Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹በፆታ ላይ የተመሠረተን አድልኦ ለመታገል የሥርዓተ ፆታን መነጽር ማጥለቅ ያስፈልጋል›› ወ/ሮ...

‹‹በፆታ ላይ የተመሠረተን አድልኦ ለመታገል የሥርዓተ ፆታን መነጽር ማጥለቅ ያስፈልጋል›› ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት

ቀን:

በፆታ ላይ የተመሠረተ አድልኦን መታገል ሥልጠና እንደሚጠይቅና የሥርዓተ ፆታ መነጽር ማጥለቅ እንደሚያስፈልግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ተናገሩ፡፡ ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ባለፈው ማክሰኞ የሴቶች ቀን በካፒታል ሆቴል ሲከበር ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት አድልኦን ማጋለጥና ቅቡልነትን ለመንፈግ ንቃት ያስፈልጋል፡፡ ችላ ማለቱ ያለማወቅ አካል ነው፡፡

ሥነ ምግባሩ ያላደገ የአመራርም ሆነ የሥራ ባልደረባ በሴቶች ላይ የሚደርሱት አድልኦና ጫና በሴቶች ላይ ጎልቶ ይውጣ እንጂ፣ እንዲህ ያሉ ሰዎች ለማንኛውም ሰው ርዕታዊ ሊሆኑ እንደማይችሉና አመራራቸውም ቢፈተሽ ሁለንተናዊ ጉድለት እንደሚታይበት ተናግረዋል፡፡

‹‹ለሴቶች እኩልነት ልብ የሌላቸው ሴቶችም የሉም ማለት አይቻልም›› ያሉት ወ/ሮ መዓዛ፣ ሴቶችም የአድሎ ስሜት የተለማመዱ፣ የተቀበሉና የተጫናቸው የዚሁ ማኅበራዊ እውነታ ውጤቶች በመሆናቸውና ብዙዎቹ ችግሮች ከዕውቀት ማነስ የሚነጩ መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹አስተሳሰባቸው የሰፋ ማን አሳደጋቸው? የት አወቁት? የሚያሰኙ ወንዶችም አሉ፡፡ በእንደዛሬው ቀን እንዲህ ያሉ ምሳሌ ወንዶችን ማመስገን ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ የተከበረው የማርች 8 መሪ ሐሳብ “Gender Equality Today for Sustainable Tomorrow) ‹‹ ዛሬ የፆታ እኩልነት ከተረጋገጠ ዘላቂነት ያለው ነገን ማምጣት ይቻላል›› በሚል ነው፡፡

የዓመቱ የማርች 8 መሪ ቃል እንደሚገልጸው ‹‹የሴቶች እኩልነት የግለሰብ ጉዳይ አይደለም፣ የሴቶች ሙሉ ተሳትፎ ተቋሞቻችን ለመገንባት፣ ሰላም ለማምጣት፣ ልማት ለማረጋገጥ፣ ቁልፍ ሀብት ነው፣ በተግባርም እያየነው ነው፡፡ ስለሴቶች አመራር ጥንካሬና ተግዳሮቶች፣ መነጋገር ያስፈልገናል፡፡ አድልዎና አግላይነት፣ ተደምሮ ሲቆይ እየቦረቦረን ኃይላችንን እየቀነሰብን ይመጣል፡፡ ሴት አመራር አባላት ደግሞ በዚህ ረገድ ልዩ ኃላፊነት አለብን፡፡ እኛ ካልተናገርን ሁሉም በጨለማ ተበድሎ ይኖራል፡፡ በግሌ ይህን አልቀበለውም፣ ከእምነቴና ከታሪኬም ጋር ተቃራኒ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የሰው ልጆች መብቶች በተለይም የሴቶች መብቶች እንደማይነጣጠሉም ማስታወስ ይገባል ያሉት ወ/ሮ መዓዛ የሴቶች የሲቪልም ሆነ የፖለቲካ መብትና ተሳትፎ ከኢኮኖሚ መብት ጋር ተያያዥ ናቸው፡፡ ለምሳሌ የግል ገቢ የሌላት ሴት ከሚበድላት ባል ጋር ለመኖር ትገደዳለች፡፡ አማራጭ የሥራ ዕድል የሌላት ሴት የመጥፎ አለቃ ዕብሪትና ትንኮሳ ችላ ለመኖር ትገደዳለች፣ ትስስሩ ግልጽ ነው፡፡ በሴቶች አመራር ረገድ የሚነሳው ዋናው ጥያቄ ሴቶች ወደ አመራር ሥራ ሲመጡ በተለመደው ሁኔታ ወንዳዊ /Patriarchal/ አመራር መከተል አለባቸው ወይስ አሳታፊ፣ በመግባባት ላይ የተመሠረተ፣ ለስላሳ የማሳመኛ መንገዶችን የተከተለ መሆን አለበት? በተግባር ያለው አካሄድ ምን ይመስላል የሚለው መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ጨምረው እንዳብራሩትም በአግባቢነት ላይ የተመሠረተውን የአመራር ሞዴል “Femist Leadership” በሚለው የአመራር ፍልስፍና የሚፈልግ ነው፡፡ እንዲሁ ሲታይ ይህ ተመራጭ የአመራር አካሄድ ነው፡፡ ችግሩ ግን ዓለም ላይ ባለውና በአጠቃላይ በወንዶች የሥልጣን ዕይታ በተገነባው የአመራርና የአሠራር ሒደት እንዲህ ያለው በመግባባትና በአሳታፊነት ላይ የተመሠረተ አመራር ሲመጣ የቆየው ሥርዓት እንዴት ይመለከተዋል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ከነበረው አሠራር ጋር ይዋሃዳል ወይስ አብሮ አይሄድም የሚለው ጥያቄ ሰፊ ውይይት የሚጠይቅ ነው፡፡

