብሎ ሲቀርብ ይስተዋላል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የዋጋ ንረትን በተመለከተ በእያንዳንዱ ክልል በየራሱ ተሠርቶለት የአገሪቱንም አማካይ ማስቀመጥ፣ በቦታዎቹ ሊስተካከል የሚገባውን ጉዳይ ለማስተካከል ያስችላል ያሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ፣ ቁጥሮች ላይ ያለው ውዝግብ በጣም መታረቅ አለበት ብለዋል፡፡

የዋጋ ንረቱ በዚህ ወቅት ብዙ ምክንያቶችን ጨምሯል የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው፣ በስፋት የሚታወቁት የማምረቻ ወጪዎች በጣም ውድ ከመሆናቸው የተነሳ በብዛት ሳይመረት ሲቀር የሚፈጠር የዋጋ ንረት፣ መካከለኛ ገቢ ያለው የኅብረተሰብ ክፍል እየጨመረ ሲመጣ የሚመጣ የዋጋ ንረት፣ እንዲሁም የሕዝብ ብዛት ማደግን ተከትሎ የሚፈጠረው የብዙ አገልግሎቶችና ፍላጎቶችና የሸመታ ዕድገት የሚጠቀሱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ዓለም አቀፋዊ የምርቶች ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ የሚመጣ ግሽበት (ኢምፖርትድ ኢንፍሌሽን) በከፍተኛ ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ ኢኮኖሚው አብሮ ገብቷል፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅምም በሒደት እየተዳከመ መምጣቱ  የሚጠቀስ ነው፡፡ ምርታማነት ከቁጥር አንፃር ሲታይ በተወሰነ ክልሎች ላይ የሚታረሱ መሬቶችን መሠረት አድርጎ እንደጨመረ የሚያሳይ አኃዝ ይኖራል፤›› ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ ነገር ግን ከሚፈለገው ቁጥር አንፃር ሲታይ ቁጥሩ በቂ ነው ብሎ ለማንሳት አይቻልም ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በሦስት ክልሎች ከጦርነት ጋር ተያይዞ መደበኛ የማምረት ሥራ ሙሉ በሙሉ መቆሙን፣ የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎችም የድርቅ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺና መተከል ዞኖች ውስጥ ያሉ ለም አካባቢዎች የመሠረታዊ አገልግሎት መቋረጥ ታክሎበት አገሪቱ በተጠናቀቀው ዓመት በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ አሳልፋለች ብለዋል፡፡

በመጋቢት ወር የዋጋ ንረቱ ከዚህ በላይ እንደሚሆን ይጠበቃል ያሉት አቶ ዋሲሁን፣ ይህም የእነ ሩሲያና ዩክሬይን ግጭት ከሥጋት ባለፈ በተግባር በኢኮኖሚው ውስጥ ጫና ማሳደር ስለጀመረ መሆኑን በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡ አገሪቱ ከደረሱባት ቀውሶች አንፃር በዋጋ ግሽበቱ ላይ የታየው አኃዝ ከዚህም በላይ ይሆን ነበር ያሉት የኢኮኖሚ ተንታኙ፣ ሆኖም መንግሥት ከቀረጥ ነፃ የሚገቡ ቁሶችን መሸከሙ፣ የነዳጅ ዋጋ ባለበት እንዲቀጥል ማድረጉ፣ በአጠቃላይ ድጎማው የዋጋ ግሽበቱን 30 እና 40 በመቶ ውስጥ እንዲቆይ ዕድል ሰጥቶታል ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ዋሲሁን አስተያየት ሽር ጉዶችን መቀነስና ቁጠባን ማሳደግ በሚገባበት አገር ውስጥ ለምርታማነት መሯሯጥ ሲገባ፣ ከሕዝብ አንስቶ አስከ መንግሥት ለዚህ ሲተጉ ማየት አልተቻለም፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (State of Emeregency) የሚያስፈልገበት ደረጃ ላይ ይገኛል፤›› የሚሉት አቶ ዋሲሁን፣ ይህም የኢኮኖሚ መረጋጋት ከሌለ ፖለቲካዊ መረጋጋት ስለማይመጣ ነው ሲሉ ያክላሉ፡፡ ‹‹ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን አጥቶ መታገስና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን አጥቶ መታገስ እኩል አይደለም፡፡ በመሆኑም መንግሥት በዚህ ወቅት ከኢኮኖሚው የቀደመ አጀንዳ ሊኖረው አይችልም፡፡ በፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ላይም ዋናውና አከራካሪ ርዕሰ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ የኢኮኖሚው ሁኔታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የፖሊሲ አማካሪ የሆኑት አቶ አማንይሁን ረዳ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት ለግብርናው ዘርፍ በመንግሥት ደረጃ ሲሰጠው የቆየው አናሳ ትኩረት ዛሬ ላይ ለሚስተዋለው የአቅርቦትና የፍላጎት አለመጣጣም፣ እንዲሁም ከወር እስከ ወር እያሻቀበ ለመጣው የዋጋ ንረት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል ይላሉ፡፡