ሴት መሪዎች ያላቸው ምርጫ ሁለት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ ሥልጣንና ኃላፊነታቸውን ይዘው ለመራመድ በዚያው በተለመደው የአመራር አካሄድ መጓዝ ወይም ሰዎችን ያማከለ፣ ውጤት ላይ ያተኮረ የማሳመን ችሎታ ላይ የተመሠረተ፣ አመራር መከተል ቢሆንም ሁለቱም አካሄድ ለሴቶች አስቸጋሪ መሆኑን አክለዋል፡፡

ሴት መሪዎች ጠንካራ፣ ሥልጣናቸውን ከላይ ወደታች በመጫን የሚጠቀሙ ሲሆን ‹‹እርሷ እኮ ክፉ ነች፣ ሌላ ፍላጎት አላት፣ ወዘተ ይባላሉ›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ፣ ለወንዶች ግን ይህ አካሄድ ተቀባይነት አለው ‹‹ቆራጥ አመራር ይሰጣል›› ይባላል፡፡ ሴት መሪዎች ሁለተኛውን አካሄድ ሲመርጡ ደግሞ እሷ እኮ ‹‹ቅን ናት›› የዋህ ናት፣ የሚል ስም ይሰጣትና ልዘዝሽ ባዩ እንደሚበዛ ጠቁመዋል፡፡

የአመራር ጥበብ ከአውዱ ጋር የተዛመደ፣ በተለያየ ማኅበራዊ፣ ሥነ ልቦናዊ ማዕቀፍ፣ የዕውቀት ስፋትና ሌሎች ሁኔታዎች ከግምት ያስገባ መሆን አለበት የሚባለው፣ የአመራር ስልቱ ከብስለት ደረጃው ጋር ዑደት ከሌለው ተግዳሮቶች ስለሚያጋጥመው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹ሴቶችን ወደ አመራር ማምጣት ራሱን የቻለ ትግል አለበት፣ ከዛሬ 20 ዓመት በፊት እኔ በሴቶች ጉዳይ መሥራት ስጀምር የፓርላማ ሴቶች አባላት ቁጥር አራት በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፎአቸው ይደግ ብለን ስንታገል እንደ ከፍተኛ የፖለቲካ ቅስቀሳ ተቆጥሮብን ‹‹አሁን ተዳፈራችሁ›› የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክቶች ደርሰውን ነበር፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ሒደት የሕግ ማዕቀፍ በማሻሻል፣ ደጋፊ ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እንዲሁም የሴቶች መሪነትን ለማሳደግ እያደጉ የሄዱ ብርቱ ዕርምጃዎች መወሰዳቸውን፣ ይህ በሒደቱ፣ በትግሉ የተሳተፉትን ብቻ ሳይሆን የአሁኑ ትውልድ ድል ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚችል አክለዋል፡፡

የሴቶችን እኩልነትና ተሳትፎ በማረጋገጥ ረገድ ሕግን በማሻሻል የተወሰደውም ዕርምጃም ሆነ እያደገ የሄደው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ፣ ከዚያም አልፎ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ሴቶች በአስፈጻሚው የመንግሥት ቅርንጫፍ ያላቸው ሚና እንዲያድግ መደረጉ፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሴት መሆናቸው፣ እሳቸውም ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መሾማቸውን ቀሎ የሚታይ ሳይሆን ታሪካዊ ፈር ቀዳጅ ዕርምጃዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ውሳኔ ሊወሰዱ የሚችሉ መሪዎች በራሳቸው የሚተማመኑ ብቻ ሳይሆኑ፣ ራሳቸውን የሚያከብሩ በመሆናቸው እንዲህ ያሉ መሪዎች ሴቶችን በመሪነት ብቻ ሳይሆን ብዙ መሰናክል አልፈው የደረሱ መሆናቸውን፣ እናትነታቸው ትርጉሙ ምን እንደሆነ የመረዳት አቅም ስላላቸው፣ ሴት መሪዎችን የሚመለከቱት እንደ ልዩ ምልክት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የደቡብ አፍሪካው የነፃነት ትጋይና መሪ የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ እንደ ማንኛውም የሰው ልጆች ትግል ‹‹አንዱን ተራራ ስንወጣው ሌላው ይጠብቀናል›› ማለታቸውን አስታውሰው ሴቶች ኃላፊነት ሲሰጠን የሚጠብቀን ኃላፊነቱን አትወጣውም የሚለው ጥርጣሬ ብቻ ሳይሆን ተማረን ኃላፊነቱን እንድንተወው ጭምር የሚደረጉ ግፊቶች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ስለሴቶች እኩልነት ማንም ወንድ ቢጠየቅ ‹‹እኔም በእናቴ ሴት ነኝ››፣ ‹‹ሚስቴ ሴት ነች››፣ ‹‹ሴት ልጅ አለችኝ፣ እኔ በሴቶች መብት አምናለሁ እንዲህ ያለ ነገር አላውቅም ይሏችኋል፡፡ ይህን የሚሉትም ከልባቸው ሊሆን  ይችላል፡፡ ምክንያቱም አስተሳሰባቸው የተዋቀረው ሴቶች ባመጡት እምነት፣ የግንዛቤ መጠንና ብስለት ደረጃ ላይ የተመሠረተ ስለሆነ የሚፈጽሙት ስህተት ቢኖር ምክንያት ከሚሰጡት በስተቀር፣ አድሎአዊ  አስተሳሰብ አለኝ  ብለው አይገነዘቡም፣ ይህ በእንግሊዝኛ ቋንቋ “Embedded Bias” ‹‹የተቆራኘ ዝንባሌ›› ልንለው እንችላለን፡፡ አውቆ አጥፊዎችም  ይኖራሉና፤›› ብለዋል፡፡

ይኼንን ችግር እንኳንስ ኢትዮጵያ አድገናል የሚሉት አገሮችም ገና ያላሸነፉት፣ እየተናነቃቸው ያለ፣ ብዙ ሀብት የሚፈስበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፣ የተባበሩት መንግሥታትና የብሔራዊ መንግሥታት ትልቅ ዓላማና የሥራ ፕሮግራም መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

ጥናቶችን እንደምታነቡት ሥልጠና ጥሩ ቢሆንም ሰዎች ራሳቸውን ለማሸነፍ  ሥልጠናም ውስንነት አለው፡፡ በሰዎች እኩልነት፣ በሰዎች መብት የማያምኑ ሰዎች ዋናው ትግላቸው፣ እንቅልፍ የሚያሳጣቸው ጉዳይ፣ ሌላውን እንዴት አሸንፋለሁ የሚለው እንጂ ራሴን እንዴት አሸንፋለሁ የሚለው አይደለም፡፡ ነገር ግን ስኬት፣ ውጤታማነት የሚገኘው ራሳችንን ስናሸንፍ ብቻ ነው›› ብለዋል፡፡

‹‹በበኩሌ እስካሁን  በከዘራ  የምራመድበት መንገድ ያሳየን ሰው አላጋጠመኝም፣ ሌሎች መገለጫዎች ግን  በሽበሽ ናቸው፤›› በማለትም አክለዋል፡፡  

አሁን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ካውንስል መሪ የሆኑት ሚሼል ባሽሌት (Michelle Bachelet) የቺሊ ፕሬዚዳንት እያሉ ስለሚገጥማቸው ሁኔታ ሲናገሩ፣ ‹‹ስብሰባ ስመራ እኔ የተናገርኩትን ወይም አንዲት የስብሰባው ተካፋይ ሴት የተናገረችውን፣ ሌላ ወንድ ተሳታፊ በሌላ አነጋገር ሲደግመው ‹‹ኦ ሚስተር እከሌ እንዳሉት›› ተብሎ የሚጠቀሰው የወንዱ ነበር፤›› ማለትቸውን ገልጸው፣ ‹‹ስለሚያግጥሙን ሁኔታዎች እርግጠኛ ነኝ ሁላችንም ተመሳሳይ ማስታወሻዎች አሉን፡፡ እርሳቸው ግን ከእኛ የሚለዩት እኔ እኮ ይኼንን ነጥብ አሁን አንስቼው ነበር በማለት ትምህርት እየሰጡ ማለፋቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

ዘላቂው እምነታቸው በትዕግሥት፣ በብስለት ላይ ተመሠረተ የግል ፍላጎትና አጀንዳን ማዕከል ያላደረገ፣ ሰዎችን ከጥንካሬና ድክመታቸው ጋር የሚቀበል፣ የሚረዳ፣ ለማስተደርና ለመመለስ የሚጥር፣ በአርአያነት ሰዎች እንዲማሩ የሚያደርግ አመራር መከተል መሆኑንም አክለዋል፡፡ ይኼን ለሴቶች ብቻ ሳይሆን ለወንድ መሪዎችም እንደሚመኙት እንዲህ ዓይነቱን አመራር የሚከተሉ ሰዎች ለማንም ምንም ነገር ለማረጋገጥ ሳይሆን በአገልጋይነት ላይ በማተኮር እንደማያስመስሉና ትሁት መሆናቸውን፣ ከመናገራቸው በፊት እንደሚያስቡ፣ ቁጥቦች መሆናቸውን፣ እንደማያስመስሉና በጀርባ ውሸት እንደማያሰራጩ፣ አላግባብ የሚጋፈጧቸውንም ራሳቸውን በመቆጣጠር ይመልሳሉ፣ እንደምንም ነገሮችን ለማሳካት እንደሚጥሩ ተናግረዋል፡፡››

የእነዚህ ዓይነት መሪዎች ችግር ከዚህ የተለየ እሴት ካላቸው ሰዎች ጋር ሲገናኙ እንዴት ይሆናል የሚለው መሆኑን ጠቁመው ይህ ትልቅ የአመራር ትምህርት የጥናት ጥያቄ ሊሆን እንደሚችልና ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ጥበብ “Wisdom” እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ትልቁ ችግር ዕውቀት ከትምህርት ቤት የሚገኝ ሲሆን Wisdom የዕድሜ ልክ ጥረትን፣ ክፍት አዕምሮን እንደሚጠይቅም አክለዋል፡፡

Stephen Hawking የተባለው የፊዚክስ ዘርፍ ሳይንቲስት ባጋጠመው የጤና ችግር ምክንያት መንቀሳቀስም ሆነ መጻፍ እንዲሁም መናገር አይችልም ነበር፣ ነገር ግን በዘመናዊ ማሽን ዕርዳታ በፊዚክስ ትልልቅ የሳይንስ ግኝቶችን ትቶ ዓለምን እንደተሰናበተና ‹‹የዕውቀት ትልቁ ጠላት ድንቁርና አይደለም፣ ስለማያውቁት ጉዳይ አውቃለሁ ብሎ ማሰብ ነው›› የሚለው መልዕክቱን እንደሚወዱት ጠቁመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...