ይህም ብቻ ሳይሆን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሥራዬ ብሎ ኢኮኖሚውን ለማስተካከል የሚያስችሉ የፖሊሲ ውሳኔዎችና ዕርምጃዎች ባለመውሰዱ እንጂ፣ ትክክለኛና የግብርናና የሌሎች የኢኮኖሚ ማሻሻያ የፖሊሲ አማራጮች መተግበር ቢችል ኖሮ ከሦስት እስከ አራት ዓመት ባለ ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮችን ለማስተካከል እንደሚቻል አስርድተዋል፡፡

ግብርናን አዘምኖና ምርታማነትን አሳድጎ ገበያ ውስጥ የምግብ ምርቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማቅረብ፣ ግብርናው ለሕዝቡ ቀለብ ከመስፈር አልፎ ለኢንዱስትሪዎች በቂ ጥሬ ዕቃ ለማቅረብ እንዲችል ከተፈለገ መወሰን ያለባቸው በርካታ የፖሊሲ ውሳኔዎች አሉ ያሉት አቶ አማንይሁን፣ ሆኖም መንግሥት በዚህ ጊዜ ከኢኮኖሚው ይልቅ የፖለቲካው ጉዳይ በልጦበታል ብለዋል፡፡

ግብርና ምግብ የሚባለውን ለመኖር መሠረታዊ የሆነ ግብዓት የሚያቀርብ፣ 70 በመቶ የኤክስፖርት ሽፋን የሚይዝ፣ 80 በመቶ ሕዝብ የሚያስተዳድር ዘርፍ በመሆኑ የሚመጥነውን ያህል ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚሉት አማካሪው፣ መንግሥት በሚመድበው በጀትም ሆነ በባንኮች አማካይነት ወደ ግብርና የሚሄደውን ገንዘብ ሊያሳድግ ግድ ይለዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የፖሊሲ አማካሪው እንዳስታወቁት፣ የሰው ጥያቄ የኑሮ ውድነት በሆነበት በዚህ ወቅት መንግሥት ቢሮ ከማደስ ወጥቶ የትኛው ጥያቄ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል? የትኛው ቀጣይ ሊመለስ ይችላል?  የሚለውን በትክክል ሊያውቅ ይገባል፡፡

ባለፉት አሥር ዓመታት ውስጥ በአማካይ ኢትዮጵያ ከኤክስፖርት ስታገኝ የቆየችው ገቢ ሦስት ቢሊዮን ዶላር መሆኑን፣ ከውጭ ለምትገዛቸው ግብዓቶች 15 ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደምታወጠ ያስታወሱት አቶ አማንይሁን፣ በወጪና በገቢ መካከል ያለውን የ12 ቢሊዮን ዶላር ልዩነት ይዞ የአገር ውስጥ ምርትና ምርታማነት ሳያሳድጉ፣ የወጪ ንግዱን ለማሳደግና የንግድ ሚዛን ጉድለት ለማስተካከል ተብሎ የብር የመግዛት አቅምን ማዳከም ከድጡ ወደ ማጡ መሄድ ነው ብለዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት የብር የመግዛት አቅም 82 በመቶ የመግዛት አቅሙ እንዲዳከም ተደርጓል ያሉት አማካሪው፣ ኤክስፖርተሮችን ለማሳደግና የንግድ ሚዛን ለማስተካከል የሚል ምላሽ ከመንግሥት የሚሰጥበት ይህ አስተሳሰብ በምን ሁኔታ ነው የሚሠራው ብሎ ማየት ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹የምርት እጥረት፣ የኮንቴይነር እጥረት፣ የመርከብ ዋጋ ማሻቀብ፣ ምዕራባውያን የገቡበት የዩክሬይንና የሩሲያ ጦርነት፣ ይህንንም ተከትሎ የመጣው የነዳጅ ዋጋ ማሻቀብ፣ ምግብ ነክ የሆኑት የስንዴና የዘይት ምርቶች አቅርቦት ዕጣ ፋንታ ችግሩን ከዓለም አቀፍ አንስቶ እስከ አገር ቤት ድረስ ያባብሱታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተፅዕኖዎች ተደምረው በፈጣን መፍትሔ ዋጋውን ማራጋጋት የሚችል መንግሥት ሊኖር ይገባል፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡

የኑሮ ውድነት እየተባበሰ ሄዶ የሚፈጥረው ችግር ከፍተኛ የፖለቲካ ቀውስ ነው  ያሉት አቶ አማንይሁን፣ ከዚህ በፊት ከድርና ዕርዳታ ሲያቀርቡ የነበሩ አገሮች ለራሳቸው ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች በመጠመዳቸው ድጋፍ አገኛለሁ ተብሎ ኢኮኖሚን ቸል ማለት ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች